Site icon ETHIO12.COM

ፍላቂት ከተማ ነፃ ሆናለች – “ወራሪው እንዳይወጣ የመቄት ወረዳ መሪዎች ቁልፍ ቦታን እንዲይዙ”

ደብረ ዘቢጥ

ወደ ኋላ እየሸሸ የሚገኘው የአሸባሪው የትህነግ ቡድን ባለበት እንዲቀበር የመቄት ወረዳ መሪዎች ቁልፍ ቦታን በመያዝ ሕዝቡን እንዲያንቀሳቅሱ ጥሪ ቀረበ።

በሰሜን ወሎ ዞን መቄት ወረዳ የምትገኘው የፍላቂት ከተማ በሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ በአማራ ልዩ ኀይል፣ ሚሊሻ፣ ፋኖ እና በአካባቢው ኅብረተሰብ ከአሸባሪው ቡድን ነፃ ሆናለች፤ አከርካሪው የተመታው የሽብር ቡድኑ ፍላቂትን ለቅቆ ወደኋላ እየፈረጠጠ መሆኑን የግንባር አመራሮች ተናግረዋል።

የሽብር ቡድኑ በደረሰበት ከባድ ኪሳራ ሞትና ቁስለኛ ከመሆን የተረፈው ፍላቂትን አልፎ እያፈገፈገ መሆኑን የግንባር መሪዎቹ ለጋዜጠኞች ገለፃ አድርገዋል። አሁን ላይ የተበታተነዉን የጠላት ቡድን የወገን ኀይል እየለቀመው እንደሆነም አስረድተዋል።

ጠላት ከፍተኛ ኪሳራ እንደደረሰበት የተናገሩት የጦር መሪዎቹ አሸባሪ ቡድኑ በርካታ የትግራይ ወጣቶችን አስጨርሷል ነው ያሉት። “የትግራይ ሕዝብ ልጆቹ የት እንደገቡ መጠየቅ አለበት፤ አሸባሪው ቡድን ወደፊት የትግራይ ሕዝብ ኢትዮጵያዊ ነኝ ብሎ እንዳያስብ እያደረገ ነው” ብለዋል።

የጠላት በርካታ የጦር መሳሪያና ተሽከርካሪዎች መውደማቸውንም መሪዎቹ ጠቅሰዋል።

የሰላማዊ ሰዎች ሕይወትን ከማጥፋት ጀምሮ አሸባሪው ቡድን ዘርፎትና አውድሞት ለሄደው የሕዝብ ሀብት ባለዕዳ እንደሚሆንም የጦር መሪዎቹ ተናግረዋል።

ቡድኑ የአረመኔነቱን ጥግ ለማሳየት በተደመሰሰባቸው የጦር ግንባሮች በተደጋጋሚ የራሱን የጦር መሪዎች አንገት መቁረጡን መመልከታቸውን ተናግረዋል። ይህ ደግሞ ከጦርነት ሳይንስ ውጪ የሆነና የጦር ወንጀል ነው ብለዋል።

አሸባሪው ቡድን ከምድረ ገጽ እስኪጠፋ ድረስ የጋለው የሕዝብ ትግል ተጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት። ሕዝቡ ከድጋፍም በላይ ግንባር ላይ በመገኘት ሕይወቱን እየሰጠ ስለመሆኑም ተናግረዋል። ድሉ የተገኘው በሁሉም ተግባር የሕዝብ ድጋፍ በመኖሩ እንደሆነ ነው ያስረዱት።

የጦር መሪዎቹ የቡድኑ ስብስብ ዓላማ የሌለው በመሆኑ የትግራይ ሕዝብ የወራሪዉን ቡድን ጥፋት ማስቆም አለበት ብለዋል። አሸባሪው ቡድን የትግራይን ሕዝብ አስጨርሼ አሸናፊ እሆናለው ብሎ ማሰቡ እብደት በመሆኑ ሕዝቡ በዚህ ሂደት ተጎጂው ማን እንደሆነ መለየት አለበት ነው ያሉት።

ደብረ ዘቢጥ በተደረገው ትግል ጠላት ከፍተኛ ሰብዓዊና ቁሳዊ ኪሳራ እንደደረሰበትም የደቡብ ጎንደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ ቀለመወርቅ ምሕረቴ ተናግረዋል።

ጠላትን ከምድረገጽ ለማጥፋት ሁሉም ኢትዮጵያዊ ርብርብ ማድረጉን መቀጠል አለበት ያሉት ዋና አስተዳዳሪው የመቄት ወረዳ መሪዎች ቁልፍ ቦታን እንዲይዙና ሕዝቡን እንዲያንቀሳቅሱ ዋና አስተዳዳሪው ጥሪ አቅርበዋል።

ደብረ ዘቢጥ አካባቢ ጠላት የቆየበት ቦታ በመሆኑ ከሁሉም አካባቢ በላይ ኅብረተሰቡ ተጎድቷል፣ በመሆኑም ለአካባቢው የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ ይቀጥላልም ነው ያሉት።

አሸባሪው እና ወራሪው የትህነግ ቡድን በደብረ ዘቢጥ አካባቢ ከፍተኛ ሽንፈት ከደረሰበት በኋላ የአካባቢው ነዋሪዎች የተለመደውን ሠላማዊ ኑሮአቸውን ቀጥለዋል።

የአሚኮ የጋዜጠኞች ቡድንም ወደ ደብረ ዘቢጥ ከተማ በደረሰበት ወቅት በሽብር ቡድኑ ላይ የደረሰውን በርካታ ሰብዓዊና ቁሳዊ ኪሳራ ተመልክቷል።

ዘጋቢ:- ቡሩክ ተሾመ – ከደብረዘቢጥ (አሚኮ) ፎቶ አሚኮ

Exit mobile version