“እኔ ያልመራኋት ሀገር ትፈርሳለች የሚል እምነት ያለው አሸባሪው ጁንታ የሀገራችንን ህልውና ለመናድ እያደረገ ያለው ጥረት በሕዝባችን የጋራ ትግል እንደሚከሽፍ ጥርጥር የለንም” የደቡብ ብሔር ብሔረሰብ እና ሕዝቦች ክልል

የደቡብ ብሔር ብሔረሰብ እና ሕዝቦች ክልል መንግሥት በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳይ ላይ መግለጫ ሰጥቷል፡፡

በመግለጫውም እኔ ያልመራኋት ሀገር ትፈርሳለች የሚል እምነት ያለው አሸባሪው ጁንታ የሀገራችንን ህልውና ለመናድ እያደረገ ያለው ጥረት በሕዝባችን የጋራ ትግል እንደሚከሽፍ ጥርጥር የለንም ብሏል፡፡

መላው የክልላችን ሕዝቦች ለሀገር መከላከያ ሠራዊታችን ድጋፍ ጎን ለጎን የአካባቢያችንን ሰላምና ደኅንነት በመጠበቅ፣ ከጸጥታ ኃይሉ ጋር በትብብርና በቅርበት በመሥራት፣ ለህዳሴ ግድባችን ድጋፋችንን በማጠናከር፣ ሀገራዊ ኃላፊነታችንን በንቃት እንድንወጣ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን ብሏል በመግለጫው፡፡

የክልሉ መንግሥት መግለጫ ቀጥሎ ቀርቧል

በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል ከሕወሓት የሀገር ክህደት ተግባራዊ እርምጃ በኋላ መንግሥት ሲያካሂድ የቆየው የሕግ ማስከበር ዘመቻ የተናጥል የተኩስ አቁም ውሳኔ ሲወስድ ሕዝቡ በጦር እንቅስቃሴ ሳይረበሽ የመኸር እርሻውን የሚያከናውንበት ሁኔታ እንዲፈጠርለት እና የሰብዓዊ እርዳታና ድጋፍ አቅርቦ በነጻነት የሚከናወንበትን ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር ሲባል ነው፡፡

ይሁን እንጅ አሸባሪው ቡድን በመንግሥት የተወሰደውን የተናጠል የተኩስ አቁም ውሳኔ ተጠቅሞ ከስህተቱ ከመማር ይልቅ ኢትዮጵያን የማፈራረስ የጋራ ዓላማ ካላቸው ኃይሎች ጋር በመተባበር ሀገራችንን ለማፍረስና ሉዓላዊ ክብሯ እንዲደፈር እየሠራ ይገኛል፡፡

ይህ የሽብር ቡድን ለዚህ እኩይ ዓላማው፤ እድሜያቸው ያልደረሱ ሕጻናትን፤ የሃይማኖት አባቶችን፤ ሴቶችን ጨምሮ በግዳጅ በጦርነት በመማገድ ለሀገራችን ብቻ ሳይሆን ለዓለም አቀፍ ሕግጋት ተፈጻሚነት ደንታ የሌለው ጨካኝ ቡድን መሆኑን በይፋ እያስመሰከረ ይገኛል፡፡

አሸባሪው ሕወሓት ኢትዮጵያን በመራበት ዓመታት ኹሉ ሕዝብ አንድ እንዳይሆን ሲሠራ መቆየቱ ይታወቃል፤ በብሔር፣ በቋንቋ፣ በሃይማኖትና በተለያየ መነሻ ሲከፋፍል መቆየቱም እንደዚሁ የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነው።

የክልላችን ሕዝብና መንግሥት የአሸባሪ ቡድኑን የሀገር ክህደት እኩይ ተግባር አጥብቆ ያወግዛል፣ እያደረሰ ያለው ጥቃት ከአንድ የሕወሓት አሸባሪ ቡድን ብቻ አለመሆኑንና የተቃጣውም በአንድ አካባቢ ላይ ሳይሆን በሀገራችን ህልውናና ሉዓላዊነቷ ላይ መሆኑን መላው የክልላችን ሕዝብ በሚገባ ይገነዘባል፡፡

ሕወሓት የሽብር ተግባሩን ሊመኝና ሊሞክር ይችላል እንጂ በፍጹም ተግባራዊ ሊያደርግና ሊያሳካ አይችልም ምክንያቱም ሀገራችን በልጆቿ ታፍራና ተከብራ የኖረች፣ በሉዓላዊነቷ የማይደራደር ሕዝብና ታሪክ ያላት ሀገር ነች፡፡

መንግሥት የአሸባሪ ቡድኑ እኩይ ተግባር ላይ የሚወስደውን እርምጃ የክልላችን መንግሥት ከዚህ ቀደምም እየደገፈ ይገኛል፤ ይህንኑ በሚያስፈልግ መጠን አጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል፡፡

መላው የክልላችን ሕዝቦች ለሀገር መከላከያ ሠራዊታችን ድጋፍ ጎን ለጎን የአካባቢያችንን ሰላምና ደኅንነት በመጠበቅ፣ ከጸጥታ ኃይሉ ጋር በትብብርና በቅርበት በመሥራት፣ ለህዳሴ ግድባችን ድጋፋችንን በማጠናከር፣ ሀገራዊ ኃላፊነታችንን በንቃት እንድንወጣ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፡፡

እኔ ያልመራኋት ሀገር ትፈርሳለች የሚል እምነት ያለው አሸባሪው ጁንታ የሀገራችንን ህልውና ለመናድ እያደረገ ያለው ጥረት በህዝባችን የጋራ ትግል እንደሚከሽፍ ጥርጥር የለንም፡፡

የደቡብ የደቡብ ብሔር ብሔረሰብ እና ሕዝቦች ክልላዊ መንግሥት

ሐምሌ 9/2013

Leave a Reply