Site icon ETHIO12.COM

ሁሉም የእርዳታ ድርጅቶች ኢትዮጵያ ውስጥ ሲሰሩ የሃገሪቱን ህጎችና መመሪያዎች ማክበር አለባቸው — ዶክተር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ

“ሁሉም የእርዳታ ድርጅቶች ኢትዮጵያ ውስጥ ሲሰሩ የሃገሪቱን ህጎችና መመሪያዎች ማክበር አለባቸው” ሲሉ የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ዶክተር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ ገለጹ።

ዶክተር ጌዲዮን ከቢቢሲ ሃርድ ቶክ ፕሮግራም ጋር ባደረጉት ቆይታ በኢትዮጵያ መንግስት ተወስዶ የነበረውንና ሌሎች ወቅታዊ ጉዳዮችን በተመለከተ ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በማብራሪያቸውም አንዳንድ የእርዳታ ድርጅቶች በአገሪቱ ያለውን ሁኔታ ለማባባስ ሙከራ ቢያደርጉም አብዛኞቹ መንግስት የወሰደውን የተናጠል ተኩስ አቁም ውሳኔ በበጎ በመውሰድ የሰብአዊ እርዳታ ስራቸው እያካሄዱ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

በመሆኑም ሁሉም የእርዳታ ድርጅቶች ኢትዮጵያ ውስጥ ሲሰሩ የአገሪቱን ህጎችና መመሪያዎች ማክበር እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

ለግብርና ስራና ለእርዳታ ስርጭት ሲባል የተናጠል ተኩስ አቁም ውሳኔ ቢደረግም አሸባሪው ህወሃት ህጸናትና ሴቶችን ለጦርነት በማሰለፍ በአፋርና አማራ ክልሎች በፈጸመው ትንኮሳ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ንጹሃንን በማፈናቀልና ብዙዎችን በመግደል የተኩስ አቁሙን ዋጋ እንዳሳጣው ጠቅሰዋል።

“በአፋር በኩል የተከፈተው የእርዳታ ማጓጓዣ መስመር በአሸባሪው ቡድን በመዘጋቱ ሰብአዊ እርዳታ በታሰበው ልክ ሊደርስ አልቻለም” ብለዋል።

አሸባሪው ቡድን የመልሶ ማልማት ስራዎች እንዳይተገበሩ የኤሌክትሪክና የቴሌኮም ባለሙያዎችን በመግደል አደጋ በመደቀኑ ጥገናውን ማድረግ እንዳልተቻለም ገልጸዋል።

“የሰብአዊ መብቶች ተሟጋች ነን የሚሉ ድርጅቶች የሚያወጧቸውን ሪፖርቶች ምርመራ የሚደረግባቸውና በቀላሉ የሚታለፉ አይደሉም” ያሉት ዶክተር ጌዲዮን፤ “አምነስቲ ኢንተርናሽናል ያቀረባቸው ሪፖርቶችን በጥንቃቄ በመመርመር እውነታዎችን አረጋግጠን ፍትህ ለማሰጠት ስራዎችን እየሰራን ነው” ብለዋል።

ምርመራዎች ባልተጠናቀቁበት ሁኔታ ድምዳሜ ላይ መድረስ የሽብርተኛውን ድርጅት ወንጀሎች ለመሸፈን የሚደረግ ጥረት እንደሚመስልም አመላክተዋል።

ህወሓት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሸባሪ ተብሎ ስለተፈረጀ ለድርጅቱ የሚደረጉ ድጋፎች ሁሉ ወንጀሎች እንደሆኑም አስገንዝበዋል።

አሸባሪው ህወሃት ለሶስት አስርታት የዘለቀ አምባገነናዊ አገዛዝ ቢያሰፍንም የህዝቡን ስነልቦና ማሸነፍ እንዳልቻለም ገልጸዋል። (ኢዜአ)

Exit mobile version