Site icon ETHIO12.COM

ህጋዊ መንግስትን ከአሽባሪ ቡድን ጋር እኩል ማየት ለምን?

የአሜሪካው ፕሬዚደንት ጆ ባይደን በኢትዮጵያ ላይ ተጨማሪ ማዕቀብ መጣል የሚያስችል ሰነድ አዘጋጀተው ፈርመዋል። ፕሬዚደንቱ የፈረሙት የዕቀባ ትዕዛዝ ሕጋዊውን የኢትዮጵያ መንግሥት ከአሸባሪው ሕወሓት ጋር እኩል በማየት ሊደራደር እንደሚገባ የሚያትት ነው።

ከፕሬዚደንቱ ፊርማ በኋላ የአሜሪካው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ወዲያወኑ ባወጡት መግለጫ በጦርነቱ ውስጥ ተሳታፊ የሆኑ አካላት ያለ አንዳች ቅድመ ሁኔታ ወደ ድርድር የሚመጡ ከሆነ አሜሪካ ልትጥል ያሰበችውን ማዕቀብ ለማዘግየት ዝግጁ ነች ብለዋል። ይህ መግለጫ የወጣው ኢትዮጵያ በህዝብ ድምጽ ምርጫ ተካሂዶ መንግስት ለመመስረት ሳምንት በቀሩበት ወቅት ሲሆን አንድምታው የጆ ባይደን አስተዳደር በመንግስት ላይ ከፍተኛ ጫና በማሳደር ለማስገደድና ቀደም ሲል ያሰቡትን ደካማ መንግስት መፍጠርን ዓላማ ያደረገ ነው።  

አሸባሪው ቡድን በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎችን በማይካድራ፣ ጭና፤ ጋሊኮማ፤ አጋምሳ መጨፍጨፉ፣ በርካቶችን ከቀያቸው እንዲፈናቀሉ ማድረጉ፤ የሰብዓዊ ቀውስ እንዲከሰት እና እንዲባባስ ማድረጉ፤ በርካታ የእምነት ተቋማትን፣ ሆስፒታሎችን እና ትምህርት ቤቶችን ማውደሙ የባይደን አስተዳደር ከበቂ በላይ መረጃ እያለው በዝምታ አልፎታል።

በአንጻሩ የኢትዮጵያ መንግስት የአሸባሪው ህወሃት ቡድንን አጥፊ አካሄድ ከመከላከል አልፎ ቡድኑ የፈጠረውን ሰብዓዊ ቀውስ ለማስተካከል እያደረገ ላለው ጥረት እና እየሰጠ ላለው ምላሽ እውቅና አልሰጠም። የመንግስትን ጥረት የባይደን አስተዳደር ብቻ ሳይሆን መላው የዓለም ማህበረሰብ ድጋፍ እና አድናቆት ሊቸረው ሲገባ ለማዕቀብ መዘጋጀት ተላላኪ መንግስት ለመፍጠር ያለመ መሆኑ ማሳያ ነው። 

ላለፉት በርካታ ዓመታት አሜሪካ በተለያዩ ሀገራት የሽብር ቡድኖችን ለማጥፋት በሚል ጣልቃ እስከመግባት የደረሰ እርምጃ ስትወስድ እንደቆየች የሚታወስ ነው። በአንዳንድ ሀገራት ለራሷም ይሁን ለሀገራቱ ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ኪሳራ ያደረሰ እርምጃ ወስዳለች። ሽብርተኛን መከላከል እና ማጥፋት የአሜሪካ ቀዳሚ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ማጠንጠኛ መሆኑን የሚያስታውሱት የዘርፉ ምሁራን ይህ በኢትዮጵያ ላይ ሲሆን ለምን ይቀየራል የሚል ጥያቄም ያነሳሉ፡፡ 

የኢትዮጵያ አሜሪካውያን የዜጎች ምክር ቤት ባወጣው መግለጫ የአሜረካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ከሰብዓዊ መብት ጥሰት ጋር በተያያዘ በኢትዮጵያ ላይ ማዕቀብ እንዲጣል ያስተላለፉትን ትዕዛዝ ሊሰርዙት ይገባል ሲል የጠየቀው በዚህ ምክንያት ነው።

