ETHIO12.COM

ከ186 ሺህ በላይ ሀሰተኛ የአሜሪካ ዶላር ሳይሰራጭ እጅከፍንጅ ተያዘ፤ ለኦነግ ሲላክ የነበረ የጦር ቁሳቁስ በቁጥጥር ስር ዋለ

በሀዋሳ ከተማ ከ186 ሺህ በላይ ሀሰተኛ የአሜሪካ ዶላር በማተም ለማዘዋወር ሲያዘጋጁ የነበሩ ሁለት ተጠርጣሪዎችን ዛሬ ረፋድ ላይ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ፖሊስ አስታወቀ።

የሲዳማ ክልል ፖሊስ ኮሚሽነር አበራ አሬራ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ተጠርጣሪዎቹ እጅ ከፍንጅ የተያዙት ከህብረተሰቡ በደረሰ ጥቆማ መሰረት በተካሄደ አሰሳ ነው።በሃዋሳ ከተማ በጥቁር ገበያ ለማዘዋወር ታቅዶ የነበረና የህትመት ሂደቱ ያላለቀ ከ186 ሺህ በላይ ሀሰተኛ የአሜሪካ ዶላር መገኘቱን አስታውቀዋል።

በዚህ የወንጀል ድርጊት የተጠረጠሩ ሁለት ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ውለው ጉዳያቸውን ለማጣራት ምርመራ እየተደረገባቸው እንደሚገኝ ኮሚሽነሩ ተናግረዋል።ሌሎች ተጠርጣሪዎችንም በቁጥጥር ስር ለማዋል ክትትል እየተደረገ እንደሆነ ጠቅሰዋል።

በቁጥጥር ሥር የዋሉት ግለሰቦች በሆቴል ውስጥ የሚያትሙትን ሀሰተኛ ዶላር የሚገዛ ሰው ሲያፈላልጉ እንደነበር ያመለከቱት ኮሚሽነሩ፤ የህብረተሰቡና የሆቴል ባለቤቶቹ ጥቆማ ለግለሰቦቹ መያዝ አስተዋጽኦ ማድረጉን ተናግረዋል።ወንጀልን ለመከላከል ህብረተሰቡ ለፖሊስ እየሰጠ ያለውን መረጃና ጥቆማ አጠናክሮ እንዲቀጥልም ኮሚሽነሩ መልዕክት አስተላልፈዋል ሲል የዘገበው ኢቢሲ ነው።

በተመሳሳይ የወንጀል ዜና በዛሬው እለት ከሰንበቴ ወደ ጋቸኒ ሊዘዋወር የነበረ ጩቤና የኦነግ ሸኔ ባንድራ ያለበት የጥይት ካርታ መያዣና ሌሎች ህገወጥ እቃዎች በሸዋሮቢት ከተማ አስተዳደር በቁጥጥር ስር መዋሉ ተገለጸ፡፡ እንደ አስተዳደሩ ፖሊስ ጽቤት ገለጻ ከሆነ ዛሬ ከጠዋቱ 3 ሰአት ተኩል አካባቢ 20 ህገ ወጥ ጩቤ 6 የኦነግ ሸኔ ባንድራ ያለበት የጥይት መያዣ ካርታ ፣ 5 እንግብ 5 የትጥቅ መያዣ ቀበቶ እንዲሁም አንጋዳ ከሰንበቴ ተነስቶ አፋር ክልል ጋቸኒ ሊዘዋወር ሲል በ08 ቀበሌ ፖሊስ ኦፊሰርና ማህበረሰብ በቁጥጥር ስር መዋሉ ታውቋል፡፡

ዝውውሩ ለማካሄድ ወደ ደብረ ብርሀን የሚያስኬደውን ኬላ በባጃጅ ማለፍ እንደ ቴክኒክ ተጠቅመው እንደነበርና ሲያዘዋውር የነበረው ግለሰብም በቁጥጥር ስር ውሎ ምርመራ እየተደረገበት መሆኑ ጽ/ቤቱ አያይዞ ገልጿል፡፡በህገ ወጥ መንገድ አካባቢው የሁከት ቀጠና ለማድረግ የሚንቀሳቀሱ አካላት ማስቆም ወይም መግታት የተወሰነ አካል ድርሻ ብቻ አድርገን ባለመውሰድ ሁላችንም የድርሻችን ልንወጣ ይገባል።

በተለይ የባጃጅ አገልግሎት የምትሰጡ አሽከርካሪዎች የሸዋሮቢትንና የአካባቢዋን ሰላም ለማምጣት የናንተም ድርሻ ከመቼውን ጊዜ በላይ አሁን ያስፈልገናል እናም አገልግሎት የምትሰጡትን አካል በደንም ማወቅና መለየት ያስፈልጋል፤ አጠራጣሪ ነገርም ስትመለከቱ ለሚመለከተው የጸጥታ አካል ጥቆማ ማድረግ ይገባል እንላለን ፡፡የሸዋሮቢት ከንቲባ ፅህፈት ቤት።

Exit mobile version