Site icon ETHIO12.COM

“ማንነትን መሰረት አድርገው የሚስተዋሉ ዋልታ ረገጥ አስተሳሰቦች ሚዛን ጠብቀው እንዲሄዱ ይሰራል”


በተለያዩ ቡድኖች፣ መደቦችና ማንነቶች የሚስተዋሉ ዋልታ ረገጥ አስተሳሰቦች ሚዛን ጠብቀው እንዲሄዱ እንደሚሰራ ራዕይ ፓርቲ አስታወቀ።

የፓርቲው ሊቀመንበር አቶ ሊላይ ሀይለማርያም ዛሬ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንደገለጹት፤ ፓርቲያቸው ከወግ አጥባቂ ዝንባሌዎች ሆነ አፍርሰው ከሚገነቡ አስተሳሰቦች ይልቅ የሀገራችንን ተጫባጭ ችግሮች የሚፈታ፣ ህዝቡን የሚጠቅም፣ በስምምነት ውጤት ላይ የሚያተኩር እንዲሁም ከርእዮተ ዓለም ጥገኝነት የተላቀቀ የመካከለኛው መስመርን ተመራጭ ያደርጋል፡፡

በሀገራችን የቀኝና የግራ አሰላለፍ ልማድና ከመደባዊ ውግንና ዝንባሌ ይልቅ አጠቃላይ በሀገረ መንግስቱ ዙርያ ባሉ ዕይታዎች ላይ እንደሚያጠነጥን ገልፀዋል፡፡ የራዕይ ፓርቲ ይህንን በመረዳት እነዚህን አመለካከቶች የሚያቀራርብ አሰላለፍ እንደሚከተል ጠቅሰዋል፡፡

ፓርቲው ሀገሪቱ ያላትን ጠንካራ ጎን በማስጠበቅ እና ውስንነቶችም በማረም ሁለንተናዊ የእድገት ምዕራፍ መክፈት እንደሆነ ሊቀመንበሩ ተናግረዋል፡፡

ሀገሪቱ ያላትን መልካም እሴቶች በመጠበቅና ነባራዊ ሁኔታን እያነበበ ቋሚ መርሆችን ማእከል አድርጎ ጉዞውን በመፈተሸና በጥናት ላይ የተመሰረተ መርህ ተኮር ይከተላል ብለዋል፡፡

በዚህም ምክንያት ሁሉም ኢትዮጵያውያን አሰባስቦ የፓርቲው ማህበራዊ መሰረት ለማድረግ የሚያስችል አካታች ፖለቲካዊ ጉዞን ተመራጭ እንደሚያደርግ ገልፀዋል፡፡

ለሁሉም ዜጎች የምትሆን ሁሉም በኩራትና በምቾት የሚኖርባት የበለፀገች ኢትዮጵያን ለመፍጠር ፓርቲው ትግል እንደሚያደርግ ተናግረዋል፡፡ ይህንን ዓላማ የሚፃረሩ በግራም ሆነ በቀኝ የተሰለፉ አፍራሽ አስተሳሰቦችንና ተግባሮችን ሁሉ ፓርቲው እንደሚታገለው ገልፀዋል፡፡

ራዕይ ፓርቲ የተጋሩ የባህልና ታሪክ እሴቶችን መሰረት በማድረግ የትግራይ ህዝብ ከወንድሞቹ ኢትዮጵያዊያን ጋር አገሩን እንዲገነባ፤ ደብዝዘው የነበሩ ገንቢ የሆኑ የተጋሩ ባህሎችና እምነቶች ወደ ቦታቸው እንዲመለሱ እንዲሁም የትግራይ ህዝብ መሪዎችን እንደ ንጉስ የሚመለከት ሳይሆን መሪዎቹ በራሱ ፍቃድ ብቻ መምረጥ እንዲችል ካልፈለገም በሰላማዊ መንገድ ማስወገድ የሚያስችል ስርዓት ለመፍጠር ጠንክሮ የሚታገል መሆኑን አቶ ሊላይ አስታውቀዋል።

(ኢ ፕ ድ)

Exit mobile version