ምክር ቤቱ የኢትዮጵያ መንግስት በክልሉ ያለውን ሰብዓዊ ቀውስ ለመቀየር በማሰብ የተናጠል የተኩስ ማቆም ውሳኔ በወሰነበት፣ የሰብዓዊ ድጋፍ አቅርቦቱ እንዲቀላጠፍ ከዓለም አቀፍ ሰብዓዊ ድርጅቶች ጋር በጥምረት እየሰራ ባለበት ይህ ውሳኔ መወሰኑ ተገቢነት እንደሌለው አመልክቷል። ከዚህ በተጨማሪ ምክር ቤቱ ሀገሪቱ አዲስ መንግስት ለመመስረት ዝግጅት እያደረገች ባለበት፣ የአፍሪካ ህብረትም ችግሩን ለመፍታት ጥረት የሚያደርግ ልዩ ልዑክ ሰይሞ እንቅስቃሴ በጀመረበት በዚህ ወቅት የባይደን አስተዳደር ይህን ውሳኔ ማሳለፉ ተቀባይነት የለውም ብሏል።

የሽብር ቡድኑ በመንግስት የታወጀውን የተናጠል የተኩስ ማቆም ውሳኔ በመጣስ በትግራይ ክልል ብቻ ሳይወሰን በአጎራባች ክልሎች እና አካባቢዎች ጦርነቱን እያስፋፋ ባለበት በዚህ ወቅት የአሜሪካ መንግስት የወሰነው ውሳኔ የኢትዮጵያን አሁናዊ ሁኔታ በሚገባ ያልተገነዘበ በመሆኑ ፕሬዝዳንቱ የወሰኑትን ውሳኔ መለስ ብለው ማየት እንደሚገባቸው ከየአቅጣጫው ግፊቶች እየተደረጉ ነው፡፡

ይህን የአሜሪካን ውሳኔ ልዩ የሚያደርገው ኢትዮጵያ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አባል እና አለም አቀፍ ሕግን በማክበር እና በማስከበር እንቅስቃሴ ውስጥ ንቁ ተሳታፊ መሆኗ እንዲሁም የውስጥ ጉዳይን በራስ አቅም የመፍታት ሙሉ መብት ያላት ሉዓላዊት ሀገር መሆኗን የዘነጋ በሚመስል መልኩ  ከሽርተኛ ቡድን ጋር በውዴታ ሳይሆን በግዴታ መደራደር አለባችሁ ማለት ሉዓላዊነት ላይ መሳለቅ እንደሆነ የሚናገሩም አልጠፉም፡፡

ላለፉት በርካታ ዓመታት ወንዶችን ሲያኮላሽ፣ የትግራይ ልጃገረዶችን ሳይቀር ሲደፍር እና ሲያስደፍር፣ ለምስኪኑ ለትግራይ ህዝብ አንዳችም የህይወት አኗኗር ዘይቤ ለውጥ ሳያመጣ፤ ነገር ግን በስሙ ሲምል እና ሲገዘት የቆየው የሽብር ቡድኑ እየፈጸመው ያለው የሽብር ድርጊት መወገዝ ነበረበት።

የሀገሪቱን ሀብት እንደግል ንብረቱ ሲመዘብር፣ ህዝቡን በዘር ሲከፋፍል፣ በተለያዩ አካባቢዎች ሁከት እና ግድያ እንዲፈጸም በገንዘብ እና በቁሳቁስ እንዳንዴም ህጋዊ ከለላ ሲሰጥ ለኖረ በመጨረሻም ለክልሉ ህዝብ ለዓመታት ጋሻ እና ከለላ በመሆን ሲያገለግለው የቆየውን የመከላከያ ሰራዊትን ሲወጋ  የባይደን አስተዳደር ማውገዝ ሲገባው ይህን ዕኩይ ተግባር ለማስተካከል የሚጥርን ህጋዊ መንግስት ከሽብረተኛ ቡድን ጋር በእኩል አይን ማየት ለምን? ይህ ኢትዮጵያውያን በጋራ የሚያቀርቡት ወሳኝ ጥያቄ ነውና ህጋዊ መንግስትን ከሽብር ቡድን ጋር እኩል ማየቱ ከባይደን አስተዳደር የማይጠበቅና በኢትዮጵያውያን ዘንድም ተቀባይነት የሌለው ነው። 

Exit mobile version