Site icon ETHIO12.COM

ትህነግ ማበዱን አረጋገጠ – መንግስትን ክዱና በእኔ ለመገዛት ተዘጋጁ አለ

” … ህፃናትን የእሳት እራት በማድረግ ላይ ያለው ኣረመኔው ቡድን ይብቃህ በማለት እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ድምፁ ሊያሰማ ይገባል!” ይላል የትግራይ ነጻ አውጪ ግንባር። ደጀን ሆኖ፣ ግንባር ወርዶ የሚደግፈውን የአገር መከላከያ ሰራዊት ላይ ሕዝብ እንዲነሳ ሲጠይቅ። “በቃኝ” ብሎ ላስፈነጠረውና ፍጹም ለሚጠላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ” በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ልጆችህን ጭፍጭፌያለሁ” ካለ በሁዋላ ” መንግስትህን ክዳና እኔን አንግስ” ሲል የተሻለ መሆኑንን ያስታውቃል።

በፈቃዱ ራሱ ተሞ፣ ቤተስብ መርቆና ሞራል ሰጥቶ ወደ ማሰልጠኛ የላከውን የአገር መከላከያ ሰራዊት “በግድ ታፍሶ የሄደ” ሲል እውነታውን በሃሰት ገልብጦ ሊያሳምን የሚሞክረው የነጻ አውጪው ቡድን “ፋሺስት” ሲል ደጋግሞ ያነሳል።

የኑሮ ውድነት እየለበለበው ከጉርሱ ነጥቆ ቀለብ እየላከ፣ መድሃኒት እያደረሰ፣ ቤንዚህ እየሰጠ፣ ተሽከርካሪ እየላከ ላለ ህዝብና መንግስት “ፋሺስት” የሚል ስያሜ የሚሰተው ትህነግ በጪና፣ በቆቦ፣ በጋሊሶማ፣ በማይካድራ፣ በውጫሌ፣ በጭፍራና በተለያዩ አካባቢዎች እንደ ጉንዳን እየወረረ ስለሚጨፈጭፋቸው ሰላማዊ ዜጎች የኢትዮጵያ ሕዝብ ምንም መረጃና ግንዛቤ እንዳለው አያስብም። “ሲኦልም ቢሆን ወርጄ” ባለባት አንደበቱ ” የኢትዮጵያ ህዝብ ስማኝ” ሲል እውቀትን እንደጻማት ከማረጋገጥ ውጪ፣ ልቡናው በሸፍጥና በግፍ የደነደነ መሆኑንን ከማመላከት ውጪ ሌላ አንድም ትርጉም ማግኘት አይቻልም።

ትህነግ ይቀጥላል። አንድ ከላሽ ለአምስትና ለአራት በማስታጠቅ፣ አንዳንዴም ባዶ እጃቸውን በመላክ የአሞራ ሲሳይ እየሆኑ ላሉ ኢትዮጵያዊያን ሃዘኔታውን ይገልጻል። ደጋግሞ ” ያሳዝናል” እያለ ሲገልጽ እነዚህ የተባሉት ” አሳዛኝ” ኢትዮጵያዊያንን ደጃቸው፣ ሰፈራቸውና መንደራቸውድረሰ እየወረ ማን ” በሂሳብ እናወራርዳለን” ስሌት እንደሚገድላቸው አልጠቆመም። ወይም ትግራይ ውስጥ ገብተው ወረው ስለመገደላቸው አላወሳም። በጥቅሉ ” ደጅህ መጥቼ ስዘርፍህ፣ ስገልህ፣ ሳወድምህ፣ በጅምላ ስጨፈጭፍህ ዝም በል” የሚል መልዕክት ያለው ይህ መግለጫ፣ ይህ እንዳይሆን የሚከላከሉትን ሁሉ በፋሽትነት ፈርጆ ለኢትዮጵያ ህዝብ ፍርድ እንዲሰጥ ይመኛል። ራሱንም የቀድሞው ቢረሳ በአሁኑ ገና ባልደረቀው የአፋርና የአማራ ንጹሃን ደም ላይ የተንጋለለ ጻድቅ አድርጎ ያያል። በሰው ማእበል እሳት ፊት ለፊት ህዝብ እየማገደ ” የልጆች ሞት አሳሰበኝ” ሲል ባስፈጃቸው ንጹሃኖች አጽም ጥርሱን ይፍቃል።

