የአሜሪካ አዲሱ ተመራጭ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን አገራቸው በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላትን ትብብር አጠናክራ ለመቀጠል ብሎም የዴሞክራሲ መርሆዎች እንዲከበሩ ለማድረግ ቁርጠኛ መሆኗን የውጭ ጉዳይ ፖሊሲያቸውን አስመልክቶ ሐሙስ ዕለት አመሻሽ ባደረጉት የመጀመሪያ መግለጫ ላይ አስታውቀዋል።

ፕሬዚዳንቱ “እያደገ የመጣውን አምባገነንነት” ለመግታት እንዲሁም አሜሪካ በየመን በሺህዎች ለቆጠሩ ሰላማዊ ሰዎች ሕይወት ማጣት ምክንያት የሆነውን የሁቲ አማፂያን ላይ የተጀመረው የማጥቃት ዘመቻ የሚሰጡትን ድጋፍ ለማቋረጥ መወሰናቸውን ገልጸዋል።

ባይደን የቀድሞው የአሜሪካ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ትራምፕ ያሳለፏቸውን ውሳኔዎች እና ከአገሪቱ እሴቶች ተቃራኒ ናቸው ያሏቸውን ውሳኔዎች በመቀልበስ ከተለያዩ የዓለማችን አገራት ወደ አሜሪካ የሚገቡ ስደተኞችን የመቀበል አቅም እንደሚጨምሩ እና አሜሪካ ከጀርመን ጦሯን ለማስወጣት የያዘችው ዕቅድ መሰረዙን ተናግረዋል።

“አሜሪካ ተመልሳለች፤ ዲፕሎማሲም ተመልሷል” ያሉት ፕሬዚዳንት ባይደን፣ “ቀድሞም እንደምታደርገው ሁሉ ዓለም ለዴሞክራሲ ዘብ እንዲቆም ጠንክራ፣ የበለጠ ቁርጠኛ ሆና እና የተሻለ ታጥቃ ትነሣለች” ብለዋል።

በቻይና፣ ሩስያ፣ ማይናማር እና በሌሎች የዓለማችን አካባቢዎች የሚታዩትን የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች፣ ጨቋኝነት እና አለመቻቻል እንደምትጋፈጥ ሆኖም ሁኔታዎች በሚፈቅዱበት ጊዜ ሁሉ ከተወዳዳሪዎቿ ጋር ትብብር ለማድረግ አሜሪካ ዝግጁ መሆኗን ጠቅሰዋል።
በትራምፕ ዘመነ መንግሥት ሞራላቸው ለተነካ የአሜሪካ ዲፕሎማቶችም “አይዟችሁ፣ ከጎናችሁ ነኝ” ብለዋቸዋል።

ከሩስያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር ከቀድሞው ፕሬዚዳንት የተለየ ግንኙነት እንደሚኖራቸው እንዲሁም “ዋነኛዋ ተወዳዳሪያችን” ካሏት ቻይና ጋር መገዳደር እና መተባበርን ያመጣጠነ ቅርርብ እንደሚኖራቸው ተናግረዋል።

ኢራንን በተመለከተ ምንም ነገር ያልተናገሩት ባይደን፣ የቀድሞው ዲፕሎማት ቲም ሌንደርኪንግ የየመን ልዩ መልእክተኛ ሆነው መሰየማቸውንም ይፋ አድርገዋል።

አሜሪካ በሳኡዲ አረቢያ መሪነት በኢራን ይደገፋሉ ተብለው በሚጠረጠሩ የየመን ሁቲ አማፂያን ላይ ለሚካሄደው ዘመቻ የምትሰጠውን ድጋፍ ማቋረጧ ሊያመጣ የሚችለው ለውጥ ግን ግልጽ አይደለም።

የባይደን አስተዳደር ቀደም ሲል በተደጋጋሚ በየመን ላይ የምትፈጽመው ጥቃት ለሰላማዊ ሰዎች ሞት ምክንያት ሆኗል ተብላ በምትከሰሰው ሳኡዲ አረቢያ ላይ የተወሰኑ የጦር መሣሪያዎች ሽያጭ እገዳ መጣሏ ይታወሳል። ባይደን ይህ እገዳ እንደሚጸና ሐሙስ ዕለት አረጋግጠዋል።

ምንጭ፤ ዋሽንግተን ፖስት – EBC

Leave a Reply