Site icon ETHIO12.COM

የአሸባሪው ህወሃት አመራሮች ከተደበቁበት የቀበሮ ጉድጓድ አድኖ በመያዝ ገድል የፈጸሙት ሻለቃ ወርቅነህ መስዋዕት ቢሆኑም ስራቸው ህያው ሆኖ ይኖራል

ስብሃት ነጋን ጨምሮ የአሸባሪው ህወሃት አመራሮች ከተደበቁበት የቀበሮ ጉድጓድ አድኖ መያዝን ጨምሮ በርካታ ገድሎችን የፈጸሙት ሻለቃ ወርቅነህ ጣዲሶ መስዋዕት ቢሆኑም ስራቸው ህያው ሆኖ እንደሚኖር ተገለጸ።

ትውልዳቸውና እድገታቸው አርባ ምንጭ ከተማ የሆኑት ሻለቃ ወርቅነህ የአገር መከላከያ ሰራዊትን ከተቀላቀሉበት ከ1991 ዓ.ም ጀምሮ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ ለ23 ዓመታት እናት አገራቸውን በትጋት አገልግለዋል።

የሻለቃ ወርቅነህ ወላጅ አባት አቶ ጣዲሶ ጮሎ ለኢዜአ እንዳሉት፤ ልጃቸው ከወጣትነት ዕድሜያቸው ጀምረው ለአገር የሰሩ፣ የኖሩና በጀግንነት የተዋደቁ ናቸው።

ከሻለቃ ወርቅነህ ጋር ከአሥር ዓመት በላይ አብረው በግዳጅ የቆዩት ጓደኛቸው አስር አለቃ ታምራት ዮሐንስ በበኩላቸው “ወርቅነህ ጀግና፣ ደፋርና ወደ ኋላ የማይል ጠንካራ ወታደር ነበረ” ሲሉ ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል።

ከጦር ሜዳ ጀግንነት ባለፈ ሰራዊት በማሰልጠን ረገድ ክህሎት ያላቸው ሻለቃ ወርቅነህ፤ ከአገር አልፈው በሩዋንዳ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ጂቡቲና ሶማሌላንድ ሠራዊትን በማሠልጠን አሻራውን አኑረዋል።

በሰላም ማስከበር ተልዕኮም በላይቤሪያና ደቡብ ሱዳን ተሳትፎ ያላቸው እኚህ ጀግና ሰራዊቱ ውስጥ በጥበብ ስራዎቻቸው ሰራዊቱ እንደሚያውቃቸው አስር አለቃ ታምራት ተናግረዋል።

የሻለቃ ወርቅነህ ታናሽ ወንድም ሳምሶን ጣዲሶ ወንድማቸው የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጅ እንደነበሩ አስታውሰው፤ በተለይም የአሸባሪውን ህወሃት ቀንደኛ አመራሮችን ከተደበቁበት ጉድጓድ መያዛቸውን አስታውሰዋል።

የወንድማቸው ስራ ታሪክ የሚያወሳው ህያው ተግባር መሆኑንም ገልጸው፤ ቤተሰቡ በሻለቃ ወርቅነህ ገድል ኩራት እንደሚሰማው ገልጸዋል።

ከአራት ዓመት በፊት በልብ ህመም ምክንያት እናቱን አሁን ደግሞ በአሸባሪው ህወሃት ድርጊት አባቱን ያጣው የሻለቃ ወርቅነህ ህጻን ልጅ ያፌት ወርቅነህ “አገርና ጀግና ወዳዶች አለውለህ አይዞህ እያሉት ነው” ያሉት አቶ ሳምሶን፤ “ጠላትን ለመደምሰስ በዱር በገደሉ የተዋደቀው ጀግና ልጅ ለችግር እንዳይጋለጥ ኢትዮጵያዊያን እገዛ ማድረግ ጀምረዋል” ብለዋል።

“ወንድሜ ለአገር ክብር የከፈለው መስዋዕትነት አንገቴን ቀና እድርጌ እንድንሄድ አድርጎኛል” የሚሉት የሻለቃ ወርቅነህ ጣዲሶ እህት ወይዘሮ ብርሀንነሽ ጣዲሶ፤ ወንድማቸው በትምህርታቸው እንዲበረቱ ያግዟቸው እንደነበር ተናግረዋል።

የጀግናው ወንድማቸውን ብድር ለመመለስ ልጁን አስተምረው ለቁምነገር ለማብቃት መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።

ወይዘሮ ብርሀንነሽ እንዳሉት የሀዋሳ ዩኒየን አካዳሚ ለሀገር ክብር በጀግንነት ለተሰዋው የወንድማቸው ልጅ እስከ 12ኛ ክፍል ነጻ የትምህርት ዕድል መስጠቱን ተናግረዋል።

“አገር ተከብራ እንድትቆይ የህይወት መስዋዕትነት እየከፈሉ ለሚገኙ የሀገር መከላከያ ሠራዊት አባላት ያለንን ድጋፍ የምንገልጸው በተግባር መሆን አለበት” ያሉት ደግሞ የሀዋሳ ዩኒየን አካዳሚ ሥራ አስኪያጅ አቶ ኢዮብ ጽጌ ናቸው።

ትምህርት ቤታቸው በ2014 የትምህርት ዘመን ባለው ክፍት ቦታ የመከላከያ ሠራዊት ልጆችን በመቀበል በነጻ ለማስተማር ዝግጅት እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

ከዚህ በተጨማሪ ያፌትን ወደ ትምህርት ቤት ወስዶ ለሚመልሰው ታክሲ የኮንትራት ክፍያ ትምህርት ቤቱ እንደሚሸፍን አቶ ኢዮብ ገልጸዋል።

የሀገር መከላከያ ሠራዊት አባላት ልጆች በግል ትምህርት ቤቶች ነጻ የትምህርት ዕድል እንዲያገኙ በማድረግ አጋርነትን ለማሳየት እየሰራ ያለው ጋዜጠኛ ባሪያስ በዛብህ በበኩሉ የሻለቃ ወርቅነህ ልጅ የትምህርት ዕድል እንዲያገኝ የበኩሉን እገዛ ማድረጉን ገልጿል።

በሃዋሳ ከተማ በሚገኙ የግል ትምህርት ቤቶች በርካታ የመከላከያ ሠራዊት አባላት ልጆች ነጻ የትምህርት ዕድል እንዲያገኙ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን ተናግሯል።

ወጣቱ ትውልድ ለአገር ክብር ዋጋ መክፈልን ከሻለቃ ወርቅነህ መማር እንዳለበት የገለጸው ደግሞ የአርባ ምንጭ ከተማ ነዋሪ ወጣት ኤሊያስ ዓለሙ ነው።

“የአገር መከላከያ ሠራዊት አባላት ምትክ የሌለው ህይወታቸውን ለአገርና ለህዝብ ደህንነት ሲሉ ይገብራሉ፤ እኛም በምትኩ ለእነሱ መቆም አለብን” ብሏል።(ኢዜአ)

Exit mobile version