የትግራይ ነጻ አውጪ ከኢትዮጵያ በትክክል ስለመገንጠሉ ማስታወቅ እያቃረው፣ አቋሙን እንደ ድመት ማንም ደብቆ፣ ምን እንደሚፈልግ በገሃድ ሳይናገር በወረራቸው ስፍራዎች ሁሉ ምን እንደፈጸመ እየታወቀ ስለ ዓለም ዓቀፍ የወንጀል ፍርድም ያወሳል። “እኔ ስገልና ስጨፈጭፍ ትክክል ነው። እኔ የማልመራት ኢትዮጵያ ትበታተናለች፣ ይህንኑ ለማስፈጸም ሲኦል እወርዳለሁ” በሚል ሰፊ ቁጥር ያላቸው ሕጻናትን ያሰለፈና በዚህ ወንጀሉ መጀመሪያ የተጋለጠ ሆኖ ሳለ ስለ የሕሳናት መብት ተሟጋች ይሆናል።

ድሮንና ዘመናዊ ጀቶች የታጠቀ ቢሆን ምን ያህል የከፋ ወንጀል ይፈጽም እንደነበር ቀደም ሲል ባህር ዳርና ጎንደር፣ እንዲሁም አስመራ ያወናጨፈው ሮኬት ምስክር እንደሆነ፣ ከዛም በላይ የአርሶ አደር የቅርብ መጠቀሚያ የሆኑትን ድመት፣ ውሻ፣ አህያ እንዲሁም ላምና ከብት የሚረሽን፣ ባልን ገሎ ሚስትን አስከሬን ታቅፋ እንድትቀመጥ የሚያደርግ የክፉ ሁሉ ማሳያ የሆነ ድርጅት፣ ዘወር ብሎ በመግለጫው ዘግየቶም ቢሆን ዜጎቹን ለመከላከል በሕዝብ ግፊት የተነሳን መንግስት ኮንኖ ራሱን ሃዋሪያ ሲያደርግ ማየት የዘመኑ ታላቅ ተውኔት እንጂ ሌላ ምንም ሊሆን አይችልም።

” ባጭሩ” ይልና መግለጫው ሲያበቃ ” በደም የተበከለ” ብሎ የሚጠራውን ኢትዮጵያዊያን የመረጡትን መንግስት በመክዳት በትግራይ ነጻ አውጪ ግንባር መሪዎች ማለትም በእነ ደብረጽዮን፣ በክህደት ኢትዮጵያ ላይ በሚዛበተው ጌታቸው ረዳና ልጆቹን እየጨፈጨፉ፣ ቤተሰቦቹን እያፈናቀሉ ባሉት እነ ጻድቃን ለመመራት፣ ለዳግም የኢህአዴግ የተላጣፊነት ዘመን ዝግጁ እንዲሆኑ ይጠየቃል። አሁን ይህ ድርጅት ጤነኛ ነው?

የተገንጣይ ስም ይዞ አንድ ሉዓላዊ መንግስትን ለመምራት ዛሬም የሚመኝ፣ ከሁሉም በላይ በኦሮሚያ፣ በሶማሌ፣ በደቡብ፣ በአማራና ጋምቤላ የፈጸመው የትላንትና የግፍ ሪኮርዱ ….. ብቻ በጥቅሉ የልቡናና የአዕምሮ መንጠፍ ይሏል ይህ ነው!!

ይህን ስል የትግራይ ሕዝብ ላይ እየደረሰ ያለውን ማህበራዊ ቀውስ ለደቂቃም ባለመዘንጋት ነው። ትኩረቴ እውክለዋለሁ ለሚለው ሕዝብ እንኳን የማይሆነውን ትህነግ የሚባል ቆሞ ቀር ሃይል ክፋት ማሳየት እንጂ የትግራይ ሕዝብን እንደ ህዝብ አከብራለሁ። ውሳኔውም ሆነ ፍላጎቱን እደግፋለሁ። ሰላማዊው የትግራይ ሕዝብ ቤተሰቤ ነውና ሕመሙ ያመኛል። ከትሀንግ ጋር አብሮ ወረራ ላይ የተሰማራና አገሬን ሊበትን የተነሳውን ጭፍራ ግን ከትግራይ ሰላማዊ ህዝብ ለይቶ ማየት ግድ በመሆንና ጊዜውም እዛ ላይ ስላደረሰን …. አበቃሁ!

