Site icon ETHIO12.COM

«ቃል ማክበር ካለ የድል ብሥራት አለ» አብይ አህመድ የድል ብስራት ፍንጭ ሰጡ

” ይህ ጦርነት እስከ መስከረም አንድ መልክ ይዞ ድል የማናውጅ ከሆነ እኔ ልብስ ቀይሬ ወደ ጦር ሜዳ እዘልቃለሁ” አሉ አብይ አህመድ ከጀነራሎቻቸውና ከከፍተኛ የጦር መኮንኖቻቸው ጋር ሲመክሩ። አንዱ ደመ ግቡ ጀነራል ተነስተው በሚነድ የዕልህ ስሜት እምባቸው እየወረደ “ድሉ መስከረምን አይዘልም፤ ቃል እንገባለን” ሲሉ ሁሉም ይህን ቃለ ለማክበር ተስማሙ። የሚከፈለውን ሁሉ እንደሚከፍሉ ቃል ገቡ!! ” እጅ በአፍ የሚያስጭን ድል” ከዚያ ስብሰባ በሁዋላ ተጸነሰ። ይህንን ተንተርሰው ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ “ቃላችንን ጠብቀናል ድል አለ” ሲሉ በአዲስ ዓመት ዋዜማ ተናገሩ።

በአዲስ ዓመት ዋዜማ “የተናገሩት ከሚጠፋ የወለዱት ይጥፋ” የሚለውን የቆየ ብሂል አስቀደመው ” ቃላቸውን” እንደሚያከብሩ አመልክተዋል። ዛሬ ማለዳ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በቲውተር ገጻቸው ባጋሩት መልዕክት በአዲስ ዓመት ለኢትዮጵያዊያን ድል እንደሚያበስሩ ምልክት ነው የሰጡት።

ኢትዮጵያዊያን ” የተናገሩት ከሚጠፋ የወለዱት ይጥፋ” በሚል ማኅበረሰብ ውስጥ ማደጋቸውንና መኖራቸውን አመልክተው፣ መንግስትና ሕዝብ በቃለ ኪዳን ተሳስረው እንደሚኖሩ ጠቁመዋል። ይህን ካሉ በሁዋላ ነው ” መንግስት ቃሉን ማክበር አለበት” ሲሉ ለህዝብ የገባውን ኮንትራት መጠበቅ እንደሚገባው ያሳዩት።

“ቃል ኪዳን የዓለም ህልውና የተመሠረተበት ሥርዓት ነው። ሰው ከሰው፣ ሰው ከአካባቢው፤ አካባቢ እርስ በርሱ ተጠባብቆና ተግባብቶ የሚኖረው በቃል ኪዳን ነው” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ፣ ቃልኪዳን ያሉትን ጉዳይ ከድል ጋር አያይዘውታል። ” እንደ መንግሥትና እንደ ሕዝብ ለገባናቸው ቃል ኪዳኖች ታማኞች ከሆንን ሀገር ሰላም፣ ምቹና ባለጸጋ ትሆናለች”ሲሉ ቃል የማክበርን ውጤት አመላክተዋል።

“ድል የገቡትን ቃል በማክበር፣ ለቃል ታምኖ በመሥራትና ቃልን በተግባር በመግለጥ የሚገኝ ነው” በማለት የአዲሱን ዓመት የድል ብስራት ያመላከቱት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ፣” ቃል ማክበር ካለ የድል ብሥራት አለ” ብለዋል። “ለኢትዮጵያ የገባነውን ቃል ኪዳን አድሰንና አክብረን፣ የኢትዮጵያን ድል እናበሥራለን” ሲሉም አክለዋል።

ከፍተኛ የጦር መኮንኖችም ” ድሉ ተቃርቧል። ትህነግ ወደ ለመደው ዋሻ …” በሚል ከጦር ሜዳ ውሏቸው ላይ ሆነው ሰሞኑንን ሲናገሩ ነበር። ሌተናል ኮሎኔል ባጫ ደበሌም መከላከያ ከመከላከል ወደ ማጥቃት እንዲሸጋገር በታዘዘ ማግስት በሰጡት መግለጫ ” ቀሪውን ድል እናበስራለን፤ መልካም አዲስ ዓመት” ማለታቸው ይታወሳል።

Exit mobile version