Site icon ETHIO12.COM

ጋይንት ከአሸባሪው ቡድን ነጻ ሆነ!

– የአሸባሪው ቡድን ጉና ተራራ ላይ እንዲቀበር በማድረግ ታሪካችንን ማደስ ችለናል

በጀግናው የሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ በአማራ ልዩ ኃይል፣ ሚሊሻ፣ ፋኖና በሕዝቡ ተጋድሎ አሸባሪው የትህነግ ቡድን በደቡብ ጎንደር ከፍተኛ ኪሳራ ደርሶበታል። በዚህም ወሯቸው የነበሩ አካባቢዎችን ጥሎ ለመፈርጠጥ ተገዷል።

የደቡብ ጎንደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ ቀለምወርቅ ምህረቴ ወቅታዊ ጉዳይን አስመልክቶ ከነፋስ መውጫ ከተማ ነዋሪዎች ጋር ውይይት አድርገዋል።

አቶ ቀለመወርቅ የአሸባሪው የህወሃት ቡድን በሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ በአማራ ልዩ ኃይል፣ ሚሊሻ፣ ፋኖና ሕዝቡ ተቀጥቅጦ ፈርጥጧል ብለዋል።

በርካታ የአሸባሪው ቡድን ጉና ተራራ ላይ እንዲቀበር በማድረግ ታሪካችንን ማደስ ችለናል ነው ያሉት።

ዋና አስተዳዳሪው ለጠላት ርዝራዥ ከላይም ከታችም እሳት ልንሆንበት ይገባል ብለዋል።

ከጠላት ጋር በነበረው ትግል በርካታ በታሪክ የሚዘከሩ ጀግኖች ሊፈጠሩ እንደቻሉም ተናግረዋል።

“የጋይንት ወጣቶች በአውደ ግንባር ላይ ስንቅ በማቀበልም የከፈሉት መስዋእትነት መቼም አይረሳም፤ አሁን የተገኘዉን እፎይታ እስከ መጨረሻ የድል ግብ ሳንቆጥር አሸባሪውን ቡድን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለመቅበር በሚደረገው ትግል ሁላችንም መተባበር አለብን” ብለዋል።

“ባንዳዎችን በተጨባጭ ማስረጃ ለቅመን በእናንተ ፊት ዋጋቸውን እንከፍላቸዋለን” ነው ያሉት።

የተጎዱ መሠረተ ልማቶችን በተመለከተም ዋና አስተዳዳሪው ለነዋሪው ማብራሪያ ሰጥተዋል። ጠላት ካወደመው አንዱ የስልክ መስመር ተመልሶ አገልግሎት እንዲሰጥ ዛሬ ጥገና መጀመሩን ተናግረዋል።

ሌሎች መሠረተ ልማቶችም በየደረጃው የሚጠገኑ መሆኑን አቶ ቀለመወርቅ ገልጸዋል።

“የጋይንት ወጣቶች በአደረጃጀታችሁ አካባቢያችሁን በደንብ የመፈተሽና ጠላትን የመለየት ሥራ መሥራት ይኖርባችኋል” ብለዋል።

ዘጋቢ:–ቡሩክ ተሾመ. (አሚኮ)

Exit mobile version