ETHIO12.COM

“ሁለት አዋጊ ኮሎኔሎች ተመቱ” ተስፋዬ ገ/ትንሳኤ ተማረከ፤ በመተማ “ወጣቱ ጠላት አናስገባም” አለ

የአገር መከላከያ ሰራዊት፣ የአማራና ኦሮሚያ ልዩ ሃይል፣ ሚሊሻና የአካባቢው ነዋሪዎች በጥምር በማይጸብሪ ግንባር በተደጋጋሚ ኮሪዶር ለማስከፈት ጥቃት ለመስነዘር የመጣውን ሃይል ሙሉ በሙሉ እንደደመሰሱ ተገለጸ። ትህነግ ያለው ነገር የለም።

የአገር መከላከያ ሚኒስቴር በፌስ ቡክ ገጹ ይፋ እንዳደረገው ዛሬ በማይጠብሪ ግንባር ለማጥቃት የመጣው “የከሀዲው ኮ/ል ኪሮስ ገ/ኪዳን” ክፍለጦር እሱን ጨምሮ በወርቅ አምባ፣ ቡና ሜዳ እና ዝንጆሮ አፋፍ አካባቢዎች ያሰማራቸው የጥፋት መልዕክተኞቹ ተደምስሰዋል፡፡

በማይጠብሪ ግንባር ከሚመሩት አዛዦች መሀል አንዱ እንደተናገሩት ፣ ትላንት ለሊት 10 ሰዓት እና ዛሬ ረፋድ ላይ በከሀዲው ኮ/ል ኪሮስ ገ/ኪዳን የሚመራው ክ/ጦር ሙሉ በሙሉ ሲደመሰስ እሱን ጨምሮ የጁንታው አመራሮች ከሆኑት መካከል ሌ/ኮ ገ/ፃዲቅ ምሩፅ መደምሰሱን አረጋግጠዋል ፡፡

በተደረጉት አውደ ውጊያዎች አሸባሪው የህውሓት ቡድን ሲጠቀምበት የነበረው ከ27 ሺ በላይ የተለያዩ ጥይቶች ፣ ዲሽቃ፣ ብሬን ፣ ስናይፐር፣ መገናኛ ሬድዮ እንዲሁም ህዝብን መደናገሪያ ሊጠቀምበት የነበረውን የሀሰት የአማራ ክልል ማህተም መማረክ ተችሏል ብለዋል፡፡

አዛዥ እንደገለፁት ፣ ይህ ድል በምዕራብ ዕዝ የሠራዊት አባላት፣ በአማራ ልዩ ኃይል እና ሚሊሺያ እንዲሁም በኦሮሚያ ልዩ ኃይል በጋራ የተገኘ ድል ነው ፡፡ በአካባቢው የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች ከሠራዊቱ ጎን በመሆን አሁን በግንባር ተሰልፈው የሚጠበቅባቸውን እየተወጡ እንደሚገኙ አመልክተዋል ።

በሌላ ዜና

ዛሬ “ሰበር” ዜና የሆነው የሌትናል ኮኔሬል ተስፋዬ ገ/ትንሳኤ መማረክ ነው። ኮሎኔሉ የትህነግን ዓላማ በመቀበል በቤኒሻንጉል ክልል በኩል ሃይል ሲያንቀሳቀስ የነበረና አካባቢውን የጦር ቀጣና እንዲያደርጉ የቤት ስራ ከተሰታቸው የሚታወቁ መኮንኖች መካከል አንዱ እንደሆነ ተመልክቷል።

በሌላ ዜና የመተማ ወጣቶች ” ጠላትን አናስገባም” ሲል በንድነት ነቅቶ እንደሚጠብቅ አስታውቋል

ድንበር ተሻግሮ ለመግባት የሚሞክር ማንኛውንም ቡድን ለመደምሰስ መዘጋጀታቸውን በምዕራብ ጎንደር ዞን የመተማ ዮሐንስ ከተማ አስተዳደር ወጣቶች ተናገሩ። መተማ፡ ነሐሴ 28/2013 ዓ.ም (አሚኮ)

የአሸባሪውን የትህነግ ወራሪ ቡድን የጥፋት ተልዕኮ ለመፈጸም የሚንቀሳቀሱ የውስጥና የውጭ ጠላቶችን በቁጥጥር ስር ለማዋልና ለመደምሰስ ወጣቱ ግንባር ከመዝመት ባሻገር አካባቢውን በንቃት እየጠበቀ ይገኛል። የመተማ ዮሐንስ ከተማ አስተዳደር ወጣቶችም ከተማው የሱዳን አዋሳኝ እንደመሆኑ መጠን የውስጥና የውጭ ጠላት ድንበር ተሻግሮ እንዳይገባና የጥፋት ተልኮውን እንዳይፈጽም በተጠንቀቅ ላይ ናቸው።

ወጣቶቹ ወታደራዊ ስልጠናውን በመውሰድ የትኛውንም ጠላት ለመደምሰስ በሚያስችል ቁመና ላይ መሆናቸውንም ተናግረዋል።የጠላት መግቢያ በር ነው ባሉት የከተማው አካባቢ ኬላ በመዘርጋት ጥበቃና ፍተሻ ሲያደርጉ ያገኘናቸው ወጣት ግርማቸው መሰረትና ጓደኞቹ አካባቢያቸውን በንቃት እየጠበቁ እንደሆነ ተናግረዋል። በማይካድራ ንጹሃንን በግፍ ጨፍጭፎ ወደ ሱዳን የፈረጠጠው የሳምሪ ገዳይ ቡድን የትና ምን እየሠራ እንደሆነ በቅርብ ርቀት እየተከታተልነው ነው፤ ይህ ቡድን ኬላ ሰብሮ የተለመደ ጥፋቱን የሚፈጽምበት ሳይሆን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የሚደመሰስበት ዕድል እንደሚጠብቀው ነው ወጣቶቹ የገለጹት።

የከተማውን ወጣቶች በተደራጀ መልኩ ከጸጥታ ኃይሉ ጋር በማቀናጀት አካባቢያቸውን እየጠበቁ ነው ያሉት የመተማ ዮሐንስ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ሐብቴ አዲሱ ሰርጎ ገቦችን በመያዝ ለሚመለከተው አካል እያስረከቡ ነው ብለዋል።

በከተማዋ ጠላት አራት ጊዜ የጥቃት ሙከራ አድርጎ ነበር ያሉት የመተማ ዮሐንስ ከተማ አስተዳደር ሰላምና ደኀንነት ጽሕፈት ቤት ኅላፊ አቶ ጌጡ ዓለሜ ሰልጣኝ ወጣቶችን ከጸጥታ ኃይሉ ጋር በማቀናጀት የጠላት መውጫ እና መግቢያ በሮችን በመጠበቅ ሰርጎ ለመግባት የሚሞክር የጠላት ቡድንን ለመደምሰስ በሚያስችል አቋም ላይ እንገኛለን ብለዋል። ዘጋቢ:— ቴዎድሮስ ደሴ -ከመተማ ዮሐንስ

የመተማ ነዋሪዎች – ፎቶ አሚኮ
Exit mobile version