Site icon ETHIO12.COM

የአውሮፓ ፓርላማ ኢትዮጵያ ላይ ማአቀብ ለመጣል ያዘጋጀው ሰነደ ሚዛን የሳተ ነው

ለኢትዮጵያ እውነት ጀርባውን የሰጠ ሰነድ

ከሰሞኑ የአውሮፓ ፓርላማ አባላት በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ አንድ ውሳኔ ለማሳለፍ ደፋ ቀና እያሉ ይገኛሉ።

‘በትግራይ የሰብዓዊ ሁኔታ’ የሚል ርዕስ የያዘ የውሳኔ ሃሳብ ረቂቅ ተዘጋጅቶ ለአባላቱ ተበትኖ ይገኛል።

ይህ ሰነድ የተለመደውን ኢትዮጵያ ላይ ጫና የማሳደር ዝንባሌ በጽኑ የተንጸባረቀበት እንደሆነ ግልጽ ወጥቷል።

ጉዳዩን በቅርበት እየተከታተለ የሚገኘው ብራሰልስ የሚገኘው የቤልጂየም፣ ሉግዘምበርግና የአውሮፓ ህብረት ተቋማት የኢትዮጵያ ኤምባሲ የአውሮፓ ፓርላማ አባላት የተሳሳተ ውሳኔ ላይ እንዳይደርሱ በማስገንዘብ፤ ሰነዱ የዘነጋቸው በርካታ ጉዳዮች እንዳሉ በዝርዝር ለማስረዳት ጥረት እያደረገ ይገኛል።

ለፓርላማ አባላቱ ኤምባሲው በጻፈው ደብዳቤ ሰነዱ ላይ መካተት የሚገባቸው ጉዳዮች እንዳልተካተቱና የአሸባሪውን ህወሃት የግፍ ድርጊት እንዳልተመላከቱ አስገንዝቧል።

ኤምባሲው በጻፈው ደብዳቤ አሸባሪው ህወሃት በአገር መከላከያ ሰራዊት ላይ በፈጸመው ድንገተኛ ጥቃት የተነሳ ግጭት መከተሉን የተዘጋጀው ረቂቅ ሰነድ እንዳላካተተው ገልጿል።

በተጨማሪም የኢትዮጵያ መንግስት የተናጠል የተኩስ አቁም ውሳኔ ቢያሳልፍም አሸባሪው ቡድን በተቃራኒው ግጭትን በማባባስ ከትግራይ ክልል ውጪ በሌሎች የአገሪቱ አካባቢዎች ወረራ መፈጸሙን ረቂቅ ሰነዱ ከግምት እንዳላስገባው አመልክቷል።

በትግራይ ክልል ያለውን የሰብዓዊ ድጋፍ ፍላጎት አጋኖ ያቀረበው ረቂቅ ሰነዱ፤ በሌሎች የአገሪቱ አካባቢዎች የደረሰውን ሰብዓዊ ቀውስ ችላ ማለቱን ኤምባሲው አስረድቷል።

ከዚህ በተጨማሪ አሸባሪው ህወሃት በአፋርና በአማራ ክልሎች ወረራ ፈጽሞ ያደረሰውን የንጹሃን ግድያ፣ አስገድዶ መድፈር እንዲሁም እንስሳትን በጥይት የመግደል ግፍ በሰነዱ ሊካተት ያልቻለና ሚዛናዊነት ያልታየበት እንደሆነ ተመላክቷል።

የሰብዓዊ ድጋፍ ጥረቱን አሸባሪው ቡድን እያደናቀፈ እንደሆነ ማየት ያልወደደው ሰነዱ፤ የሰብዓዊ ድጋፍ ለማድረስ ወደ ትግራይ ክልል አቅንተው የውሃ ሽታ ስለሆኑት ተሽከርካሪዎች ያነሳው ነገር የለም።

የኢትዮጵያ መንግስት በተቻለው መጠን የሰብዓዊ ድጋፍ ተደራሽ እንዲሆን ጥረት ቢያደርግም አሸባሪው ቡድን በሚፈጥረው እንቅፋት ጥረቱ በሚፈለገው ልክ ሊሆን አልቻለም።

በዚህ ረገድ ውንጀላ የሚቀርበው ሰብዓዊ ድጋፍ ተደራሽ እንዲሆን ጥረት እያደረገ ባለው የኢትዮጵያ መንግስት ላይ መሆኑ የተሳሳተ ግንዛቤ በምዕራባውያኑ ዘንድ መያዙን ያሳያል።

ወይም ደግሞ የኢትዮጵያን እውነት የማየት ፍላጎት የለም።

ኤምባሲው እንዳስረዳው አሸባሪው ቡድን የሰላም ፍላጎት የሌለውና በግጭት ውስጥ መኖር የሚፈልግ ነው።

ለአብነትም የኢትዮጵያ መንግስት በአዎንታ የተቀበለውን የአፍሪካ ህብረት የጀመረውን የሰላም ጥረት አሸባሪው ቡድን አጣጥሎታል።

ኢትዮጵያ 40 ሚሊዮን ያህል ዜጎችን ያሳተፈ ስኬታማ ምርጫ ማካሄዷን ያስታወሰው ኤምባሲው፤ መንግስት መመስረቷን ገልጿል።

እውነታ ሊካድ ወይም ተዛብቶ ሊቀርብ እንደማይገባ በመግለጽ የአውሮፓ ፓርላማ አባላት የኢትዮጵያን እውነት በማየትና በአግባቡ በማጤን የተሳሳተ ውሳኔ ከማሳለፍ እንዲቆጠቡ አስገንዝቧል።

አሸባሪው ቡድን የሰላም ፍላጎት እንደሌለውና ለግጭት ጥማቱ ማርኪያ ህጻናትን በጦርነት ውስጥ እንደሚማግድ መዘንጋት እንደሌለበት ኤምባሲው አጽንኦት ሰጥቶታል።

ENA

Exit mobile version