ETHIO12.COM

ኢትዮጵያ “ከአክቲቪስቶችም” ይጠብቅሽ!

ማሳሰቢያ ይህ ጽሁፍ ሁሉንም ሳይሆን አብዛኞችን ታሳቢ ያደረገ መሆኑ ቅድሚያ ይታወቅልኝ። በኢትዮጵያ ራሳቸውን የሾሙ በርካታ መንግስታት አሉ። እነዚህ ለውጡን ተከትለው የተፈለፈሉ መንግስታት ሳያመዛዝን የሚከተላቸውን የህዝብ ብዛት እየነዱ ነው መንግት የመሆን ቅዠት ውስጥ የገቡት። መኖሪያ ቤተ መንግስታቸው ፌስ ቡክ ወይም ዩቲዩብ ነው። እነዚህ ራሳቸውን አክቲቪስት፣ የማህበራዊ ሚዲያ አርበኛና አዋጊ መኮንን አድርገው የሰየሙ አካላት ከቀን ወደ ቀን እየፈጸሙ ያሉት ተግባር አሳፋሪ ብቻ ሳይሆን አስደንጋጭም እየሆነ ነው።

ዛሬ አገራችን ዙሪያዋን በክፋት አምራቾችና ቅጥረኞቻቸው እየተለበለበች ባለበት ሁኔታ የማህበራዊ ሚዲያ አንቂዎች አስፈላጊነት ለጥያቄ አይቀርብም። በዚህ ወቅት አገሪቱን እንደ ወረርሽኝ ካጠቃት የዘር አመለካከት ለመታደግ ማህበራዊ አንቂዎች ያስፈልጋሉ። በዚህ ረገድ በርካታ መልካም ተግባራት ተከናውነዋል። ራሳቸውን ሳይሾሙ በጨዋነት የዜግነት ሃላፊነታቸውን የሚወጡ፣ እንደ ተልባ የማይንጫጩ ግን ስራ የሚሰሩ ምርጥ ባለ እውቀቶች የማየት እድል አጋጥሞናል። የነቁ ናቸውና በሚገባ ያነቁናል። ሲያጠቁም ቦታ መርጠውና የክፉዎችን ምሽግ እንዴት እንደሚበሱት አሳይተውናል። በተቃራኒው ሹመት ደርበው መረን የለቀቁ፣ ሁሉም ስፍራ የሚዋኙ፣ እንደ ከርከሮ እዚህም እዚያም እየረገጡ የሚያደባዩ ተበራክተዋል።

” ሚስጥሩ ተጋለጠ” እያሉ ሚስጢር በመፍጠርና በመተንተን ሳንቲም የሚያመርቱ፣ “ከፍተኛ የጦር መኮንን ነገረኝ” በሚል ተመሳሳይ ዲስኩር የሚያሰራጩ ” አወቅሽ አወቅሽ ሲሉሽ” አይነት የማህበራዊ አንቂዎች ዛሬ ላይ ስናያቸው ” የንቃተ ህሊና” ስልጠና የሚያሻቸው፣ እንኳን ሊያነቁ የመንቃት አቅም እንዳላቸው እንኳን እንጠራጠራለን።

ከላይ እንዳልኩት በዕውቀት ላይ ተመስርተው፣ በቀናነት የሚሰሩና የሚተጉ እንዳሉ ሁሉ በተቃራኒው የማሰቢያ ኪሏቸው አነስተኛ የሆነ የአገር ሚስጢር ሲበትኑ እያየን ነው። ጦር ሜዳ ድረስ ገብተው “እናዋጋ” የሚሉ፣ ከከፍተኛ የመከላከያ ሰራዊት አመራሮች ጋር ሆነው የሰሙትን የሚበትኑ “አንቂዎችን” ማየት የተለመደ ቢሆንም የሰሞኑ ግን ዝም የማለት ትዕግስትን የሚፈታተን ሆኖ አግቸዋለሁ።

