Site icon ETHIO12.COM

” ታሪክ ራሱን ዝም ብሎ አይደግምም” ፕሬዚዳንት ሣሕለወርቅ

የፕሬዝዳንቷ ሙሉ መልዕክት እንደሚከተለው ይነበባል።በሀገር ውስጥ እና በውጭ ሀገር የምትገኙ ውድ ኢትዮጵያዊያን እና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን የሀገርን ዳር ድንበር እና ህልውና ለማስከበር በዱር በገደሉ ግዳጃችሁን በጀግንነት እየፈጸማችሁ ያላችሁ ውድ የመከላከያ ሠራዊት አባላትውድ ወገኖቼ፤ማንም ሊያቆመው በማይችል የተፈጥሮ ህግ ጨልሞ እንደሚነጋው፣ ደመናው ተገፎ ፀሀይ እንደምትወጣው ሁሉ 2013 ን ተሰናብተን 2014 ዓመተ ምህረትን ለመቀበል መባቻው ላይ እንገኛለን ።

እንኳን ለ 2014 ዓመተ ምህረት በሠላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን!!ያጠናቀቅነውን ዓመት መለስ ብለን ስንመለከተው ለሀገራችን ዘላቂ አንድነት ትልቅ ሚና ካላቸውና ካከናወናቸው መካከል የ6ተኛው ዙር ሀገራዊ ምርጫ በሠላማዊ መንገድ በማካሄድ ለዲሞክራሲያዊ ሥርአት ግንባታ ጥረታችን መሠረት መጣላችንና 2ኛው የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሙሌት መጠናቀቅ በዋናነት የሚጠቀሱ ናቸው።በአንጻሩ ደግሞ ሀገራችን ኢትዮጵያ በታሪኳ ከሚገባት በላይ በርካታ መከራዎችን ያላሳለፈች ይመስል በዚህ ዓመት ከባድ ፈተና ውስጥ የገባችበት ሆኖ የሚመዘገብ ዓመት ነው፡፡አገራችንን ከመፍረስ ለማዳንና ህልውናዋን ለማስከበር ባለፉት አስር ወራት ከፍተኛ ፍልሚያ ተካሂዷል። እየተካሄደም ነው፡፡

የመከላከያ ሠራዊታችንን በመደገፍ በውጊያ ላይ የተሳተፉ ሀይሎች እና ዜጎቻችን በከፈሉት ከፍተኛ መስዋትነት ሀገራችን ከከፍተኛ አደጋ ታድገዋታል።ለዚህ ላበቃችሁን ሁሉ ምስጋናዬን ለመግለጽ ቃላት ያጥረኛል። ፈጣሪን በእጅጉ ልናመሰግነው ይገባል፡፡እንደሚታወቀው በየትኛውም ሀገር በማንኛውም መለኪያ የእርስ በርስ ውጊያ ሌላውን ሳያቆስሉ፣ ሳያደሙ ከከፋም ሳይገድሉ ማሸነፍ የለምና ከፍተኛ ዋጋ ስለሚያስከፍል እጅግ አስከፊ ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም።

የመንግሥትን ሥልጣን በሀይል መፈታተን ፣ የሀገር መከላከያ ሠራዊትን ማጥቃት፣ የቆምንበትን መሠረት ለመናድ መሞከር ፣ ጦርነትን በሌሎች ክልሎች በማዛመት ከእሳት ጋር መጫወት ነውና መቃጠል ቢከሰት የሚገርም አይሆንም።በጣም የሚያሳዝነውና ልብ የሚሰብረው በዚህ 10 ወር ባስቆጠረ ጦርነት ንጹሃን ቤተሰቦች ፣ ወጣቶች ፣ ሴቶች፣ አዛውንቶች ሰለባ መሆናቸው ነው። ውድ ህይወታቸውን አጥተዋል ፣ ተፈናቅለዋል ፣ ክረምትና በጋ ተፈራርቆባቸዋል፣ ተሰደዋል፣ ትምህርት ቤቶችና የጤና ጣቢያዎች ተጎድተዋል፡ ብዙዎቹ ተፈናቃዮችን በማስተናገድ ላይ ይገኛሉ። በአጭሩ የጦርነትን አስከፊ ገጽታ በሙሉ አይተናቸዋል። ይህንን አደጋ ለመመከት ኢትዮጵያዊያን ጦር ግንባር ድረስ በመዝመት በየሙያ መስካቸው የበኩላቸውን ለመወጣት በመረባረብ ፣ ገቢ በማሰባሰብ ያበረከቱት አስተዋጽኦ ሁላችንንም ያኮራን ነው፡፡

