Site icon ETHIO12.COM

ከትችት ያላመለጠው የባይደን አስተዳደር የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ

የዓለማችን ልእለ ኃያሏ ሀገር አሜሪካ ከሀገራት ጋር የሚኖራትን ግንኙነት የሚወስነው የውጭ ጉዳይ ፖሊሲዋ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ትችቶችን እያስተናገደ ይገኛል። በተለይም በመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት በአፍጋኒስታን፣ በኢራቅ፣ በኢራን እና በመሳሰሉት ሀገራት አሜሪካ በምታደርገው ጣልቃ ገብነት የተነሳ ለረጅም ጊዜ የቆየው ተቀባይነቷ እየተፈታተነው ይገኛል፡፡

አሜሪካ ላለፉት 20 ዓመታት በአፍጋኒስታን በቆየችባቸው ጊዜያት ታሊባንን ለማስወገድ በከፈተችው ጦርነት ወደ 3 ሺህ የሚጠጋ ወታደሮቿን ያጣች ሲሆን ያቀደችውን ማሳካት ተስኗት በቅርቡ አፍጋኒስታንን ሙሉ ለሙሉ ለመልቀቅ ተገዳለች። አፍጋኒስታንን መልቀቋን ተከትሎ በሀገሪቱ የተፈጠረው ቀውስ የባይደን አስተዳደር ክፉኛ እንዲተች አድርጎታል።

አሜሪካ ጦሯን ካሰወጣች በኋላ የተለያዩ የውጭ ሀገራት ዜጎቻቸውን ሲያስወጡ በነበረበት ወቅት በሺዎች የሚቆጠሩ ተስፋ የቆረጡ አፍጋኖች በካቡል አውሮፕላን ማረፊያ የፈጠሩት ትርምስ የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ተመልክቶታል።

በባይደን አስተዳደር ውስጥ የበዙት ከፍተኛ የፖሊሲ አውጪዎች እኤአ በ2012 የሊቢያ ቤንጋዚ ቀውስ እጃቸው የጎደፈ መሆኑን የሚያነሱ ብዙዎች ናቸው። በተሳሳተ መረጃ ላይ ተመስርቶ በተካሄደው የኢራቅ ጦርነት የግብር ከፋዩን ህዝብ ከፍተኛ ገንዘብ ብቻ ሳይሆን ለበርካታ አሜሪካውያንና ኢራቃውያን ህይወት መጥፋት ምክንያት እንደሆነ የታሪክ አዋቂዎች ይናገራሉ።

የፕሬዝዳንት ጆ ባይደን አስተዳደር በትግራይ ክልል ህግ የማስከበር እርምጃ ከተወሰደበት ጊዜ ጀምሮ በኢትዮጵያ ላይ የያዘው አቋም በእውነተኛ መረጃ ላይ ያልተመሰረተና የሁለቱ ሀገራት ታሪካዊ ግንኙነት የሚያሻክር መሆኑን ብዙዎች ሲተቹ ይደመጣል። የባይደን አስተዳደር በኢትዮጵያ ውስጥ ስላለው ወቅታዊ ሁኔታ እውነታውን እያወቀ “አይናችሁን ጨፍኑ” ማለቱ ለረጅም ዓመታት የዘለቀውን የኢትዮ-አሜሪካ የግንኙነት ድልድይ የሚሰብር ነው በማለት በርካታ ምሁራን ይናገራሉ።

መንግሥት በትግራይ ክልል ላለው ህዝብ ካለው ተቆርቋሪነት በመነሳት እርዳታ እንዲገባ ለማድረግ ጥረት እያደረገ ቢሆንም የጆ ባይደን አስተዳደር ግን “የሰብዓዊ መብት አይከበርም፤ መንግስት እርዳታ እንዳይገባ ከልክሏል” የሚሉ ውንጀላዎችን በማስቀመጥ ጥፋተኛ መደረጉ ተገቢ አለመሆኑን ብዙዎች ይተቻሉ። የተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት እና መገናኛ ብዙሃን

ጭምር ይህን በአግባቡ ለመረዳት አልፈለጉም። መጠየቅ ያለበትን አካልም ለመጠየቅ ፈቃደኝነት አላሳዩም።

ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በኢትዮጵያ ላይ የሚከተሉት አቋም የተሳሳተ ስለመሆኑ ከሚተቹት መካከል በቀዳሚነት የሚጠቀሱት የአሜሪካ ምክር ቤት አባላት ናቸው። እነዚህ የምክር ቤት አባላት ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በኢትዮጵያ ላይ የያዙት አቋም የውጭ ፖሊሲያቸው ውድቀት ማሳያ መሆኑን ይናገራሉ።