“ወታደራዊ መረጃን የመሰል በጥብቅ መያዝ ያለበት ጉዳይ አደባባይ ላይ በመዘርጋት ምን አይነት ድል ይጠበቃል። አንድ ግለሰብ ተነስቶ እስከ ከፍተኛ ወታደራዊ አመራሮች ጋር በመቅረብ ወታደራዊ መረጃ የሚያገኝ ከሆነ፣ ወታደራዊ ተቋሙ እንደ ተቋም ፈርሱዋል ማለት ይቻላል። informal / መደበኛ ያልሆነ/ ግኑኝነት የትኛውም ግለሰብ ከአመራሮች ጋር ሊኖረው ይችላል፤ ነገር ግን በተቋም ደረጃ ያሉ ጥብቅ ሚስጥሮች በቀላሉ ግለሰቦች እጅ የሚወድቁ ከሆነ አመራሮቹ ተጠያቂ መሆን አለባቸው። ወታደራዊ ተልዕኮ በ social media አይመራም። እንዲህ ያሉ ክስተቶች በተከታታይ ሲከሰቱ እያየን ነው፤በዚህ እንዝላልነት ምክንያት ለሚጠፋው ….” ሲሉ ምርቱ በየነ የሚባሉ ዜጋ በፌስ ቡክ ገጻቸው የጻፉትን ሳይ ነው እኔም ሁሌ ሲመላለስብኝ የነበረውን ሃሳብ ይፋ ለማውጣት የተነሳሁት።

አቶ ምርቱ እንዳሉት የአገር መከላከያን ህንጻ መጎብኘትም ሆነ የአገራችንን ከፍተኛ መኮንኖች ኢመደበኛ በሆነ አግባብ ማግኘት ብዙም አይገርምም። በጉብኝቱ ወቅት በዛ “የአገር መከላከያ” በተባለው ውብ ህንጻ ውስጥ ያሉትን የግለሰቦች ሳይሆን የአገር ሚስጢር ፌስ ቡክ ላይ አውጥቶ መርጨት ግን አይፈቀድም። ሲጀመር በዚህ ደረጃ ሚስጢርን መናገርንስ ምን አመጣው? ጀነራል ብረሃኑ ጁላና ባጫ ደበሌ ፎቷቸው ከአቶ መሳይ መኮንንና ናትናኤል ጋር በፌስ ቡክ መከላከያ ደጅ ላይ ተነስቶ በማህበራዊ ሚዲያ ሲበተን ” በድሮን የተፈጸመውን ጥቃት አየን። ይገርማል ዶክመንቱን በቪዲዮ ይዤ እመለሳለሁ” የሚል ካፕሺን/ መግለጫ ሲከተል ነገሮች እንደተበላሹ ሸቶኝ ነበር።

አልቆየም ከላይ የተያያዘውን ሃሳብ ናትናኤል መኮንን በፌስ ብኩ ገጹ ለጠፈ። በመሶበ ተራራ ላይ ተህነግ እየገነባ ያለው የአየር መቃወሚያ በዚህ በሁለት ቀን እንደሚወድም አስታወቀ። ሙሉውን ከላይ አንብቡት። ( በነገራችን ላይ ጀነራል መርዳሳ የሚመሩት አየር ሃይላችን ማንንም ስለማያስተጋና ወሬ ስለሌለ እንጂ ይህ የተባለው የአየር መቃወሚያ ግንባታ ሙከራ ከስድስት ቀን በፊት አፈር ነህና ወደ አፈር ትመለሳለህ እንደተባለው ሆኗል)

አሁን ስለናትናኤል አቆማለሁ። ከዚህ በላይ ስለሱ ማለት ብፈልግም አልችልም። የሚባል ነገርም የለም። ለሁሉም ግን ለማንቃትና ሃላፊነት ለመውሰድ መጀመሪያ መንቃት፣ ለመንቃት የሚችል አንጎልና ነቅቶ ሃላፊነትን የሚመዝን ልቡና እንደሚያስፈልግ ለመጠቆም እወዳለሁ። መሳይ መኮንን አብሮ ስለነበር ይህን ጉዳይ ይደግመዋል ብዬ አላስብም።

