Site icon ETHIO12.COM

የደቡብ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ጥሪ

ፓርቲው በወቅታዊ ሀገራዊ ሁኔታ ላይ መግለጫ ሰጥቷል። የመግለጫው ሙሉ መልዕክት ቀጥሎ ቀርቧል:-

ኢትዮጵያን በታሪኳ የሞከረ እንጅ ያሽነፈ ኃይል አልነበረም፣ አይኖርም።

ከጽንሰ ሐሳቡ እስከ ውልደቱና እድገቱ አልፎም የኖረበትን 27 ዓመታት በሙሉ ለስልጣኑ ሲል ኢትዮጵያን በዘር፣ በሃይማኖት፣ በጎሳና በጎጥ ከፋፍሎ ሲመዘብር የቆየው አሸባሪው ትህነግ ቡድን ብሶበት በሀገራዊ ለውጥ ምክንያት ስልጣኑን ካጣበት ጊዜ ጀምሮ “እኔ ያልመራኋት ኢትዮጵያ መፍረስ አለባት” በሚል እሳቤ ኢትዮጵያን ለማፍረስ ያለ የሌለውን ኃይል አሰባስቦ እየዘመተ ይገኛል።

በከፍተኛ መስዋእትነት የመጣውን ሀገራዊ ለውጡን ለመቀልበስ በተለያዩ ጊዜያት ሞክሮ ያልተሳካለት ይሄው አሸባሪ ቡድን ጥቅምት 24/2013 ዓ ም የሀገራችን ዳር ድንበር በመጠበቅ ላይ በነበረውን በኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት በሰሜን እዝ ላይ ጥቃት በመሰንዘር በይፋ ኢትዮጵያውያን በይፋ መውጋት ከጀመረ ድፍን አንድ ዓመት ሊሞላው ቀናቶች ብቻ ቀርተውታል። ዛሬም ይህንን እኩይ ተግባር ሳያቆም እየወጋት ይገኛል።

በሰሜን እዝ ጥቃቱ የተቆጣው መከላከያ ኃይላችንና መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ በወሰደው ሕግ ማስከበር ዘመቻ የጥቃቱ ጠንሳሾችና ባለቤቶችን ለሕግ ማቅረብ፣ እርምጃ በመውሰድና የቀሩትን መበተን ቢቻልም፣ በሕግ ማስከበሩ የተጎዱ የትግራይ አከባቢዎችን መልሶ ለማቋቋምና አርሶ አደሮች እርሻቸውን ተረጋግተው እንዲያርሱ የተሰጠውን ጊዜ አሸባሪ ቡድኑ እንደ መልካም አጋጣም በመጠቀም በአማራና አፋር ክልሎች ንጹሐንን በመግደል፣ ኢትዮጵያዊነትን ለማዋረድና ሀገር ለማፍረስ እኩይ ተግባሩን ቀጥሎበታል።

ጁንታው በፈጸማቸው በእነዚህ ጥቃቶች ንጹሐን ተገድለዋል፣ በሺህዎች የሚቆጠሩ ቤተሰቦች ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል፣ በሴቶች ላይ አሳዛኝና አስነዋሪ ተግባሮች ተፈጽሟል።

ከተቻለ ኢትዮጵያዊያንን በኃይል በማንበርከክ ወደ ቀድሞ ስልጣን መመለስ ካልሆነ ራሱ ያልመራትን ኢትዮጵያን ለማፍረስ ዓልሞ የተነሳው ይኸው ቡድን የቅዠት ዓላማውን ለማስፈጸም የኢትዮጵያን አንድነትና ጥንካሬ የማይፈልጉ ታሪካዊ የውጭ ጠላቶችና የውስጥ ባንዳዎችን አስተባብሮ እየሠራ ይገኛል።

ታላቋ ኢትዮጵያ በታሪኳ ተፈትና እንጂ ተንበርክካ እንደማታውቅ፣ በውጭ ጠላቶችም ኾነ በውስጥ ባንዳዎች ቢሞከሩት እንጂ ተሸንፋ እንደማታውቅ ታሪክ ምስክር ብቻም ሳይሆን ጠላትም ወዳጅም የማይክደው ሀቅ ነው።

የዚህ ዋነኛው ምስጢር ኢትዮጵያዊያን በሀገር አንድነትና በሉዓላዊነት ጉዳይ ላይ ድርድር አለማወቃቸው ነው። ዛሬም እንደ ጥንቱ የአሁኑ ትውልድ ትላንት አያቶቻችንና ቅድመ አያቶቻችን በከፈሉት ህይወት መስዋእትነት ያወረሱትን ነጻነት ከእጅ አዙር ቅኝ ገዥዎች ከውስጥ ባንዳ የመከላከልና ለመጪው ትውልድ ነጻ ሀገር የማስረከብ ኃላፊነት ተጥሎብናል።

ስለሆነም በሀገር ሉዓላዊነት ላይ ድርድር የማያውቀውን ሕዝባችን በዘር፣ በፖለቲካና በሃይማኖት ሳይለያይ አሸባሪው የህወሓት ጁንታ ቡድን ሀገር ለማፍረስ በያዘው እቅድ በአሁኑ ወቅት በአማራና አፋር ክልል ሕዝብ ላይ እየፈጸመ ያለውን ጥፋት በጋራ በመመከት ጁንታውን ግብዓተ መሬቱን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለመፈጸም በጋራ መነሳት አለብን።

የክልላችን ብልጽግና ፓርቲ አመራሩን፣ አባሉንና መላው የክልላችን ነዋሪዎች በማስተባበር ጀግናው የሀገር መከላከያ ሠራዊታችን አሸባሪውን ቡድን ለመደምሰስ እየወሰደ ያለውን እርምጃ በአይነት፣ በገንዘብና በሞራል እየደገፈ የቆየ ሲሆን ይህንን ድጋፍ አጠናክሮ ይቀጥላል።

ለሀገር ሠላም፣ አንድነትና ሉዓላዊነት ነቀርሳ የሆነውን ይህን የጥፋት ኃይል እስከ ወዲያኛው ተሸኝቶ የህልውና ዘመቻው በአጭር ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ የተጀመሩ ሥራዎችን ለማሳካት የክልላችን ሕዝቦች ከሀገር መከላከያ ጎን እንዲቆም የክልሉ ፓርቲ ጽሕፈት ቤት ጥሪውን ያቀርባል።

የክልላችን ፀጥታ ኃይሎችና ወጣቶች ክልላችን ሰላምና ደኅንነት በንቃት በመከታተል የጀመሩትን ሥራ እንዲያጠናክሩና ፀጥታ ኃይሎች የጋራ ሰላም ለማስከበር ለሚያደርጉት ጥረት ኅብረተሰቡም እንዲተባብራቸውም ያሳስባል።

የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት

ጥቅምት 21/2014 ዓ.ም
ሐዋሳ

አብራችሁን ስለሆናችሁ ደስተኞች ነን!

Exit mobile version