Site icon ETHIO12.COM

ብሔራዊ ባንክ የጣለውን የብድር ዕግድ በከፊል አነሳ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ለተለያየ የቢዝነስ ዘርፎች ባንኮች ይሰጡ የነበረውን ብድር ላልተወሰነ ጊዜ እንዲያቆሙ የተላለፈው መመርያ ተግባራዊ መሆን ከጀመረ ከአራት ሳምንታት በላይ አስቆጥሯል፡፡ባንኮችም በዚህ መመርያ መሠረት የተፈቀዱ ብድሮች ሳይቀሩ እንዳይለቀቁ ተደርገው ቆይተዋል፡፡ በዚህ መመርያ መሠረት የተለያዩ ቢዝነሶች ከባንክ ሊያገኙ የሚችሉትን ብድር ባለማግኘታቸው በሥራዎቻቸው ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳደሩ አልቀረም፡፡

የማይንቀሳቀስ ንብረት አስይዞ መበደር እንደማይችል ጭምር የሚደነግገው ይህ መመርያ ተግባራዊ ከሆነ በኋላ ግን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ‹‹ብድር ሊለቀቅላቸው ይገባል›› ያላቸውን የቢዝነስ ዘርፎችና ሁኔታዎች እየፈተሸ፣ ባንኮች ብድር መስጠት እንዲችሉ በተከታታይ እያስታወቀ ነው፡፡ ከትናንት በስቲያም ሰኞ ጥቅምት 1 ቀን 2014 ዓ.ም. የአበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬ ምርት ዘርፍ ላይ ለተሰማሩ ኩባንያዎች የተቋረጠው የብድር አቅርቦት እንዲለቀቅላቸው ውሳኔ አስተላልፏል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ከትናንት በስቲያ ለባንኮች ባስተላለፈው መልዕክት መሠረት በአበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬ በማምረትና ለውጭ ገበያ በማቅረብ ላይ ለሚገኙ ኢንቨስተሮች ብድር መስጠት የሚችሉ በመሆኑ፣ በዚሁ መሠረት ደንበኞቻቸውን ማስተናገድ እንደሚችሉ አሳውቋቸዋል፡፡የአበባ፣ የአትክልትና ፍራፍሬ ኢንቨስተሮች ብድር እንዲሰጥ የተፈቀደበት አንዱ ምክንያት፣ በአብዛኛው ሥራቸው ከባንክ ብድር ጋር የተገናኘ በመሆኑ፣ ብድር እንዲቋረጥ መደረጉ ሥራዎቻቸው ላይ ተፅዕኖ ፈጥሯል በሚል የኢትዮጵያ አበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬ አምራችና ላኪዎች ማኅበር ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አቤቱታ በማቅረቡ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡

የማኅበሩ ዋና ዳይሬክተር አቶ ቴዎድሮስ ዘውዴ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ለዘርፉ የሚሰጠው ብድር መቋረጡ፣ በአጠቃላይ በአበባ፣ አትክልትንና ፍራፍሬ ምርትና የወጪ ንግድ ላይ ሊያሳርፍ የሚችለውን ተፅዕኖ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በማቅረብ የተሰጠው ምክንያት አሳማኝ ሆኖ በመገኘቱ ነው፡፡ብድር በቆመበት ወቅት ብዙ የዘርፉ አልሚዎች ላይ ጫና ፈጥሮ እንደነበርም የገለጹት ዳይሬክተሩ፣ በተለይ የሥራ ማስኬጃ ወጪ እንዲቸገሩም አድርጎ እንደነበር አክለዋል፡፡

በዚሁ የብድር ዕገዳ ሳቢያ የማስፋፊያ ሥራ እየሠሩ የነበሩ እርሻዎችም በተወሰነ ደረጃ ችግር ገጥሟቸው እንደነበርም አቶ ቴዎድሮስ ሳይጠቅሱ አላለፉም፡፡ የማስፋፊያ ሥራ ለመሥራት በዝግጅት ላይ የነበሩና ብድር ሲጠባበቁ የነበሩ፣ ብድር ለመጠየቅ ዝግጅት ላይ የነበሩ አልሚዎችም በተመሳሳይ በዕቅዳቸው ልክ እንዳይሄዱ የብድር ዕቀባው ተግዳሮት እንደነበረውም አስረድተዋል፡፡ አሁን ግን የዚህ ብድር መፈቀድ እንዲህ ያሉ ችግሮችን ለመቅረፍ ከማስቻሉም በላይ፣ በባንክ ብድር ምክንያት ሊስተጓጎሉ ይችሉ የነበሩ ሥራዎች እንዲቀጥሉ ያደረጋል በማለት፣ ብሔራዊ ባንክ የወሰደው ውሳኔ ተገቢ እንደሆነ አቶ ቴዎድሮስ ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ መመርያ ተግባራዊ መሆን ከጀመረ ወዲህ ባንኩ ብድር ይሰጣቸው ብሎ ውሳኔ ካስተላለፈባቸው ዘርፎች መካከል ቡና አብቃይና ላኪዎች ተጠቃሽ ናቸው፡፡ከዚያም በኋላ ለአስመጪዎችና ለዘይት አምራቾች የብድር ገደቡ እንደተነሳላቸው ይታወቃል፡፡ ባለፈው ሳምንትም በአምስት የተለያዩ ዘርፎች ላይ የተጣለው የብድር ገደብ እንደተነሳ ማስታወቁ አይዘነጋም፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ይህንን መመርያ ከአገር ደኅንነትና ኢኮኖሚዊ አሻጥሮችን ለመከላከል ታሳቢ በማድረግ ያወጣው መመርያ መሆኑ የሚታወስ ነው፡፡

ተንተርሶ የተቋረጡ ብድሮች በተለያየ ቢዝነሶች ላይ ጫና እያሳደረ መሆኑ እየተነገረ ሲሆን፣ በተለይ የሥራ ማስኬጃ ብድር ባለማግኘታቸው ሥራዎቻቸው ላይ እንቅፋት እየፈጠሩ ነው የሚሉ አስተያየቶች እየተደመጡ ነው፡፡በባንኮች በኩልም መንግሥት የወሰደው ዕርምጃ ተገቢና አገራዊ ኢኮኖሚውን ከማከም አንፃር የተወሰነ ቢሆንም፣ የብድር ዕገዳው ጊዜ እስከ መቼ ይሆናል የሚለውን ጉዳይ መመርያው መልስ የሚሰጥ ያለመሆኑ ግን ያሳስበናል ማለታቸው አይዘነጋም፡፡

ምንጭ፡- ሪፖርተር

Exit mobile version