Site icon ETHIO12.COM

የደ.ዕዝ ወታደራዊ ፍ/ቤት የዕዙ የሰራዊት አባላት ሆነው ለአሸባሪው የህወሓት ቡድን ሲሰሩ በነበሩ የሰራዊት አባላት ላይ የጥፋተኝነት ውሳኔ ሰጠ


የሰራዊት አባላቱ ለህገ-መንግስቱና ለሃገራቸው የገቡትን ቃል ኪዳን ወደጎን በመተው የሰራዊቱን አጠቃላይ እንቅስቃሴዎች አደጋ ላይ የሚጥሉና የትግራይ ልዩ ሃይልን የሚያጠናክሩ ተግባራትን ሲያከናውኑ መቆየታቸው በችሎቱ ተነስቷል፡፡

በተለይም የሰራዊቱን ልዩ ልዩ ምስጢራዊ ሰነዶች ለትግራይ ልዩ ሃይል አሳልፈው በመስጠት፣ የሰራዊቱን ልዩ ልዩ ትጥቆች የሚጠበቅባቸውን አገልግሎት እንዳይሰጡ ምስጢራዊ ቡድን በማደራጀትና መሳሪያዎቹን በማበላሸት ስራ ላይ ተጠምደው እንደነበር በችሎቱ ተገልጿል፡፡

በዚህ የተከሳሾች መዝገብ ስር፡-

  1. ለግዳጅ የተዘጋጁ መሳርያዎች የሚጠበቅባቸውን አገልግሎት እንዳይሰጡ በማድረግ፣
  2. ሰራዊቱ ሽብርተኛውን የሸኔ አባላትን ለመደምሰስ በሚንቀሳቀስበት ዕለት ቀድሞ መረጃ
    በመስጠትና ተልዕኮው ተፈላጊውን ውጤት እንዳያገኝ በማድረግ፣
  3. የሰራዊቱን ምስጢራዊ ክንዋኔዎች ለሽብርተኛው አካል እንዲደርስ በማድረግ፣
  4. በበላይ አካል የሚሰጣቸውን ተልዕኮ ወደጎን በመተው ከሽብርተኛው አካል
    የሚሰጣቸውን ድብቅ አጀንዳ መፈፀም በሚያስችላቸው አካሄድ ላይ ብቻ ማተኮር፣
  5. የትግራይ ልዩ ሃይሎች “የብልፅግና ወታደሮችን” ድል እያደረጉ ነው የሚል ሽብር
    በመንዛት በሰራዊቱ ውስጥ የሚገኙ የትግራይ ተወላጅ የሰራዊት አባላትን በማነሳሳት
    የቆሙለትን አላማ ወደጎን በመተው የወንጀል ድርጊታቸው አካል እንዲሆኑ በማድረግ፣
  6. ከቆሙለት ሃገራዊ አላማ ይልቅ ለክልል ልዩ ሃይል የሚጠቅሙ ተግባራትን ማከናዎን
    የሚሉ ክሶች ተዘርዝረዋል።

ተከሳሽ የሰራዊት አባላትም የቀረቡላቸውን ክሶች ክደው የተከራከሩ ሲሆን የዕዙ ፍትህ ቡድን የሰነድና የሰው ማስረጃዎችን አቅርቦ ተከራክሯል፡፡

የተከሳሾች ጠበቃ በበኩሉ ተከሳሽ የሰራዊት አባላቱ ከዚህ ቀደም ሃገራቸውንና ህዝባችውን ለማገልገል በርካታ አወንታዊ ተግባራትን ያከናወኑ መሆናቸውንና የቤተሰብ አስተዳዳሪ መሆናቸውን ከግምት ውስጥ በማስገባት ፍርድ ቤቱ የቅጣት ማቅለያ እንዲያደርግላቸው ጠይቋል፡፡

ግራ ቀኙን ያዳመጠው ወታደራዊ ፍርድ ቤትም ተከሳሾቹ በቀረቡባቸው ክሶች ላይ በትክክል መከላከል ያልቻሉ በመሆኑ ጥፋተኛ ናቸው ሲል በመወሰን የቅጣት ውሳኔ ለመስጠት ተለዋጭ ቀጠሮ በመስጠት ችሎቱን አጠናቋል ሲል የደቡብ ዕዝ ኢንዶክትሪኔሽንና ህዝብ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት ያደረሰን መረጃ ያመለክታል፡፡

EBC

Exit mobile version