Site icon ETHIO12.COM

ʺፋኖ የጥንቱ የጫካው ጌጥ፣ማተበ ጽኑ አይለወጥ”

ጠላቶች ይፈሩታል፣ ስሙን ሲሰሙ ገና ይሸበሩለታል፣ አተኳኮሱን ያደንቁለታል፣ አንድ ጥይት ለአንድ ጠላት ነውና የሚያድለው፣ ከፊቱ አይቆሙም፣ በእርሱ ፊት ለውጊያ አይሰለፉም፤ አልሞ ተኳሽ፣ ክብር አስመላሽ፣ ለወገን ደራሽ፣ እንባ አባሽ ነው፤ የሚመኩበት፣ የሚኮሩበት፣ መከራውን የሚያልፉበት፣ ሀገር የሚያስከብሩበት፣ ጀግና ጦረኛ፣ እምቢ ካለ የማይመለስ እልኸኛ፣ ሀገር ከተነካች የማይተኛም ነው፡፡

ፋኖነት ውርስ ነው ከአባት የተቀበሉት፣ ቃል ኪዳን ነው አጽንተው የሚይዙት፣ ስም ነው የሚጠሩበት፣ ጌጥ ነው የሚደምቁበት፣ ካባ ነው የሚለብሱት፣ ሕይወት ነው የሚኖሩበት፣ የድል ምልክት ነው የሚያሸንፉበት፣ ጥላ ነው የሚጠጉበት፣ ሲደክም የሚያርፉበት፣ ምርኩዝ ነው የሚደገፉበት፣ ጋሻ ነው የሚመክቱበት፣ ጦር ነው የሚዋጉበት፣ ብርሃን ነው የሚጓዙበት፣ የጨለማውን መንገድ የሚጠርጉበት፣ ታሪክ ነው ለልጅ የሚነግሩት፣ ዛሬም የሚኖሩበት ነው፡፡

ፋኖ እምቢ ለነጻነት፣ እምቢ ለማንነት ብሎ የሚነሳ፣ ነፍጥ የሚያነሳ ጀግና ነው፡፡ ሀገር ከነድንበሯ፣ ነጻነት ከነ ክብሯ እንድትኖር ፋኖ ነብሱን ሰጥቷል፣ ቤትና ንብረቱን ትቷል፡፡ ዱር ቤቴ፣ ለሀገር መሰቃየት ሕይዎቴ ብሎ ጫካ እየወረደ፣ ጠላቱን ሳይወድ እያስገደደ ከሀገሩ የሚያጠፋ ነው፡፡ ፋኖነት አሸናፊነት፣ ፋኖነት ኢትዮጵያዊነት፣ ፋኖነት፣ አይደፈሬነት፣ ፋኖነት ታሪካዊነት፣ ፋኖነት ነጻነት፣ ፋኖነት አንድነት፣ ፋኖነት ተፈሪነት ነው፡፡ የፋኖ ክንድ ጠላት ደምስሷል፣ ታሪክ አንግሷል፣ ደም መልሷል፣ ሀገርና ሕዝብ ክሷል፤ እምቢ ዘራፍ ብሎ እየገሰገሰ፣ ለተጨነቀው እየደረሰ፣ ያነባውን እምባ እያበሰ፣ ያዘነውን እንጀቱን እያራሰ የሚኖር ጀግና ነው ፋኖ፡፡

ፋኖ ቃሉን ከሚለውጥ አንገቱን ቢሰጥ ይሻለዋል፣ እስከ ሞት ይታመናል፣ ልቡ አይደነግጥም፣ ጀግንነቱ አይለወጥም፣ እጁ አይጨበጥም፣ ለጠላት ፋታ አይሰጥም፣ ሲሻው እግሩን ካለበለዚያ ግንባሩን እያነጣጠረ፣ ከምሽግ ምሽግ ተራምዶ እየሰበረ፣ ጠላትን እየመነጠረ፣ ተከብሮ፣ አስከብሮ የኖረ ነው፡፡ ብዙዎች ፈትነውታል፣ እንችለዋለን ብለው ገፍተውታል፣ እንጥለዋለን ብለው ታግለውታል፣ ዳሩ አንዳቸውም አልጣሉትም፣ ከክብሩ ንቅንቅ አላደረጉትም፣ የገፉት እየወደቁ፣ የቀረቡት እየራቁ ሁሉም እንዳልነበር ሆነው ተሸኙ እንጂ፡፡ በየዘመናቱ የተነሱት የኢትዮጵያ ጠላቶች የፋኖን ክንድ ቀምሰውታል፣ ጀግንነቱን አድንቀውለታል፣ ለክብሩ ሰግደውለታል፡፡ አሁንም እየቀመሱት ነው፡፡