ፎቶ – ይህን ፎቶ የመረጥኩት ለጽሁፉ ማሳያና ለመግለጫው መመዘኛ ያመቻል በሚል ነው

በሰላሙ ሃይሌ ጥቁር አንበሳ

ዝግጅት ክፍሉ – ጽሁፉ የጸእሃፊው አስተያየት እንጂ የዝግጅት ክፍሉን አቋም አይወክልም። ምላሽ ለመስጠት ለሚፈልጉ ክፍት ነው። የትህነግን መግለጫ እንዳለ ከስር አትመነዋል።

ከትግራይ ነጻ አውጪ ግንባር ለጨቋኟ ኢትዮጵያ የተላለፈ መግለጫ

በደም የተነከረ የፋሽሽት ኣብይ ኣህመድ ቡድን ዕድሜ ለማራዘም ሲባል፣ ህፃናትን የእሳት እራት በማድረግ ላይ ያለው ኣረመኔው ቡድን ይብቃህ በማለት እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ድምፁ ሊያሰማ ይገባል!

በሕገ-ወጥ መንገድና በማጭበርበር የስልጣን ጥመኛ ፋሽሽት ቡድን፤ ካለፉት ሶስት ኣመታት ተኩል ጀምሮ እስከ ዛሬ ጥቅምት 12/2014 ዓ.ም የትግራይ ህዝብ እንደ ህዝብ፤ከምድረ ገፅ ለማጥፋት፡ ዕድሜ፣ፆታ፣ሃይማኖት፣የስራ ሁኔታ ወዘተ ሳይለይ በኣየር እና በምድር ህዝብን የማጥፋት ጅምላዊ የጀኖሳይድ ጭፍጨፋ ኣካሂደዋል፡፡ ኣሁንም በማካሄድ ላይ ነው።

ኣረመኔው የፋሽሽት ኣብይ ኣህመድ ቡድን በኣጠቃላይ ባለፉት 11 ወራት በተለይም ካለፈው ሰኔ ወር 2013 ዓ.ም እስከ ኣሁን ድረስ ባሉት ኣራት ወራት በትግራይ ሰራዊት ኣይቀጡ ቅጣት ተቀጥቶ ሽንፈት በተጎነጨባቸው ሁሉም ዓውደ ውግያዎች የፋሽሽት ሰራዊቱ በትግራይ፣ አማራና፣ ኣፋር በረሃዎች፣ ሜዳዎች፣ ተራራዎች፣ ኮረብታዎች እና ሸለቆዎች እንደቅጠል ረግፈዋል፡፡ የሀገሪቱ ማህበረ ኢኮኖሚ ምስቅልቅሉ ኣውጥቶ በውጭ ምንዛሬ የገዛቸው ዘመናዊ የጦር መሳርያዎችም የትግራይ ሰራዊት ንብረት ሆነዋል፡፡ ነገር ግን ፋሽሽት ቡዱኑ ይህንን ሁሉ ሽንፈት ተከናንቦም ቢሆን ለህዝብና ለሀገር ህልውና ቅንጣት ታክል እንደማይቆረቆርና ደንታ ቢስ መሆኑን በተግባር በማሳየት ላይ ነው፡፡

ይኸውም በማደናገር በዋነኛነት በኣስገዳጅ ኣፍሶ በየጦር ግንባሩ እየማገዳቸው ያሉት ለኣቅመ ሄዋንና ኣዳም ያልደረሱ ህፃናት እንዲሁም ዕድሜያቸው የገፋ ኣዛውንቶች ሳይወዱ በግድ የእሳት እራት እየሆኑ መሆናቸው በትግራይ ህዝባዊ ሰራዊት የተማረኩ ዕድሜያቸው 14፣15፣16 የሆኑ ህፃናት እንዲሁም ምንም ዓይነት የጦር መሳርያ ተኩሶው የማያውቁ ሽማግሌዎች ህያው ምስክር ናቸው፡፡