የአሜሪካ ምክር ቤት የሪፐብሊካን ፓርቲ የኮንግረስ አባል የሆኑት ክሪስ ስሚዝ አሁን የሚስተዋለው የአሜሪካ ፖሊሲ በአፍሪካ ቀንድ ውጥረትን እና ግጭትን የሚያባብስ ነው ይላሉ። ክሪስ ስሚዝ ህወሓት በስልጣን ላይ በቆየባቸው ዓመታት ሲፈጽማቸው የነበሩ የመብት ጥሰቶች በመኮነን የሚታወቁ ናቸው።

ክሪስ ስሚዝ በኢትዮጰያ ስላለው ወቅታዊ ሁኔታ በማንሳት የባይደን አስተዳደር ጭካኔ የተሞላበት ግፍ ማን እየፈጸመ እንደሆነ በውል ሊገነዘብ እንደሚገባ አስምረው ይገልጻሉ። ባለፈው ዓመት ጥቅምት ወር የሽብር ቡድኑ የፈጸመው ጭካኔ የተሞላበት ግፍ በወንጀል የሚያስጠይቅ መሆኑንም ያነሳሉ። ይሁን እንጂ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ጉዳዩን ችላ ብሎ አልፎታል በማለት ይተቻሉ።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት በሽብር ቡድኑ የሚፈጸሙ ማናቸውንም ጥፋቶች ችላ በማለት መንግስትን ብቻ እየተጫነ መሆኑ ትክክል አለመሆኑን የሚያነሱት ክሪስ መስሪያ ቤቱ በሽብር ቡድኑ እና በኢትዮጵያ መንግስት መካከል ያለውን ልዩነት በትክክለኛው መንገድ መመልከት ይጠበቅበታል ይላሉ፡፡ በሽብር ቡድኑ የሚፈጸሙ የሽብር ተግባትን በሙሉ ለፌዴራል መንግስቱ መስጠት ትክክለኛ እይታን አያመላክትም ባይ ናቸው ክሪስ፡፡

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት በሽብር ቡድኑ የሚሰራጩ የተሳሳቱ መረጃዎችን ብቻ በመመልከት በተሳሳተ መረጃ ላይ ተመስርቶ በኢትዮጵያ መንግስት ላይ የሚያሳድረውን ጫና ማቆም እንዳለበት ክሪስ አሳስበዋል፡፡ አክለውም የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት በኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ የተሳሳተ መረጃ መያዝ የጀመረው አሁን ሳይሆን ቀደም ብሎ ማለትም የሽብር ቡድኑ ለግጭቱ መቀስቀስ ምክንያት መሆኑ እየታወቀ ይህንን በይፋ ለማውገዝ ፍላጎት እና ድፍረቱን ከማጣት እንደሚጀምር አስታውሰዋል፡፡ በዚህም የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ እያራመደ ካለው አቋም አንጻር ውድቀት ገጥሞታል ብለዋል፡፡

የአሪዞናው ሴናተር ጆን ማኬይን አንቶኒ ብሊንከንን ለውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት በታጩበት ወቅት የአሜሪካ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ውድቀት ያጋጥመዋል ሲሉ ተቃውሟቸውን አሰምተው ነበር። “እየተናገርኩ ያለሁት ስለ አንቶኒ ብሊንከን ለቦታው ብቁ አለመሆን ወይም የአቅም ማነስ ብቻ አይደለም ይልቁንም ሰውየው ስልጣኑ ቢሰጣቸው ለአሜሪካ የውጭ ግንኙነት ውድቀት አደገኛ ምክንያት እንደሚሆኑም ጭምር እንጂ” ሲሉ ነበር በምክር ቤት የተናገሩት፡፡ ይህ የጆን ማኬይን ንግግር መሬት ጠብ ሳይል ይኸው አሜሪካ በዓለም ላይ ከነበራት ደረጃ ዝቅ ማለት ብቻ ሳይሆን በመሪዎቹ መካከልም እየተፈጠረ ያለው ልዩነት ለዓለም የፖለቲካ እና የዲፕሎማሲ ገበያ እንዲሰጣ አድርጎታል፡፡

የጆ ባይደን አስተዳደር በኢትዮጵያ ላይ የያዘው አቋም አሜሪካ በምስራቅ አፍሪካ እና በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ያላትን የቆየ ብሔራዊ ጥቅም ስሌት ውስጥ ያላስገባ ነው። ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ህጋዊውን መንግስት ወደ ጎን በማለት ከሽብር ቡድን የሚመጣን መረጃ ብቻ በመያዝ በኢትዮጵያ ላይ ተጽዕኖ ለማሳደር መንቀሳቀሳቸው አሜሪካ የምትከተለውን ፖሊሲ እንዲበላሽ ስለማድረጉ ሌላ ማሳያ አያስፈልገውም።

በሚዲያ ሞኒተሪንግና ትንተና ቡድን (ኢዜአ)

Exit mobile version