Site icon ETHIO12.COM

ሊቃነ ጳጳሳት ከአሜሪካ የኮንግረስ አባላት ጋር ተወያዩ።-የኢ.ሃ.ተ ጉባኤ ቅርንጫፍ ጽ.ቤት በሮም ተመሰረተ

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ብጹዓን ሊቃነ ጳጳሳት ከአሜሪካ የኮንግረስ አባላት ጋር ውይይት አካሄዱ። በአሜሪካና በካናዳ የሚኖሩ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የ11 አህጉረ ስብከት ሊቃነ ጳጳሳት በዋሽንግተን ዲሲ ከኮንግረንስ አባላት ጋር ነው ውይይት ያደረጉት።

ሊቃነ ጳጳሳቱ በውይይታቸው የኢትዮጵያን እውነት ለኮንግረስ አባላቱ ማስረዳታቸው ታውቋል። እነዚሁ የቤተክርስቲያኒቱ ሊቃነ ጳጳሳት በተመሳሳይ ከአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ኀላፊዎችና ሴናተሮች ጋር ለመገናኘት ቀጠሮ መያዛቸው ተገልጿል። የጳጳሳቱ ከባለስልጣናቱ ጋር መገናኘት አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ የያዘችውን የተዛባ አቋም ለማስተካከል ይረዳልም ተብሏል። ምንጭ፦ የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ

በሌላ ዜና የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ በአውሮፓ የመጀመሪያው የሆነው ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት በጣልያን ሮም ተመሰረተ።የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ በሮም ከሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ጋር በመተባበር በሮም ከሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ጋር የተወያየ ሲሆን የጉባኤውን ሶስተኛ ቅርንጫፍ አደራጅቷል፡፡

በምስረታው ላይ የተገኙ የጉባኤው ጠቅላይ ፀሐፊ ሊቀ ትጉሀን ታጋይ ታደለ ኢትዮጵያ የእምነት ሀገር መሆኗን ህዝቧም አማኞች እንደሆኑ ገልጸው፤ አማኞች የሃይማኖትና የእምነት ልዩነታቸው ሳያግዳቸው ሀገራዊ አንድነታቸውንና ሉዓላዊነታቸው አስከብረው የኖሩ ስለመሆናቸው አብራርተዋል፡፡

በተጨማሪም ሃይማኖቶች የሰላምና የትብብር መሰረቶች በመሆናቸው ሁሉም አማኞች የሃይማኖታቸውን አስተምህሮ አክብረውና አስከብረው በጋራና በትብብር እንዲሰሩ በማሳሰብ በውይይቱ ወቅት ከተሳታፊዎች ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ በተያያዘም በሮም የኢትዮጵያ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ደሚቱ ሀምቢሳ ጉባኤው በሀገር ሰላምና የህዝብን አንድነት ከማጠናከር አንፃር መልካም ሥራ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቱ መደራጀቱ ወቅቱ የሚጠይቀውን ሰላምና አንድነት የሚያጠናክር እንደሚሆን ገልፀዋል፡፡ የጽህፈት ቤቱ ስራ የተሳካ እንዲሆን ኤምባሲው አስፈላጊውን ድጋፍ ሁሉ እንደሚያደርግም አረጋግጠዋል፡፡በሮም ከተማ የሚኖሩ በውይይቱ የተገኙት ኢትዮጵያዊያን የጉባኤው መደራጀት አስፈላጊነት አሳማኝ እንደሆነና ይህንንም እንዲጠናከርና ለሀገርና ለህዝብ የሚጠቅም ስራ እንዲሰራ ተሳታፊዎች ያላቸውን ቁርጠኝነት ገልፀዋል፡፡

የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ በአውሮፓ የመጀመሪያውንና ከሀገር ውጪ 3ኛውን ቅርንጫፍ በጣሊያንና አካባቢው በማደራጀትና የቅርንጫፉን አመራሮች በመሰየም እና አስፈላጊውን የስራ አቅጣጫ በመጠቆምና አመራር በመስጠት በጉባኤው መጠናቀቁን ከውጭ ጉዳይ ያገኘነው መረጃ ያሳያል ሲል ኢዜአ ዘግቧል፡፡

Exit mobile version