Site icon ETHIO12.COM

ጆባይደን ለኢትዮጵያና ኤርትራ አዲስ ዓመት የመልካም ምኞት መልዕክት አስተላለፋ


“ለኢትዮጵያና ለኤርትራ ህዝብ እንዲሁም በመቶ ሺዎች የምትቆጠሩ የኢትዮጵያና የኤርትራ ውርስ ያላችሁ አሜሪካዊያንን ጨምሮ በዓለም ዙሪያ ነገ እንቁጣጣሽን ለምታከብሩ ሁሉ ጂል እና እኔ የላቀ ምኞታችንን እና መልካም አዲስ ዓመት እንመኝላችኋለን” ሲሉ የዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን በራሳቸውና በባለቤታቸው ስም ማምሻውን መልዕክት አስተላልፈዋል።

“ለእንቁጣጣሽ በዓል የፕሬዚዳንት ጆዜፍ ባይደን መልዕክት” በሚል ርዕስ በዋይት ሀውስ ቤተመንግሥት ድረ ገጽ ላይ በወጣው መልዕክታቸው “ኢትዮጵያዊያን አሜሪካዊያንና ኤርትራዊያን አሜሪካዊያን በመላ አሜሪካ ያሉ ማህበረሰቦችን በማበልጸግ በሃገራችን የየዕለት ህይወት እያንዳንዷ ገፅታ ላይ ቁልፍ ናችሁ” ብለዋል ባይደን።

“ለብዙዎቻችሁ ያለፈው ዓመት ከባድ እንደነበር አውቃለሁ” ብለዋል ፕሬዚዳንቱ። “ኮቪድ 19 ካደረሰው መጎዳትና ማጣት ጋር ኢትዮጵያ ውስጥ እየተካሄደ ያለው ግጭት ቤተሰቦቻችሁንና የምትወዷቸውን ሁሉ እየጎዳ መሆኑን አውቃለሁ” ያሉት ፕሬዚዳንት ባይደን ፣ኢትዮጵያ ውስጥ በሲቪሎች ላይ እየደረሰ ነው ያሉት ጥቃት በጥልቅ እንደሚያሳስባቸው ገልፀዋል።

አፍሪካ ቀንድ ውስጥ ያሉ ግጭቶች ሁሉ ወደ ሰላማዊ መፍትኄ እንዲያመሩ አስተዳደራቸው በመላ አካባቢው ካሉ አጋሮች ጋር የነቃ የዲፕሎማሲ ጥረት እያደረገ መሆኑንም ባይደን አስታውቀዋል።

“እንደ ኢትዮጵያና ኤርትራ የዳያስፖራ አባላት በአካባቢው ሰላምና ብልፅግና እንዲጠናከሩ ብዙዎቻችሁ በቀጥታ እያበረከታችሁ ያለውን አስተዋፅዖ እገነዘባለሁ፤ አደንቃለሁም” ብለዋል ፕሬዚዳንት ባይደን።

አሜሪካ ለአፍሪካ ቀንድ ህዝብ ጥቅልና የረዥም ጊዜ የወዳጅነት ቁርጠኛነት እንዳላት ፕሬዚዳንቱ አመልክተው፣ በየትኛውም የሕዝብ ቡድን ላይ የሚፈፀምን ኢሰብዓዊ ጥቃት መቃወማችንን እንቀጥላለን” ብለዋል።

በአካባቢው ለሰብዓዊ እርዳታ ፍላጎቶችም ምላሽና ድጋፍ መስጠታቸውን እንደሚቀጥሉ ፕሬዚዳንት ባይደን አክለው አስታውቀዋል።

“ታላቋና ኅብረ-ስብጥሯ ኢትዮጵያ አሁን የተደቀኑባትን የመከፋፈል አደጋዎች እንደምታሸንፍና በድርድር የሚደረስበትን ተኩስ ማቆም ጨምሮ እየተካሄደ ላለው ግጭት መፍትኄ እንደምታበጅ እናምናለን” ብለዋል ፕሬዚዳንት ባይደን በዚሁ የአዲስ ዓመት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክታቸው።

“ሰላምን መገንባት ቀላል አይደለም” ያሉት ባይደን ፣ይሁን እንጂ በውይይትና በሰብዕናችን ውስጥ አንድነትን በመሻት ወይም በመፈለግ ዛሬ ሊጀመር ይችላል፤ መጀመር አለበት” ሲሉ በሐሳባቸውን አጠናክረዋል።

በአማርኛ ቃላት “መልካም አዲስ ዓመት” ብለዋል ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን በዓሉን ለሚያከብሩ ሁሉ።

“ይህ ዓመት ሰላምና እርቅ የሚወርድበት በመላ ኢትዮጵያ እና ኤርትራ እንዲሁም በመላው ዓለም፤ ቤተሰቦችና ማኅበረሰቦች ፈውስ የሚያገኙበት እንዲሆን እፀልያለሁ” ሲሉ ባይደን ለኢትዮጵያ እና ለኤርትራ የአዲስ ዓመት የእንቁጣጣሽ የመልካም ምኞት መግለጫቸውን ማስተላለፋቸውን ቪኦኤ ዘግቧል።

Exit mobile version