Site icon ETHIO12.COM

ዴልታ በተባለው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት በሆስፒታል የሚታከሙ ሰዎች መጠን በእጥፍ እንዲጨምር አድርጓል–ጥናት

ዴልታ በተባለው አዲሱ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት በሆስፒታል የሚታከሙ ሰዎች መጠን በእጥፍ እንዲጨምር ማድረጉን በእንግሊዝ እና በስኮትላንድ ተመራማሪዎች የተሰሩ ጥናቶች አመልክተዋል፡፡

እነኝህ የጥናት ውጤቶች ይፋ እንዳደረጉት ከሆነ ቀደም ሲል ተከስቶ በነበረው አልፋ በተባለው የቫይረሱ ዝርያ ምክንያት በሆስፒታል ክትትል ሲደረግላቸው ከነበሩት ታማሚዎች ይልቅ በዴልታ ዝርያ የተያዙት በእጥፍ እንደሚበልጡ አመላክተዋል፡፡

ቀደም ሲል በስኮትላንድ ተመራማሪዎች ይፋ የተደረገው የምርምር ውጤት እንደሚያመላክተው ቀደም ሲል ከነበረው የአልፋ ዝርያ የመተላለፍ መጠን አዲሱ የዴልታ ዝርያ የመተላለፍ መጠን እስከ 50 በመቶ እንደሚደርስ አስታውቀው እንደነበር ይታወሳል፡፡

እንደ የጥናት ግኝት ከሆነ ሙሉ የቫይረሱን መከላከያ ክትባት የወሰዱ ሰዎች ሁለቱንም የቫይረሱ ዝርያዎች የመከላከል አቅማቸው ከማደጉ በተጨማሪ በሆስፒታል ተኝቶ ህክምና ምጣኔም እንዲቀንስ አድርጓል ብለዋል፡፡

በዚህ የሚቀጥል ከሆነ አልጋ ይዘው የሚታከሙ ብቻ ሳይሆን በወረርሽኙ ምክንያት ህይወታቸውን የሚያጡ ሰዎች ቁጥርም እንደሚጨምር ቅድመ-ግምት ማስቀመጣቸውን አልጄዚራ ዘግቧል፡፡

ክትባቱ የዴልታ ዝርያን እንደሚከላከል አረጋግጠናል የሚሉት በእንግሊዝ የህብረተሰብ ጤና ተቋም ብሔራዊ የተላላፊ በሽታዎች አገልግሎት ከፍተኛ ባለሙያ እና የጥናት ቡድኑ አማካሪ የሆኑት ጋቪን ዳብሬራ በዚህም መሰረት እስካሁን ሁለቱንም ዙር ክትባት ያልወሰዱ ሰዎች በተቻለ መጠን ክትባቶቹን እንዲወስዱ ምክረ-ሀሳባቸውን ለግሰዋል፡፡

የኢፌዴሪ ጤና ሚኒስቴር አዲሱ የዴልታ ቫይረስ ሀገር ውስጥ መግባት አለምጋባቱን ለማረጋገጥ ጥናት እየተደረገ እንደሆነ ጠቅሶ፤ ከተወሰኑ ጊዜያት ወዲህ በቫይረሱ የሚያዙ እና በሆስፒታል ክትትል የሚደረግላቸው ሰዎች እና በቫይረሱ ምክንያት ህይወታቸውን የሚያጡ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ በመምጣቱ አዳዲስ ህጎችንና መመሪያዎችን አውጥቶ ተግባራዊ ማድረጉ ይታወሳል፡፡

ENA

Exit mobile version