Site icon ETHIO12.COM

የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ወቅታዊ መግለጫ

የተሰነዘረብንን እኩይ ጥቃት መክተን የአገራችንን አንድነትና ሉዓላዊነት እንጠብቃለን

አሸባሪው የትህነግ ኃይል በ27 ዓመታት የሥልጣን ዘመኑ አያሌ ዜጎች ላይ  መከራና እንግልት በማድረስ የአገርን ሐብት ሲዘርፍና ሲያዘርፍ እንደነበር ይታወቃል፡፡  ትህነግ በውስጥና በውጭ እንዲሁም በሐሳብ በመድረክ ላይ በተደረገው የተቀናጀ ትግል  የአገራችንን ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ እድገት የሚመጥን ሐሣብ የማመንጨት አቅም መንምኖበት በ2010 ዓ.ም ከሥልጣን ተወገደ፡፡  ይህ ትግል ያስገኘው ድል ለአገራችንና ህዝባችን  በተስፋ የተሞላ አዲስ ምዕራፍ መክፈት ችሎአል፡፡

ይሁን እንጂ አሸባሪው የትህነግ ቡድን በጠብመንጃ የራሱ አድርጎ ከነበረው የመንግሥት ሥልጣን በህዝባዊ ተቃውሞና በመድረክ ትግል ቢነጠቅም፣ በሥልጣን ዘመኑ የዘረፈውን ሐብት በመጠቀም ላለፉት አራት ዓመታት በአገራችን ረብሻ እና ግጭቶችን በመፍጠርና በማስፋፋት  አገራችንን  ለማፍረስ ያለውን ዓላማ ለማሳካት አቅሙን ሁሉ አሟጦ ሲሰራ ቆይቷል፡፡   እንደ ሸኔ ካሉት የሽብር  ኃይሎች  ጋር በመመሳጠር  የብሔርና የኃይማኖት ግጭቶችን በመፍጠር የአያሌ ዜጎችን ህይወት ለቀውስ ዳርጓል፡፡  ብዙዎችን ለሞት፣ ለአካል ጉዳት፣ ለሥነ-ልቦና እና  የንበረት ጉዳት አጋልጦአቸዋል፡፡

የትህነግ የሽብር ኃይል ግጭትና ሁከት በመፍጠር የዜጎችን  ህይወት ለመከራ ከማጋለጥ አልፎ፣  በጀግናው መከላከያ ሰራዊታችን  የሰሜን ዕዝ  ላይ ባደረሰው የክህደት ጥቃት  የአገራችንን ሉዓላዊት፣ ሠላምና መረጋጋት ለአደጋ አጋልጦ ነበር፡፡ ይህ የሽብር ቡድን በቅርቡ በአማራ እና በአፋር ህዝቦቻችን ላይ ባደረሰው ወረራ፣ በመቶ ሺዎች የሚቀጠሩ  ዜጎቻችንን ከመኖሪያ ቀዬአቸውና ከሐብት ንብረታቸው በማፈናቀልና በመዝረፍ፣ ሴቶችን በመድፈር፣ ዘግናኝ ግድያዎችን በመፈጸም ተወዳዳሪ የሌለው ጭካኔ አሳይቶአል፡፡ 

አሸባሪው የትህነግ ኃይል ከተላላኪዎች ጋር በማበር ኢትዮጵያን ለመበተን የፎከረበትን  ህልሙን ለማሳካት፣ ያለውን ኃይል ሁሉ ማሰማራት ብቻ ሳይሆን ከአገራችንን ጠላቶች ጋር በጋራ እየሰራ ይገኛል፡፡  

በአገር ሉዓላዊነት  ላይ ከማንም ጋር የማይደራደር የኢትዮጵያ ህዝብ  በፖለቲካ አመለካከት ልዩነት ሳይለያይ፣ የትህነግ የሽብር ቡድን የሰነዘረበትን እኩይ ጥቃት በአንድነት እየቀለበሱ ይገኛሉ፡፡  የክልላችን ህዝብም ለጀግናው የመከላከያ ሰራዊታችን ‹‹ለዶሮአችን እስከ ነፍሳችን››  በማለት የሚያስፈልገውን ሁሉ እየሰጠ ነው፡፡  

ትህነግ ትናንት እንደለመደው  የኢትዮጵያን ብሔር ብሔረሰቦች በትናንሽ ልዩነቶች በመለያየት በመካከላቸው ጥርጣሬን ፈጥሮ እየገዛ ነበር፡፡ ዛሬም አንድነታችንን ለማዳከም የውሸት ፕሮፖጋንዳ ማምረትና ማሰራጨት ቀጥሎበታል፡፡ በተለይም በኦሮሞ ህዝብና በአማራ ህዝብ መካከል ያለውን ወንድመማችነት ለማዳከም ያልተበተበ ሴራ፣ ያልሰራ ፕሮፖጋንዳ፣ ያላሰራጨው የጥላቻ መርዝ አልነበረም፡፡  

ይሁን እንጂ የኦሮሞ ህዝብና እና የአማራ ህዝብ  እንደ ትናንቱ ከኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች ጋር ወድቀው በመነሳት ኢትዮጵያን እንደ ገነቧት፣ ዛሬም የአንድነቷ እና የህዝቧ ጸር የሆኑ፣ የአገራችንን ሰላምና መረጋጋት ለአደጋ የሚያጋልጡ የውስጥና የውጭ ጠላቶችን ለመቀልበስ ከየትኛውም ጊዜ በላይ በአንድነት ቆመው እየተፋለሙ ይገኛሉ፡፡

የኦሮሞ ህዝብና የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ጀግናው የመከላከያ ሰራዊት የትህነግ አሸባሪ ቡድንን ለመደምሰስ ሰሞኑን እየወሰደ ያለውን እርምጃ በመደገፍ የሚስፈልገውን ድጋፍ ሁሉ በመስጠት፣ የትህነግ ተላላኪ የሆነውን ሸኔ ከክልላችን ለማስወገድ የህዝብና የመንግሥት አስተባብረው በመስራት ላይ ይገኛሉ፡፡  የክልላችን ህዝብ  እንደ ትናንትናው አንድነታችሁን ጠብቃችሁ፣ በውጭና በውስጥ ኃይሎች ያስመዘገባሁን ድል  ዛሬም በአንድነት የአገራችን ጸር የሆኑ ኃይሎችን በማስወገድ አገራችንን ብልጽግና እንደምታሳኩ ጥርጥር የለውም፡፡

በመጨረሻም የኦሮሞ ህዝብ በክልላችን ለብዙ ዘመናት በሰላም ከኖሩ ብሔር በሔረሰቦች  ጋር በመተባበር  በህዝቦች መካከል ጥርጥር የሚረጩና ጥላቻን የሚያሰራጩ የጥፋት ኃይሎችን በመታገል፣ ለክልላችን ልማት በመደማመጥና በአብሮነት መስራት ከየትኛውን ጊዜ በላይ  አሁን አስፈላጊ ነው፡፡  በተለይም ከክልላችን የጸጥታ ኃይሎች ጋር በመተባበር ከአካባቢያችሁን ሰላምና መረጋጋት በንቃት እንድትጠብቁና ለጀግናው መከላከያ ሰራዊታችን እያደረጋችሁ ያላችሁን እርዳታ እንድቀጥሉበት  የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት በድጋሚ ጥሪውን ያቀርባል፡፡

የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት

ጥቅምት 19፣ 2014 ዓ.ም

ፊንፊኔ


Exit mobile version