ከሁሉም በላይ የመከላከያ ሠራዊታችን እንደወትሮው ሁሉ አገራችንን ለማዳን እየፈጸመ ያለው ጀብዱ በእጅጉ ያኮራን ነዉ፡፡ህዝባችን ላይ አሁንም እያንዣበበ ያለው የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ሌላው በ2013 ያስተናገድነው ፈተና ነው፡፡ ቫይረሱ ጠባዩን በየጊዜው በመለዋወጥ ችግሩን አወሳስቦታል። እስከዛሬ ድረስም 320,453 ዜጎች ቫይረሱ ሲገኝባቸው 287,147 አገግመዋል ። 2 726 015 ተከትበዋል፡፡ 4,857 ዜጎችን አጥተናል፡፡ ከባለሙያዎቹ የሚሰጠው መረጃ ወረርሽኙ ዳግም ማገርሸቱን ያመለክታል። ብዙዎቹ ወገኖቻችን በቫይረሱ እየተያዙ ነው። የህክምና ተቋሞቻችንም በተለይ የጽኑ ህሙማን ክፍሎች እየተጣበቡ ይገኛሉ።

አንድ ነገር ሲቆይ የመላመድ ሁኔታ መኖሩ ተፈጥሮዓዊ ቢሆንም እራሱን እየለዋወጠ የሚመጣ ባላንጣ በመሆኑ ልንመክተው የምንችለው የሚሰጡንን መመሪያዎች ሳናጎድል እና ሳንሰላች በመተግበርና በመከተብ መሆኑን ለማሳሰብ እወዳለሁ፡፡በተለይ በዓል ለማክበር ስንሰባሰብ ለቫይረሱ ስርጭት አመቺ ሁኔታን ልንፈጥር እንደምንችል አንዘንጋ። ይህንን ካላደርግን ሀላፊነታችንን በመዘንጋት ለእራሳችን ብቻ ሳይሆን ለህብረተሰቡ ጠንቅ እንደምንሆን መዘንጋት የለብንም። እንደውም ከፍተኛ ሃላፊነት አለብን።መጪው ዓመት ልዩ ትኩረት የሚሰጠው ይሆናል።በተካሄደው ምርጫ ውጤት መሰረት አዲሱ ፓርላማ ሥራውን ይጀምራል፡፡ ቀጥሎም አዲስ መንግስት ይመሰረታል። ይህም መንግስት ለሕዘባችን ቃል የገባዉን ዕቅዶቹን ተግባራዊ ማድረግ የሚጀምርበት ይሆናል።

ስለሆነም ሁላችንም ኢትዮጵያዊያን በሃገራችን ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ፣የህዝቡ መሰረታዊ ፍላጎቶች እንዲሟሉ፣ ሀገራችን በጦርነት ሳይሆን በአብሮ መኖር እና በጋራ ማደግ መቻሏን እንድታሳይ የሁላችንንም ትብብር፣ ድጋፍ፣ ብሎም በተቀናጀ ሁኔታ ያልተቋረጠ ጽኑ ተሳትፎን ይጠይቃል።ሁላችንም ኢትዮጵያዊያን ተስፋ በመሰነቅ ብቻ ሳንወሰን ለተግባራዊነቱ የበኩላችንን ድርሻ እንድንወጣና ለአዲስ ዓመት ቃል ኪዳን እንድንገባ በትህትና እጠይቃለሁ።ታሪክ ራሱን ይደግማል ሲባል እንሰማለን። ሁኔታዎችም ሲደገሙ ይታያሉ ። ታሪክ ራሱን ዝም ብሎ አይደግምም። ሰው ነው ከታሪክ ላለመማር አሻፈረኝ የሚለው። በእውነቱ ከሆነ በዚህ ዓመት ካየነው መከራ እንድንወጣና ዳግም እንዳይከሰት ለማድረግ የምንችለው ትምህርት ስንወስድበት ብቻ ነው ብዬ በጽኑ አምናለሁ፡፡

