Site icon ETHIO12.COM

ትህነግ መስጊድ አወደመ፤ እስልምና ጉባኤ አወገዘ

አሸባሪው የትህነግ ኃይል በዛሪማ ከተማ የሚገኘውን መስጂድ ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ማውደሙን ተከትሎ የየአማራ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ተቃውሞውን አሰማ። ድርጊቱም ፍጹም የከፋ መሆኑንን አስታውቋል። ድርጊቱ በትግራይ ያሉ ሙስሊሞች ላይ ለዓመታት ሲካሄድ የኖረው ሙስሊም ጠል አመለካከት ውጤት እንደሆነ ተጠቁሟል።

አሸባሪው የትህነግ ኃይል በሰሜን ጎንደር ዞን አዲአርቃይ ወረዳ ዛሪማ ከተማ በሚገኘው መስጂድ ላይ በከባድ መሳሪያ ያደረሰውን ውድመት እንደሚያወግዝ የአማራ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ያስታወቀ ባሰራጨው መግለጫ ነው።

በአሁኑ ወቅት አሸባሪውና ወራሪው የትህነግ ኃይል በአማራ ክልል ላይ እየፈጸመ በሚገኘው ጦርነት በሕዝብ ሕይወት ላይ አስከፊ ግድያና መፈናቀል በየቀኑ የሚሰማ መርዶ መሆኑንን ያወሳው የምክር ቤቱ መግለጫ በዜጎች፣ በሕዝብ መገልገያ ተቋማትና መሠረተ ልማቶች ላይ እየደረሰ ያለው ውድመት በጥቅሉ ከሰው ልጆች የማይጠበቅ ብሎታል።

በሰሜን ወሎ፣ በዋግ ኽምራ፣ በደቡብ ወሎ አካባቢዎች በርካታ መስጂዶችና መድረሳዎች ጉዳት ደርሶባቸዋል፣ አማኞችም ተጎድተዋል ያለው መግለጫው ዝርዝሩ ወደፊት በጥናት የሚገለፅ መሆኑንም አመላክቷል።

ምክርቤቱ በመግለጫው አሸባሪው የትህነግ ኃይል ጉዳት ያደረሰበት ዛሪማ ከተማ የሚገኘዉ ጥንታዊ መስጂድ በርካታ ዓመታት እድሜ ያለው እና በቅርቡ በዘመናዊ መንገድ ተገንብቶ እንደነበርም ገልጿል። የዛሪማ መስጂድ ጥቅምት 7/2014 ዓ.ም ከቀኑ 10 ሰዓት 30 አካባቢ በአሸባሪው የትህነግ ኃይል በተተኮሰ ከባድ መሳሪያ ከፍተኛ ዉድመት እንደደረሰበት ከአካባቢው ኅብረተሰብ እና ከወረዳዉ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት የሥራ ኃላፊዎች በደረሰው መረጃ ለማረጋገጥ መቻሉንም በመግለጫው አመላክቷል፡፡

ከፖለቲካ ጋር አንዳች ግንኙነት በሌላቸዉ የእምነት ቤቶች ላይ የሚፈፀመዉን አውዳሚ ተግባር የእስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት በጽኑ ያወግዛል ብሏል፡፡ ወደፊት መስጂዱን መልሶ ለመገንባት በሚደረገው እንቅስቃሴ ኅብረተሰቡ የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያደርግ ምክር ቤቱ ጥሪ አቅርቧል፡፡ መንግሥት የሕዝቦችንና የእምነት ቤቶችን ደኅንነት እንዲያስጠብቅም የአማራ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ጠይቋል፡፡

በተመሳሳይ እነ አሕመድ ጀበልን የመሳሰሉ የሙስሊሙ ተቆርቋሪ ነን ባዮች ይህን ተግባር አለማውገዛቸው በሙስሊሙ ሕብረተሰብ ዘንዳ መንጋገሪያ ሆኗል። በትግራይ ሙስሊሞች መቀበሪያ ቦታ ለማግነት መከራ የሚያዩበትን እንድ ባዕድ የሚስተናገዱ መሆናቸውን ያስታወሱ ድርጊቱን ” እስልምና ጠል የሆነው አመለካከት ውጤት ነው” ሲሉ ጽፈዋል። ትህነግ ኤርትራን ሲወር ለትግራይ ብቻ ሳይሆን ቆለኛ የሚላቸውን የኤርትራ ሙስሊሞች ያገለለ ክልል እንደሚፈጥር ደጋፊዎቹን አንቂዎቹ በተደጋጋሚ ሲናገሩ እንደሚደመጥ የስታወቁም አሉ።

Exit mobile version