ይህንን በዓለም ኣቀፍ ፍርድ ቤት በጦር ወንጀለኝነት የሚያስከስስ ድርጊት እውነት መሆኑን ማረጋገጥ ለሚፈልግ ማንኛውም ንፁህ ህሊና ያለዉ ሰው፣ ዓለማቀፍ ማህበረሰብ፣ የሰብኣዊ መብት ተማጓች እና የግብረ ሰናይ ተቋም በኣጠቃላይ እያንዳንዱ ባለድርሻ ኣካል የትግራይ መንግስት በሩን ክፍት ኣድርጎ ሃቁን ለማሳየት ዝግጁ እና ፍቃደኛ መሆኑን በዚህ ኣጋጣሚ ሊገልፅ ይወዳል፡፡

የፋሽሽት ኣብይ ኣህመድ ቡድን በኣጠቃላይ ባለፉት 11 ወራት በተለይም ከመስከረም 27/2014 ዓ.ም ጀምሮ በኣራት ግንባሮች በትግራይ ሰራዊት ላይ በከፈተው ጦርነት የሞቱ፣ የቆሰሉ እና የተማረኩ የኣረመኔው ቡድን ቅጥረኛ ታጣቂዎች የሚበዙት ህፃናትና ወጣቶች መሆናቸው በእጅጉ ያሳዝናል፡፡ በነዚህ ግንባሮች በነበረው ፍልምያ የታየው ሌላ ኣስደንጋጭ ጉዳይ ኣንድ ጠመንጃ ለኣራትና ለኣምስት ሰዎች ኣንዳንዴም ምንም ዓይነት ጦርነት የማያውቁ ኣርሶ ኣደሮች ባዶ እጃቸውን ወደ ጦርነቱ ኣስገብቶ የኣሞራ ሲሳይ እያደረገቸው ይገኛል፡፡

ይህ ኣረመኔ ቡድን በጭፍራ፣በውጫሌ እና በወገል ጤና ግንባሮች ወዘተ የደረሰበት ሽንፈት ለመሸፋፈን የዘወትር የቅጥፈት ተግባሩ የሆነውን የበሬ ወለደ ውሸት የታከለበት የመግለጫ ጋጋታ ነጋ ጠባ በመለፈፍና የክተት ነጋሪት በመጎሰም እንዲሁም መቐለ ከተማ በጦር ኣውሮፕላኖች በተከታታይ ቀናት በመደብደብ የንፁሃን ደም በማፍሰስ ውርደቱንና ሽንፈቱን ለማካካስ በመፍጨርጨር ላይ ይገኛል፡፡

ይሁን እንጂ የዚህ ውጤት የፋሽስቱ ቡድን እድሜ ለማሳጠር የትግራይን ህዝብ ለበለጠ ትግል ተጠናክሮ እንዲዘምት የሚያደርግ ነው። ሰሞኑም ይህ ፋሽሽት ቡድን ሌላ ተጨማሪ ደም ሊያፈስ፤ “ደቡብ ወሎና ኣማራን ታደጉ” ወዘተ የሚል ሌላ የጥፋት ጥሪ በማስተጋባት ላይ ይገኛል፡፡ ነገር ግን በኣሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ ህዝብ ከዚህ በፊት ከትግራይ ሰራዊት ጋር ተዋግተው በመቶ ሺዎች የተደመሰሱ ልጆቻችን የት ገቡ ብሎ የፋሽሽት ቡድኑን ሊጠይቅ ይገባል፡፡ “እስከ መቼስ ነው ኣንዳችም ጥቅም ለማናገኝበት ጦርነት ልጆቻችን የምንገብረው” ብሎ ሊነሳ ይገባል፡፡

ባጭሩ በደም የተነከረንና የሰላም ጥሪን ወደ ጎን ኣሽቀንጥሮ ኢትዮጵያ ደም እንድታነባ ያደረገው እና በማድረግ ላይ ያለውን የፋሽሽት ኣብይ ኣህመደ ቡድን ዕድሜ ለማራዘም ሲባል ህጻናትን የአሳት እራት በማድረግ ላይ ያለው አረመኔ ቡድን ይብቃህ በማለት እያንዳንዱ የኢትዮጵያዊ ድምፁ የሚያሰማበት ወቅት ኣሁን መሆኑን ኣውቆ የድርሻው ሊወጣ ይገባል፡፡የህፃናት ደም በከንቱ መፍሰስ ሊቆም ይገባል!የትግራይ መንግስትጥቅምት 12/2014 ዓ.ምመቐለ

Exit mobile version