ʺከጠመንጃው ጋር አለው መሃላ፣
ሰውዬው ላይሸሽ መውጊያው ላይላላ” ከጠመንጃው ጋር መሃላ አለው፣ እርሱም አይሽሽም፣ መውጊያውም አያብልም፣ አፈሙዙ አይስትም፣ የሚያዞረው አፈሙዝ የሚልከው ጥይት ያለ ቁም ነገር አይወድቅም፣ ምታ ከተባለበት ላይ ለይቶ ይመታል እንጂ፡፡ የፋኖ ጠመንጃና መሃላው
ዘመናትን ያስቆጠረ፣ ከጥንት ጀምሮ የኖረ፣ ዛሬም ያለ ነገም የሚኖር ነው፡፡ ፋኖነት ቢገፉት የማይወድቅ፣ ቢፍቁት የማይለቅ፣ ቢዝቁት የማያልቅ እንደ ተራራ የገዘፈ፣ እንደ ውቅያኖስ የሰፋ ደማቅ ታሪክ፣ ኀያል ስም ነው፡፡
ዘመናትን ሀገር የጠበቀው ፋኖ፣ ዛሬም ሀገር የመጠበቅ አደራውን ተቀብሎ ሀገር ለመጠበቅ በጦር ግንባር እየተፋለመ ነው፡፡ ኢትዮጵያን ክዶ፣ ሕዝቦቿን አዋርዶ መኖር ያሰበውን፣ ንጹሐንን የጨፈጨፈውን፣ ሀገር ለማፍረስ የሚውተረተረውን ጠላት ለማጥፋት ፋኖ ግንባር ላይ ነው፡፡ ፋኖ በገባበት ሁሉ ጠላት እየተደመሰሰ፣ ወደ መጣበት እየተመለሰ፣ የመጣበትን ቀን እየረገመ ነው፡፡

የትግራይ ወራሪና አሸባሪ ቡድን ሕዝብን ለማጥፋት፣ የሚያደርገው መውተርተር በጀግኖች ልጆች እየመከነ፣ ጠላትም እየተሽመደመደ ነው፡፡ ጠላት በገባባቸው የአማራ መሬቶች ቆራጥ የኢትዮጵያ ልጆች እየጠበሱት፣ በጥይት እየቆሉት፣ በባሩድ እያሹት ነው፡፡ አሁን ላይ መውጫም ማምለጫም ያለው አይመስልም፡፡ ጀግኖች ገብተውበታል፣ ዙሪያ ገባውን ከበውታልና፡፡ አንተም ከተከበበው ጠላት ታሪክ ለመጻፍ፣ ድል ለመጨመር ሂድ፣ የድርሻህን አድርግ፡፡

ʺፋኖ የጥንቱ የጫካው ጌጥ፣
ማተበ ጽኑ አይለወጥ” ፋኖ የሌለበት ጫካ ጌጥ የለውም፣ ግርማ አይኖረውም፣ በጌጥ የሚኖረው የሚከበረውና የሚፈራው ፋኖ ከመውዜሩ ጋር ሲውልበት፣ ኧረ ፋኖ፣ ፋኖ እያለ ሲያዜምበት፣ ጀግኖች ሲጫወቱበት፣ ዒላማ ሲመቱበት፣ ተስፋ ሲሰንቁበት፣ ተስፋ ሲሰጡበት ነው፡፡ የጫካ ጌጥ፣ ማተቡ የጸና በመከራ ዘመን የማይለወጥ ነው፡፡ ፋኖ ሀገር ሊያድን፣ ወገን ሊታደግ ትግል ላይ ነው፡፡ ሀገር ከሚያድኑ ጀግኖች ጋር ይተባበራል፣ ሀገር የሚያፈርሱትን ደግሞ ይቀብራል፡፡ የሀገሩ ሰላም ሳይመለስ፣ ጠላት ሳይደመሰስ ወደኋላ ላይመለስ፣ ምቾት ላያስታውስ ምሎ ገብቷል፣ ፊቱ ተቆጥቷል፣ ልቡ ሸፍቷል፡፡ የሚያቆመው የለም፣ ከወገኖቹ ጋር ኾኖ ጠላትን እንዳልነበር ያደርጋል እንጂ፡፡

ዛሬ ላይ ሀገርህን ሊወር፣ ቀዬህን ሊደፍር ጠላት አሰፍስፎ መጥቷል፣ መውዜርህን ወልውለህ፣ ትጥቅህን አስተካክለህ፣ ጀበርናህን ሞልተህ መጣሁበት ወደ አለበት ሥፍራ ሁሉ ትመም፡፡ አባቶች ደም አፍስሰው፣ አጥንት ከስክሰው ያቆዩትን ሀገር በአንተ ዘመን እንድትደፈር አትፍቀድ፡፡ በዋዛ ፈዛዛ የቆመች ሀገር የለችህም፤ ሀገርህ የቆየችው በደም መሠረት፣ በአጥንት ምሰሶነት፣ በሕይዎት ማገርነት ነው፡፡ አንተም መሠረቷ እንዳይናጋ፣ ምሰሶው እንዳይዘነብል፣ ማገሯ እንዳይላላ እምቢ ብለህ ተነስ፡፡ መሠረቱ ከተናጋ መኖሪያ የለምና፡፡
እንሂድባቸው፣ እናጥፋቸው የሚልህን ዝም ብለህ እንዳታየው፡፡ እንዳይመጡብን ተብለህ የምትፈራ እንጂ፣ እንሂድባቸው ተብለህ የምትደፈር የሕዝብ ልጅ አይደለህም፡፡
ታሪክህ የጸናው በአሸናፊነት ላይ ነው፡፡ ለአንተ ልክ የሚሆንህ ማሸነፍ ብቻ ነው፡፡ አሸንፈህ ሀገርህን አስከብር፡፡ መጥቶ የአንተን ቀየ መድፈሩ ብቻ ሳይሆን እንሂድባቸው ተብሎ መመከሩም ለአንተ አይስማማም፤ ቀየህን እሳተ ገሞራ አድርግበት፣ መንገዱን አንድድበት፡፡ እምቢ ስትል ነው ነጻነት የሚመጣው፣ አይሆንም ስትል ነው ወገንህ ነጻ የሚወጣው፡፡

በታርቆ ክንዴ. (አሚኮ)

Exit mobile version