ዓለም አቀፍ የእርዳታ ተቋማት በአማራና አፋር ክልሎች የሰብዓዊ እርዳታ እንዲያቀርቡ የሰላም ሚኒስቴር ጠየቀ


ዓለም አቀፍ የእርዳታ ተቋማት በአማራና አፋር ክልሎች የሰብዓዊ እርዳታ እንዲያቀርቡ የሰላም ሚኒስቴር ጠየቋል።

የኢትዮጵያ መንግስት የተናጠል ሰብዓዊ ተኩስ አቁም ከወሰነበት ጊዜ ወዲህ አሸባሪው ቡድን ህውሃት በአማራ እና አፋር ክልሎች በፈጸመው ወረራ ምክንያት ቁጥራቸው 4.5 ሚሊዮን የሚገመት ዜጎቻችን ለጉዳት ለጉዳት መጋለጣቸውን የሠላም ሚኒስቴር አስታውቋል።

ህወሓት በንፁሃን ላይ የሚፈጽመውን ጥፋት ለማስፋፋት ባለው ፍላጎትና ባደረሰው ጥቃት ቀድሞ በመጠለያዎች ከሚገኙ ዜጎች በተጨማሪ በቅርቡ ከ550,000 በላይ ዜጎቻችን ከቤት ንብረታቸው መፈናቀላቸውን ሚኒስቴሩ ገልጿል ።

መስከረም 4 ቀን፣ 2014 የሰላም ሚኒስትሯ ወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚል በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል የሰብዓዊ እርዳታን በማስተባበር እና በማዳረስ ላይ የተሰማሩ የተባበሩት መንግስታት እና ሌሎች አለም ዓቀፍ ድርጅቶች ተወካዮችን አነጋግረዋል።

በአማራ እና አፋር ክልሎች የተባበሩት መንግስታት እና ሌሎች አለም አቀፍ የሰብዓዊ ድርጅቶች እገዛ እጅጉን አናሳ በመሆኑ ድርጅቶቹ ድጋፋቸውን በማስፋት ሁለቱን ክልሎች የማገዝ የሞራልም የተቋቋሙበት የሰብዓዊ ስራ መመሪያም ግዴታ እንደሆነ አስገንዝበዋል።

እንደ ትግራይ ክልል ሁሉ በአማራ እና አፋር ክልሎች የሚገኙ ወገኖቻችን ጉዳት ደርሶባቸዋል፣ ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል፣ መሰረተ ልማት ወድሟል። ስለሆነም አለም ዓቀፍ ሰብዓዊ ድርጅቶች በትግራይ ክልል ለተፈጠረው የሰብዓዊ ቀውስ ያደረጉትን ጊዜ፣ ቦታ እና የጦር ቀጠና ተግዳሮቶች ያልገደቡትን ርብርብ ያህል ትኩረት ሰጥተው በአማራ እና አፋር ክልሎች ድጋፍ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው ሚኒስትሯ አሳስበዋል።

ህወሓት እርዳታ ማዳረስን ሆን ብሎ በማደናቀፍና መንገድ በመዝጋት ረሃብን እንደ ጦር መሳሪያ እየተጠቀመ መሆኑንም በግልጽ ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ማሳወቅ እንደሚገባቸውም አሳስበዋል።

ወደ ትግራይ ክልል እርዳታ ጭነው የገቡ የጭነት መኪኖች በተያዘላቸው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ያልተመለሱ በመሆኑ ኃላፊነት ወስደው ያሰማሯቸው ሰብዓዊ ድርጅቶች በአስቸኳይ ወደማዕከል መመለሳቸውን አረጋግጠው ሪፖርት እንዲያቀርቡም ጠይቀዋል።

በአሁኑ ወቅት መንግስት የተለየ ትኩረት በሚፈልጉ የሰሜን ወሎ፣ ዋግኸምራ እና ሰሜን ጎንደር አካባቢዎች ላይ የቅድሚያ ቅድሚያ በመስጠት በባህር ዳር፣ ደሴ፣ ሰሜን ጎንደር እንዲሁም በአፋር ክልል ሰመራ ላይ የአስቸኳይ ጊዜ ማስተባበሪያ ማዕከላት ተከፍተው ባለሙያዎች ተመድበው እርዳታ የማዳረስ ስራውን በተሻለ ቅንጅት ለማካሄድ የሚያስችል ሁኔታ መፈጠሩንም ተመልክቷል ።

See also  "ኢትዮጵያን የሚመስልና የሚመጥን ጠንካራ ሠራዊት እየተገነባ ነው" ጄ.ል ጌታቸው ጉዲና

በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ እና በብሄራዊ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ጥረት ቀደም ሲል ያልነበሩ ውስን የሰብዓዊ ድርጅቶች ወደ ክልሉ ገብተው ስርጭት የጀመሩ ቢሆንም በቂ ያለመሆኑ ተገምግሟል። በተወሰኑ የሰሜን ወሎ ወረዳዎችም እርዳታ ማድረስ ጀምረዋል። በደቡብ ወሎ ከሰሜን ወሎ ለተፈናቀሉ እንዲሁም በዋግኸምራ ዞን ቀደም ሲል ነጻ በሆኑ አካባቢዎች ላይ በተወሰነ ደረጃ ስርጭት ተጀምሮ የነበረ ሲሆን ከዋግ ኸምራ ዞን ተፈናቅለው የተለያዩ ጣቢያዎች ላይ ለሚገኙ ወገኖቻችንም የዕለት ደራሽ እርዳታ እየተሰራጨ መሆኑ ሚኒስቴሩ አስታውቋል ።

የአጋር ድርጅቶቹ ተወካዮች የተነሱት ስጋቶች ትክክለኛ በመሆናቸው በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል ወጥ የሆነና የተቀናጀ የሰብዓዊ ድጋፍ ለማድረግ በአስቸኳይ የጋራ እቅድ አውጥተው በክልሎቹ ከሚንቀሳቀሱ የፌደራል እና የክልል ማዕከላት ጋር በትብብር እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።

ሚኒስትሯ ሁሉም የሰብዓዊ አካላት ያላቸውን አቅም ሁሉ አሟጠው ተጠቅመው ከመንግስት ጎን በመቆም ጉዳት የደረሰባቸውንና ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ዜጎችን ለመታደግ ከመቼውም በበለጠ ተቀናጅቶ መረባረብ እንደሚያስፈልግ አጽንኦት ሰጥተው ማሳሰባቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

EBC News

Leave a Reply