Site icon ETHIO12.COM

የጉጂ አባ ገዳዎች “ሸኔ የኦሮሞ ጠላት ነው” ሲሉ አወጁ፤ 2000 የጉጂ ኦሮሞዎችን ገሏል

የጉጂ አባ ገዳዎች በአንዳንድ የኦሮሚያ አካባቢዎች እንደሚንቀሳቀስ የሚነገረው ታጣቂው ቡድን ‘ሸኔ’ የኦሮሞ ጠላት ነው ሲሉ አወጁ። አባገዳዎቹ መንግሥት ሸኔ የሚለው እና እራሱን የኦሮሞ ነጻነት ጦር እያለ የሚጠራው ቡድን ‘የኦሮሞ ጠላት ነው’ ሲሉ የፈረጁት በቡድኑ በርካታ ንጹሃን ዜጎች በመገደላቸው ነው ብለዋል። ከዚህ ቀደም በተመሳሳይ የቦረና አባ ገዳ የሆኑት ኩራ ጃርሶ ታጣቂ ቡድኑን በተመሳሳይ ‘የኦሮሞ ጠላት ነው’ በማለት አውጀው ነበር።

የአገሪቱ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም ባለፈው ዓመት ይህንን ታጣቂ ቡድን ‘ሸኔ’ን እና ህወሓትን አሸባሪ ድርጅቶች ሲል መፈረጁ ይታወሳል። በቅርቡም እራሱን የኦሮሞ ነጻነት ጦር የሚለውና መንግሥት ሸኔ የሚለው ታጣቂ ቡድን መንግሥትን ለመጣል ከህወሓት ጋር በትብብር እንደሚንቀሳቀስ ይፋ አድርጓል።

ባህላዊው መሪ ታጣቂው ቡድን ላይ ውግዘት ያስተላለፉት “ኦሮሞ ሆኖ ኦሮሞን የሚገድል ጠላት ነው” በማለት እንደሆነ የጉጂ አባ ገዳ ጂሎ ማንዶ ለቢቢሲ ተናግረዋል። ባለፉት ሦስት ዓመታት በጉጂ ሕይወት እጅጉን ፈታኝ ሆኗል የሚሉት አባ ገዳ ጂሎ፤ “የኦሮሞ ነጻነት ጦር ለኦሮሞ ሕዝብ ነው የምታገለው ይላል። ለኦሮሞ የሚታገ ከሆነ ኦሮሞን መግደል የለበትም” ብለዋል።

በሁለቱ የጉጂ ዞኖች ማለትም በጉጂ ዞን እና በምዕራብ ጉጂ ዞን ባለፉት ሦስት ዓመታት ከ2000 በላይ ንጹሃን ሰዎች መገደላቸውን አባ ገዳ ጂሎ ማንዶ ይናገራሉ። ከሦስቱ የጉጂ አባ ገዳዎች መካከል አንዱ የሆኑት አባ ገዳ ጂሎ፤ “እኛ ስለፖለቲካው አይደለም። ኦሮሞ ኦሮሞን መግደል የለበትም። ኦሮሞን የሚገድል ጠላታችን ነው ያልነው። ለኦሮሞ ነው የምንታገለው ብለው ሕዝቡን እየጨረሱ ነው” ብለዋል። “በቅርቡ እንኳን ዱግደ ዳወ ተብሎ በሚጠራ አካባቢ በአንድ ቤት ውስጥ 13 ሰዎች ከገደሉ ሳምንት አልሆም” ይላሉ አባ ገዳው።

አባ ገዳው ጨምረውም፤ “መንግሥትን የሚፈልግ ከሆነ ከመንግሥት ጋር መዋጋት ነው እንጂ ሕዝብ ይጨርሳል እንዴ? ሕዝቡ ነው እያለቀ ያለው” በማለት ይናገራሉ። አባ ገዳው የመንግሥት ኃይል በተመሳሳይ ንጹሃንን ይገድላል ሲሉም ይከሳሉ።

እኛ መንግሥትንም አፈልግም

የጉጂ አባ ገዳዎች ከዚህ ውሳኔ ደረሱት ሕዝብ ወደ አደባባይ ወጥቶ የጉጂን ሕዝብ እየጨረሰ ያለውን ታጣቂ ቡድን ሥርዓት አስይዙ ብሎ ስለጠየቃቸው መሆኑን ለቢቢሲ ገልጸዋል።

አባ ገዳው ከዚህ ውሳኔ ላይ እንዲደርሱ አንዳችም የመንግሥት ጫና እንዳልገጠማቸው የተናገሩ ሲሆን “እኛ መንግሥትንም አንፈልግም፤ መንግሥት ቢኖር ኖሮ ይህን ያክል ሕዝብ ያልቅ ነበር?” በማለት ይጠይቃሉ። አባ ገዳው ጨምረውም 2000 ሰው ከማለቁ በፊት መንግሥት ጣልቃ በመግባት ግድያውን ማስቆም ነበረበትም ይላሉ።

በታጣቂው ቡድን ላይ ውግዘት ለመጣል “መንግሥት ሳይሆን ሕዝቡ ወጥቶ አቤቱታ አቀረበ፤ መንግሥት ከእኛ ጎን የለም፤ እንደዚህ ነው እያለቅን ያለነው። ይህን ውሳኔ አሳልፉልን ሲሉን [ሕዝቡ] ውሳኔውን አሳለፍን” በማለት ይናገራሉ።

በጉጂ ዞኖች ባለው የፀጥታ ችግር ሕዝቡ የዕለት ሥራውን ማከናወን እንደተሳናው አባ ገዳው ያስረዳሉ። “ሕዝቡ የሚሄድበት ግራ ገብቶታል። ገበሬው አያርስም፣ ነጋዴውም መነገድ አልቻለም። ለቅሶ መድረስ አልቻለም” የሚሉት አባ ገዳው ውሳኔው ለአካባቢው ሰላም ያመጣል ብለው ያምናሉ። ከዚህ ቀደም በተመሳሳይ የቦረናው አባ ገዳ ታጣቂው ቡድን የሕዝብ ጠላት ነው ብለው ከፈረጁ በኋላ በቦረና ሰላም ሰፍኗል ይላሉ።

በኦሮሞ ማኅበረሰብ ውስጥ አባ ገዳዎች በሕዝብ ዘንድ ከፍተኛ ተሰሚነት ያላቸው ሲሆኑ የሚያስተላልፉትም መልዕክት ተቀባይነት ያለውና ተጽዕኖ ፈጣሪ ነው። መንግሥትም የተለያዩ መልዕክቶችን ወደ ኅብረተሰቡ ማስተላለፍ ሲፈልግም በአባ ገዳዎች አማካይነት የሚያደርስበት አጋጣሚዎችም አሉ።

መንግሥት በምዕራብ ኦሮሚያ በሚገኙ በወለጋ ዞኖች እንዲሁም በደቡብ ኦሮሚያ በሚገኙት ጉጂ እና ቦረና ዞኖች ውስጥ ለሚፈጸሙ ጥቃቶች በአካባቢዎቹ የሚንቀሳቀሱትን የ’ሸኔ’ ታጣቂዎችን ተጠያቂ ያደርጋል።

ቡድኑንም ከምዕራብና ከደቡብ የአገሪቱ ክፍሎች ለማስወገድ የፌደራል መንግሥቱ ሠራዊትና የኦሮሚያ ክልል የጸጥታ አካላት በተለያዩ ጊዜያት ዘመቻዎችን ሲያካሂዱ ቆይተዋል።

bbc amharic

Exit mobile version