ነገር ግን ኤታምዦር ሹሙም ሆኑ ሌተናል ጄነራል ባጫ ደበሌ በየትኛው የወታደር ሳይንስ ላይ ተመስርተው ነው እንዲህ ያለ ከፍተኛ ሚስጢር ለማህበራዊ ሚዲያ ግብአት እንዲሆን አድርገው የሚያካፍሉት? ምንስ ውጤት እንዲገኝ ነው እንዲህ ያለ ከባድ ጉዳይ በየኮሪዶሩ የሚያወሩት? እንዴትስ ነው የመከላከያ ኦፕሬሽን እንደዚህ እንደ ቀላል ጉዳይ የታያቸው? ስንቱንስ ሚስጢር ነው የዘከዘኩት? ይህ ጉዳይ ሊያስጠይቅ ይገባል። ጀነራል ብርሃኑ ጁላም ሆኑ ባጫ በግልጽ ሊመረመሩ ይገባል።

ማጠቃለያ

ስሙን የጠቀስኩት ናትናኤል የሚዲያ አጠቃቀም ክህሎቱ ብዙም ባይስበኝም፣ ለማስተባበርና የትህነግን የሳይበር ጦርነት ለመመከት የሚያደርገውን ጥረት አደንቃለሁ። ይህን በሚገባ እንዲረዳልኝና አስተያየቴን በቀናነት እንዲያየው እጠይቃለሁ። አስቀድሜ እንዳልኩት ጉዳይ በአየር ሃይል በኩል አስቀድሞ ባይቋጭ መረጃ አቀብለህ ኦፕሬሽን አበላሽተህ ሊሆን እንደሚችል አስብ። እያደራጁ ያሉት አየር መቃወሚያ ነው።

የመከላከያ አመራሮች ክብራችሁን፣ ሚስጢራችሁን ጠብቁ። የአገርን ሚስጢር የመንፋት ህገ መንግስታዊ ስልጣን የሰጣችሁ አካልም ሆነ ድርጅት የለም። ለአንድ ወታደር ቅድሚያ መርሁ ሚስጢርን መቅበር መቻሉ ነው። ሚስጢርን፣ በተለይም የአገር ሚስጢርን ለማህበራዊ ሚዲያና ዩቲኡብ ገበያነት ማካፈል ያስጠይቃል። ዛሬም ባይሆን አድሮ ታሪካችሁን ጎዶሎ ያደርገዋል። በየመድረኩ ባንዶችን እያወገዛችሁ እናንተ ሚስጢር ካልጠበቃችሁ ጉዳቱ አሳሳቢ ይሆናል። የዛሬው ለትምህርት፣ ለመጨረሻ ትምህርት ይሆን ዘንድ እማጸናለሁ።

በሌላ አግባብ ግን “አክቲቪስት” ነን የሚሉ ወገኖች በቀን በቀን ሲተቹና ሲተነትኑ ኪሏቸው እየቀነሰ፣ ጥራታቸው እየጎደለ፣ ዝግጅታቸው እየላላ፣ ለዛቸው እየደበዘዘ፣ ጥልቀታቸው እያነሰ … በጥቅሉ ወደ መክሸፍ እንደምታመሩ ለማሰብ ጊዜ ብትወስዱ መልካም እንደሆነ ለማሳሰብ እወዳለሁ። “እኔ” የሚለውን ትርክት ከመንጋጋችሁ ነቅላቹህ ጣሉ። በፍጹም የአዛዥነት መንፈስ ውስጥ ሆናችሁ አትናገሩ። እናንተ ብቻ ተናዳጅ፣ አዋቂ፣ ማስጠንቀቂያ ሰጪና ተቆርቋሪ ሆናችሁ አትቅረቡ። እንደዚህ አይነት በሽታ የሚስተዋልባችሁ ጎበዝና ለበ ሙሉ አንቂዎች በሽታው ሳይጠናባችሁ ወደ ሚዛን ተመለሱ። አቶ Mirtu Beyene ሃሳብ እንደሰጥ ስላነቁኝ አመሰግናልሁ።

ከባህር ሃይል ስታፍ አንዱ ነኝ

Exit mobile version