የመሳሪያ ድምጽ መሰማት ማቆሙ ብቻውን ሰላም ሰፈነ ማለት ስላልሆነ ብዙ ሥራ ይቀረናል። የተጋጨነው እርስ በርሳችን ነው፣ የቆሰለውን ማዳንም የኛ ፋንታ ነው። የፈረሰውን መልሶ መገንባት፣ መጠገን፣ ልጆቻችንን ወደ ትምህርት ቤት እንዲመለሱ፣ ሁሉም በየዘርፉ ከገበሬው እስከ ሰራተኛው ወደ ስራው እንዲመለስ ወዘተ የሚያደርግልን ሌላ የለም። የእኛው ሀላፊነት ነው።በሰላም ግንባታ በቀላሉ ሊተገበሩ የሚችሉ ፕሮጀክቶች ያስፈልጉናል። ሰላም የሚገነባ ነው። ለዚህም ሁላችንም የየራሳችን ድርሻ አለን፡፡ ለተወሰኑ የተከለለ አይደለም፡፡የእናት ሆድ ዥንጎርጉር እንዲሉ የእናት ኢትዮጵያ ልጆችም የተለያየን ነን፡፡ ልጆቻችንን ሳናዳላ እኩል በማሳደግ፤ በማስተማር፤ ሲያጠፉ በማረም፤ ሲያስፈልግ በመቅጣት…. ነገር ግን የቤተሰብን ሰንሰለት ሳንበጥስ እንደምንኖረው ሁሉ እኛም የአንድ አገር ልጆች ተቻችለን፤ ተደማምጠን፤ ተነጋግረን፤ የሃሳብ ልዩነትን እንደጸጋ ተቀብለን፤ ዘላቂ አገራዊ መግባባትን መፍጠርና ማዳበር ቀዳሚ ተግባራችን ሊሆን ይገባል፡፡ የምናካሂደዉ ትግል የሃሳብ እንጂ ደም አፋሳሽ ሊሆን አይገባም፡፡ ያንን ጎዳና የመረጠ የሚያስከትለዉን ውጤት የተቀበለ ይሆናል፡ውድ ወገኖቼ በ2013 ያየነው መደገም የለበትም ። ከመፈክር ባሻገር እንሥራበት። ብዙ ጊዜ አዲስ ዓመት እናከናውናለን ብለን ያሰብናቸውን ለመፈጸም ከራሳችን አንስቶ ቃል የምንገባበት ነው።2014ን ስንቀበል፣ትውልድ በዘረኝነት፣ በጭካኔ፣ እንዳይበከል በርትተን የምንንቀሳቀስበት፣ የተፈናቀሉትን በርካታ ወገኖቻችንን ወደ ቤታቸው የምንመልስበት፣ ካለፈው ትምህርት ተምረን ተግባራዊ የምናደርግበት፣ በሀገራችን ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ በጋራ ተወያይተን፣ ተደማምጠን፣ ተከባብረን የጋራ መግባባት ላይ የምንደርስበት፣ ኢትዮጵያን በማክበር፣ በማስከበር፣ በማሳደግ አንድነቷን ከመጠበቅ ውጭ የተወሰኑ ለያዙት አጀንዳ መጫወቻ እንዳትሆን ነቅተን የምንጠብቅበት፡ የምንከላከልበት፣ ዲሞክራሲን የምናጠናክርበት፣ ጫፍ የነካ ጥላቻና ጭካኔን ከውስጣችን የምናወጣበት እንዲሆን ለመላው ኢትዮጵያዊያን ጥሪዬን በአክብሮት ለማቅረብ እወዳለሁ።በትናንትናው ዕለት የጀግኖችን ቀን ምክንያት በማድረግ በጦር ሓይሎች ሆስፒታል በውጊያ ሜዳ ቆስላ በሕክምና ላይ የምትገኝ የሠራዊት አባል እህታችንን እያበረታኋት እያለሁ “ሳይክስ አይበድልም” በማለት ብትቆስልም ለአገር የተከፈለ መስዋዕትነት በመሆኑ ፈጣሪ ክሶኛል አለች፡፡ለቆሰሉት ምህረቱን ይስጥልን፣ የተፈናቀሉትን፣ በየጫካው፣ በየሜዳው የሚገኙትን ለቤታቸው ያብቃልን፡፡ከመደምደሜ በፊት አንድ ታዋቂ ፈላስፋ ያሉትን እጠቅሳለሁ፤ “ከማንኛውም ፈተና በኋላ ብርሃን ምን ጊዜም አለ። እጆቻችን እሾህ ወግቷቸው እየደሙ ከሆነ ጽጌረዳዋ ላይ ለመድረስ ብዙ ስላልቀረን ነው”፤ እኛም ወደዚያው እየተቃረብን ያለን ይመስላል።ነገ አዲስ ቀን ነው! የአዲሱን ዓመት ምዕራፍ በጸዳ ወረቀት ላይ ለመጻፍ እንነሳ።በያላችሁበት መልካም ዓመት ይሁንላችሁ !!ፈጣሪ አገራችንንና ሕዝቧን ይጠብቅልን፡፡አመሠግናለሁ!

Exit mobile version