Site icon ETHIO12.COM

ለኢትዮጵያ ባንኮች የሚቀርበው ግማሽ ቢሊየን ዶላር ብድር

የአፍሪካ ኢምፖርት ኤክስፖርት ባንክ (አፍሪ ኤግዚም ባንክ) ለኢትዮጵያ ባንኮች ግማሽ ቢሊየን ዶላር ብድር ለማቅረብ መወሰኑን አስታወቀ፡፡

የአፍሪ ኤግዚም ባንክ የደንበኞች ግንኙነት ዓለም አቀፍ ዳይሬክተር ረኔ አዋምበንግ እንዳሉት፣ ባንኩ ከሌሎች አፍሪካዊ ባንኮች ጋር መወዳደር ሳይሆን በፋይናንስ ዘርፍ የአፍሪካን ችግር በአፍሪካ ለመፍታት ይሰራል።

እስካሁንም ከ25 ቢሊየን ዶላር በላይ በአፍሪካ ንግድ ፋይናንስ ዘርፍ ለፕሮጀክቶች ድጋፍ ማድረጉን ተናግረዋል።

ላለፉት ዓመታት በአፍሪካ መንግስታት ፋይናንስ ዘርፍ ትልቅ ድጋፍ ሲያደረግ መቆየቱን ገልፀው፣ በኮቪድ-19 ወረርሽኝም ከሦስት ቢሊየን ዶላር በላይ ድጋፍ ማቅረቡን ተናግረዋል።

አሁንም ተጨማሪ ለጸረ-ኮቪድ ክትባት ግዥ የሚውል ከ2 ቢሊየን ዶላር በላይ ገንዘብ ለማቅረብ ከአፍሪካ ህብረትና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በጋራ እየሰራ መሆኑንም አመልክተዋል።

ባንኩ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ለተመታው የአፍሪካ ኢኮኖሚ ማገገሚያም ሶስት ቢሊየን ዶላር ለባንኮች ድጋፍ መስጠቱን ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ የተዘጋጀው መድረክ ዓላማም ከኢትዮጵያ የፋይናንስ ተቋማት ጋር በጋራ ለመስራት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ለመምከር ስለመሆኑ አንስተዋል።

ይህም የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ዕድገት አጀንዳዎች ማስፈጸም በሚያስችሉ ዘርፎች ለመደገፍ በኢትዮጵያ ለሚገኙ ባንኮች 500 ሚሊየን ዶላር ብድር ለመስጠት ባንኩ ውሳኔ ማሳለፉን ተናግረዋል።

ባንኩ ካሁን በፊት በኢትዮጵያ በተለያየ ዘር ከ1 ቢሊየን ዶላር በላይ ድጋፍ ማድረጉን አስታውሰዋል።

በመስከረም መጨረሻም ሁሉም ሂደቶች ከባንኮች ጋር ከተፈጸሙ በኋላ ብድሩ እንደሚቀርብ ገልፀው፣ ለእያንዳንዱ ባንክ ምን ያህል ገንዘብ እንደሚቀርብላችውም አሳውቀዋል፡፡

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ ገዥ ይናገር ደሴ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ባንኩ በአፍሪካ አገራት መካከልና አፍሪካን ከዓለም ጋር ያላትን ንግድ ለማሳለጥና በንግድ የማስተሳሰር ዓላማ ይዞ መቋቋሙን ተናግረዋል።

ከአፍሪ ኤግዚም ባንክ በርካታ የአፍሪካ አገራት ብድሮችና ሌሎች አገልግሎቶችን ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸው፤ ኢትዮጵያ መስራች በሆነችበት ኤግዚም ባንክ እስካሁን ተጠቃሚ እንዳልነበረች ገልጸዋል።

አፍሪ ኤግዚም ባንክ ለአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጣና ትስስር ስኬት አንዱ አሳላጭ ተቋም መሆነን ገልፀው፤ እንደሌሎች ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ሁሉ በአዲስ አበባ ቅርንጫፍ እንዲከፍትም ጥያቄ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ከአፍሪካ የገቢና ወጪ (ኢምፖርት ኤክስፖርት) ባንክ ጋር በቅርበት ለመስራት ቁርጠኛ መሆኑን መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ኢትዮጵያ እስካሁን ከባንኩ ጋር ተጠቃሚ ያልሆነችው የኢትዮጵያ ባንኮች ከውጭ ባንኮች መበደር እንዳይችሉ የሕግ ከለላ ስለነበር መሆኑን አንስተዋል።

Exit mobile version