Site icon ETHIO12.COM

በአሸባሪው ህወሀት ጥቃት ሀገራችን ፈጽሞ አትንበረከክም – የደቡብ ክልል መንግስት

የደቡብ ክልል መንግስት በወቅታዊ ሀገራዊ እና ክልላዊ ጉዳይ ላይ ባወጣው መግለጫ እንደገለጸው አሸባሪው ህወሀት እየፈጸመ ባለው ጥቃት ሀገራችን ፈጽሞ ልትንበረከክ አትችልም።

ሽብርተኛው ህወሀት ሀገሪቱን እየመራ በነበረበት ወቅት ሁሉንም አድራጊ ፈጣሪ በመሆን መላው የሀገራችን እና የክልላችን ህዝቦች በሽብር ቡድኑ ግልፅና ስውር እጆች ተጽዕኖ ስር ወድቀው እንደነበረ በመግለጫው ጠቁሟል።

በዜጎቻችን ላይ ዘግናኝ ሰብአዊ ጉዳትና ሀገራችንን በመዝረፍ ከፍተኛ በደል ሲፈፅም የቆየው የትህነግ ቡድን የተለያዩ አጀንዳዎችን በመቅረጽ በህዝቦች መካከል አለመተማመን እንዲኖር በማድረግ የሀገራችን ብሎም የክልላችን ህዝቦች የዚህ የሽብር ቡድኑ እኩይ ተግባር ሰለባ ነበሩ።

እኔ ያልመራኋት ሀገር ትፈርሳለች በሚል እሳቤ በርካታ የሽብር ተግባራትን በመፈጸም ላይ የሚገኘው ይህ የሽብር ቡድን በህዝቦች መራራ ትግል በበላይነት ከተቆጣጠረው ከፌደራል መንግስት ስልጣን እንዲወገድ ከተደረገ ወዲህ በቃላት ለመግለጽ ከሚቻላው በላይ በህዝባችን ላይ ግፍ እየፈጸመ መሆኑንም ይታወቃል።

የሽብር ቡድኑ በሀገሪቱ የተጀመረውን ለውጥ ለመቀልበስ ሁሉንም አማራጮች በመጠቀም በደል መፈጸሙ በተለይ ባለፉት 27 ዓመታት የክልላችንን ህዝቦች በሴራ ፓለቲካ ሲያተራምስ እንደነበርም ጠቁሟል መግለጫው።

አሸባሪው ትህነግ የሀገር መከታ በሆነው በጀግናው መከላከያ ሰራዊት ላይ ጥቃት ከፈጸመበት ጊዜ ጀምሮ በሀገራችን ህዝቦች ላይ ግልጽ ጦርነት አውጇል።

የሽብር ቡድኑ በከፈተው ጦርነት በርካቶች በግፍ ተገድለዋል፣ ሴቶች እና ህጻናት በቡድኑ የአስገድዶ መድፈር ወንጀል ተፈጽሞባቸዋል፣ ከሞቀ ቀያቸው የተፈናቀሉ ዜጎች ቁጥርም ከፍተኛ ነው።

የሽብር ቡድኑ የሀገርን እና የህዝብን ንብረት ማውደሙ እና አቅሙ የቻለውን ዘርፎ በመውሰድ የጭካኔውን ጥግ አሳይተዋል።

የአርሶ አደሩ የኑሮው መሰረት የሆኑ እና ከጦርነቱ ጋር ምንም ግንኙነት የሌላቸውን የቤት እንስሳት ጭምር በግፍ በመግደል የጭካኔ ተግባር ተፈጽሟል።

የክልሉ መንግስት በመግለጫ እንደጠቆመው በሀገራችን የተከፈተውን ጦርነት በአስተማማኝ ደረጃ በመመከት እና ድል በማድረግ የኢትዮጵያን ትንሳኤ እውን እናደርጋለን።

የህልውና ዘመቻውን ከግብ ለማድረስ መላው የሀገራችን ብሎም የክልላችን ህዝቦች የጀመሩትን ሁሉን አቀፍ ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉም የክልሉ መንግስት ጥሪ አቅርቧል።

የደቡብ ክልል መንግስት (ኤፍ ቢ ሲ)


Exit mobile version