Site icon ETHIO12.COM

በአዲስ አበባ ሕገ-ወጥነትን ለሚጠቁሙ መረጃ አቅራቢዎች ስለሚሰጥ ማበረታቻ የወጣ ደንብ

ሕገወጥነትን በዘላቂነት ለመፍታት ሕገወጦችን ለሚያጋልጡ ነዋሪዎች የማበረታቻ ሥርዓት በመዘርጋት ችግሩን መከላከል አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ “ሕገ-ወጥነትን ለሚጠቁሙ መረጃ አቅራቢዎች ስለሚሰጥ ማበረታቻ” ደንብ አውጥቷል፡፡

በመደበኛ ሕጎች የሚፈጸሙት ተግባራት እንደተጠበቁ ሆኖ ይህ ደንብ በቅርብ ጊዜያት እየተንሰራፉ የመጡ በመንግስትና በሕዝብ ንብረት ላይ የሚሰሩ እና ነዋሪውን የሚያማርሩ ሕገወጥ ተግባራት ላይ እንዲያተኩር ተደርጓል፡፡

ደንቡ ከለያቸው ዋና ዋና ሕገ-ወጥ ተግባራት ውስጥ፡-
• የመሬት ወረራ፤ በመሬት ባንክ ተይዘው የነበሩ ይዞታዎችን ሕገወጥ በሆነ መንገድ የይዞታ ማረጋገጫ ምስክር ወረቀት እንዲወጣባቸው ማድረግ፤
• ሕገ-ወጥ ግንባታ፤
• የአርሶ አደር ይዞታዎችን በህገ ወጥ መንገድ ለማይገባው ሰው መብት እንዲፈጠር ማድረግ፤
• አላግባብ የመንግስት ቤቶችን፣ ሼዶችን፣ አረንጓዴ ቦታዎች እና ሌሎች ማንኛውም የመንግስት ይዞታዎችን ወደ ግለሰብ ማዞር፤
• በመሬት፣ በመሬት ነክ እና በማናቸውም የከተማው አስተዳደር አካላት ላይ የተመደበ ኃላፊ ወይም ሠራተኛ ተገቢ ያልሆነ ጥቅም ለራሱ ወይም ለሌላ ሰው ለማስገኘት በማሰብ የመንግስት አግልግሎቶችን በገንዘብ መሸጥ፣ ጉቦ እና መማለጃ መቀበል፤
• በግልጽ ባለቤት ሳይኖራቸው በህገ-ወጥ መንገድ ተገንብተው ያሉ ሕንጻዎች እና ታጥረው የተያዙ ባዶ ቦታዎችን ይዞ መገኘት፤
• በስም ዝውውር መክፈል የሚገባውን የአሹራ፣ የቴምብር ቀረጥ፣ እና ሌሎች የአገልግሎት ክፍያዎች ህጋዊ ባልሆነ መንገድ ቀንሶ ማስከፈል፤
• መሠረታዊ የንግድ ዕቃዎችን በመደበኛ የንግድ መስመር እንዳይሸጥ መደበቅ፣ ማገድ ወይም መያዝ፤
• ሕገ-ወጥ የጦር መሣሪያ ዝውውር፣
• በህገወጥ መንገድ የውጭ ምንዛሬ ማዘዋወር፣
• የሀገር ውስጥ እና የውጭ ገንዘቦችን በማተምና በማሰራጨት የማጭበርበር ወይም የማታለል ተግባር መፈፀም፤
• ሀሰተኛ ሰነድ በማዘጋጀት አገልግሎት መቀበልና መስጠት እና ሌሎች በወጣው ደንብ የተዘረዘሩ ናቸው፡፡

ደንቡ ጥቆማ የሚቀርብባቸው ሕገወጥ ተግባራትን ከለየ በኋላ ጥቆማው በምን ዓይንት መንገድ መቅረብ እንደሚገባው የጥቆማ ወይም የመረጃ አቀራረብ ሥርዓት በግልጽ አስቀምጧል፡፡

ከዚህም በተጨማሪም ተጨባጭ መረጃ ለሚያቀርቡ ጠቋሚዎች ወይም መረጃ አቅራቢዎች ስለሚሰጥ ማበረታቻ ምጣኔ የሚገልጹ ድንጋጌዎችን ይዟል፡፡

ማበረታቻው ተጨባጭ መረጃ ያስገኘውን ውጤት መሠረት በማድረግ በገንዘብ የሚሰጥ ይሆናል፡፡

ደንቡ ይህን ተግባር የሚያከናውን የስራ ክፍል፣ የጥቆማ ማቅረቢያ ማዕከሎች፣ በዚህ ተግባራት ላይ የሚሳተፉ ሠራተኞች፣ ኃላፊዎችና ጠቋሚዎች ስለሚኖርባቸው ኃላፊነት እና ተጠያቂነትም በዝርዝር አስቀምጧል፡፡

ጥቆማ ያለው ማንኛውም መረጃ አቅራቢ ከታች በተዘረዘሩ አማራጮች ጥቆማ ማቅረብ ይችላል፡-
• በነጻ የስልክ መስመር 9977፣
• በአካል ከንቲባ ጽ/ቤት 4ኛ ፎቅ፣
• በኢሜል acity4338@gmail.com

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር

Exit mobile version