Site icon ETHIO12.COM

የምዕራብ ዕዝ ዋና አዛዥ ሜ/ጀ መሠለ መሠረት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት

የምዕራብ ዕዝ ዋና አዛዥ ሜ/ጀ መሠለ መሠረት
የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት

በውጭም በአገር ውስጥም የምትገኙ ጀግናው የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት አባላትና ሲቪል ሠራተኞች መላው የኢትዮጵያ ህዝቦች እንኳን ለ2014 ዓ/ም ለዋዜማው በሰላም በጤና አደረሳችሁ!!

የተከበራችሁ የአገራችን ህዝቦች መንግስታችን በ2013 ዓ/ም ለዕዛችን እንድንፈፅመው የተሰጠን ግዳጅ አሸባሪው የህውሓት ቡድንን እና አሸባሪው የሸኔ ቡድንን እንዲሁም ተላላኪው የጉሙዝ ታጣቂዎችና የህውሓት ሴሎችን ለማጥፋት በተንቀሳቀሰንበት ቦታዎች ሁሉ የሰጡንን ተልዕኮዎች በሚገባ አሳክተነዋል፡፡

በተለይ የአሸባሪው የህውሓት ቡድን በሰሜን ዕዝ የሠራዊት አባላት ላይ የፈፀመውን ጥቃት እና ክህደት ተከትሎ ለዕዛችን የተሰጠንን ተልዕኮ በፍጥነት በመወጣት የአሸባሪውን የህውሓት ቡድንን ከፍተኛ አመራሮች ገሚሱን በመደምሰስ ገሚሱን ደግሞ ለህግ እንዲቀርቡ በማድረግ ከፍተኛ ስራ መስራት ችለናል፡፡

ከሀገራችን ሜጋ ፕሮጀክቶች መካከል አንዱ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዋነኛው ነው ፡፡ ይህ ፕሮጀክት ከማንኛውም የፀረ-ሠላም ሃይሎች የጥፋት ሠለባ እንዳይሆን በንቃት እና በትጋት እየተከታተልንን ያለ ምንም የፀጥታ ችግር የሁለተኛውን ዙር የውሀ ሙሌት በድል ማጠናቀቅ ተችሏል፡፡ የህዳሴ ግድባችን ላይ ጥቃት ለማድረስ የሚሞክሩ ካሉ ደግሞ የዕዙ የዝግጁነት ደረጃ በአስተማማኝ ቁመና ላይ ይገኛል፡፡

አሸባሪው የህውሓት ቡድን በመንግስት የተሰጠውን የተናጠል የተኩስ አቁሙን ውሳኔና ለትግራይ ህዝብ የጥሞና ጊዜ ወደ ጎን በመተው በሰሜን ጎንደር ዞን አንዳንድ አካባቢዎች ሾልኮ በመግባት ጥቃት ለማድረስ የሞከረው አርሚ አንድ በሚል የተደራጀው ኮር እና ክ/ጦሮች በትንታጎቹ የምዕራብ ዕዝ የሠራዊት አባላት ሙሉ በሙሉ ተደምስሰዋል፡፡ አሁን በተለያዩ አካባቢዎች የመሸጉትን ኃይሎች እስከ ወዳኛው ለማጥፋት በማይጠብሪ ግንባር የተሰለፉት በዕዙ ውስጥ የሚገኙ ክ/ጦሮች በድል ግስጋሴ ውስጥ ናቸው፡፡

በ2013 ዓ/ም በዕዙ የታዩ ጥንካሬዎችን በማጎልበት በማጠናከር ድክመቶችን በመቅረፍ በቀጣይ 2014 ዓ/ምም የምዕራብ ዕዝ ውጤታማ ተልዕኮዎችን እንደምንተግብር ሙሉ እምነት አለኝ ፡፡

አዲሱ የ2014 ዓ/ም ለመላው የኢትዮጵያ ህዝቦች እና ለመከላከያ ሠራዊታችን የሠላም፣ የጤና፣ የብልፅግና እና የዕድገት እንዲሆን እመኛለሁ፡፡

ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ህዝቦቿን ይባርክ ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!
አመሰግናለሁ!

ፎቶግራፍ ተሰማ ኡርጌሳ via defense Fb

Exit mobile version