Site icon ETHIO12.COM

አደጋ አለ!! ሁሉም ወገን ይጠንቀቅ፤ እዛና እዚህ መጫወትም ይቁም!!

እየጋመ የመጣው የኢትዮጵያ ጉዳይ እየፈጠረ ያለው ቁጣ ይከብዳል። ከየአቅጣጫው የሚሰነዘሩት ሃሳቦች ትንፋሽ ይነሳሉ። ከሁሉም ወገን ማስተዋልና ማሰብ ደግ ነው። “ባለ በለኤል ሃይላችን ሰብረን እንግብ” በሚል አቋም በወሎ ግንባር የተጀመረው ውጊያ የሚዘገንኑ መረጃዎች እያሰማን ነው። የሚያሳዝነው ይህን ጤና የሚነሳ ዜና በማጦዝ የሰው ልጅን ህይወት መማገድ እንደ ጀብድ እየታየ በየማህበራዊ ሚዲያው የሚረጨው ሃሳብ ነው። ሃሰት እየታከለ ሰው መማገድ ስራ የሆነላቸው ምድር ላይ ካለው በተቃራኒ ወይም እያጋነኑ ይዘፍናል። ሰው ይረግፋል። የጥንቃቄ ያለህ!!

ላለፉት ሶስት ዓመታት ኢትዮጵያን አንቆ የያዛት የሴራ ፖለቲካና “ጎደለብኝ” እብሪት ከሁሉም ወገን ምስኪን ዜጎች ላይ በትሩን እያሳረፈ እዚህ ደርሷል። ምስኪኖችን ለርሃብ፣ ለስደት፣ ለጉስቁልና ዳርጎ አገሪቱን የሰቆቃ ተውኔት ማዕከል አድርጉታል። በሰቆቃው ደራሲና ተግባሪ ማንነት ጉንጭ አልፋ ክርክር ከመነሳቱ ውጪ ንጹሃን ዜጎች ከህጻን እስከ አዛወንት በአሰቃቂ ሁኔታ ሲገደሉ፣ ንብረታቸው ሲወድም፣ ሲዘረፉ፣ በማንነታቸው ሲጠቁ፣ ሲሰቀሉና ከሞቱ በሁዋላ ሲወገሩ አይተናል። እጅግ የሚገርመው ይህ ሁሉ ሲሆን ድርጊቱን በፊልም፣ በምስልና በድምጽ የሚያከፋፍሉን ፈጣን ተዋኞች መኖራቸው ነው።

በአገር መከላከያ ላይ በተወሰደ ድንገተኛ ማጥቃት ምን እንድተፈጠረና ምን እንደሆነ ለምስክርነት የተረፉ ነገረውናል። የክህደትን መጨረሻ ደረጃ እየታዘብን እንደየ ርህራሄ መጠናችን የተሰማንን ስሜት እያስተናገድን አድምጠናል። ያነቡ፣ ያለቀሱና መፈጠራቸው የጠሉ ስለመኖራቸው ተሰምቶም ነበር። የሴት መከላከያ ሰራዊት አባላት ጡት ተቂርጧል። በወገኖቻችን ላይ ከባድ መኪና ተነድቶባቸዋል። ዕድሜ ልካቸውን ሲጠብቁት በነበረ ውስን ከሃጂ ሃይል ሴራ እንደ ባዕድ እየተተፋባቸውና “አህያ” እየተባሉ አደባባይ ባዶ እግራቸውን ሲኢንከራተቱ ፊልም ቀርጸው ጋብዘውናል።

የመከላከያ ሰራዊት አባላት አስከሬን በየሜዳው እርቃኑንን ተጥሎ ጅብ ሲበላው፣ ጥንብ አንሳ ሲዘለዝለው በፎቶ እንድናይ ተደርጓል። ይህ ብቻ አይደለም ይህ ሁሉ የጀግትንነት ማማ ሆኑ ” በአርባ ደቂቃ ኦፕሬሽን አመድ አደረግናቸው” ተብሎ ተነግሮናል። ይህን የሚክድ አይንና ጆሮ ያለው ዜጋ የለም። ሊኖርም አይችልም። ካለ አፈጣጠሩ ብቻ መመርመርና መጠናት ያለበት ይሆናል።

በህግ ማስከበር ስም በተደረገው ጦርነት በትግራይ የተከሰቱ ህግን ያልጠበቁ ተግባራት ስለመኖራቸው ዜጎች በጩኸት አሰምተዋል። ማንም ያድርገው ማን ተፈጸመ ተብሎ የሚቀርብ የነበረው ሁሉ እንዲጣራ ከስምምነት ላይ ተደርሶ በቅርቡ ይፋ እንደሚሆን ስለሚጠበቅ የማይካድራ፣ የቆቦ፣ የጋሊኮማ፣ የጭፍራ፣ የሺና… አካቶ በንጹሃን ላይ ጥፋት የፈጸሙ ሁሉ ህግ እንዲፋረዳቸው ሰው የሆነ ሁሉ ብሄር፣ ዘርና አካባቢ ሳይለይ ጫና ሊፈጥር ይገባል።

መከላከያ ከትግራይ ከወጣና ያለምንም ቅድመ ሁኔታ መንግስት የተኩስ አቁም ካወጀ በሁዋላ ሰፊ የአማራ ክልልን የያዘውና ራሱን ለግማሽ ክፍለ ዘመን የትግራይ ሕዝብ ነጻ አውጪ ግንባር እያለ የሚተራው ሃይል

1- አማራ ክልል በዚህ ደረጃ ዘልቆ ወረራ ለመፈጸምና በግልጽ በምስልና ምስኪን አርሶ አደሮች ሲናገሩ እደተሰማው ዓይነት ግፍ ለመፈጸም ያነሳሳው ምክንያት ግልጽ አይደለም። ይህን ምክንያት የትግራይ ሕዝብም የተረዳው አይመስልም። አማራ ክልል ከብቶች፣ ድመትና ውሻ እንዲገደል የትግራይ ህዝብ ተስማምቷል? እንስሳ ቢገደል ለትግራይ ህዝብ ምን ይፈይዳል? እንደው በገፍ ከትግራይ ነቅሎ በመምጣት አማራ ክልል የምስኪን ገበሬ እርሻ ማሸድና መዝረፍ፣ ዶሮና እንቁላል ማጓጓዝ እንደው ለወደፊትስ ክብር ነው?

2- ከትግራይ ተነስቶ ጋይንት በመድረስ ወይም ነፋስ መውጫ እስኪደረሰ ባሉ የመስመር ከተሞችና ቀበሌውች ክሊኒክ፣ ትምህርት ቤቶች፣ ማውደም ያስፈለገበት ምክንያት ምንድን ነው? መዝረፍ የተመረጠበት ዋና መነሻ ነጥብስ ከየት ተነሳ? ለምን?

3- ከአንድ ቤት ሶስት፣አራት፣ አምስት … ሰዎችን መግደል፣ በጅምላ ማጥፋት በመጨረሻ ምን ለመሆን ነው? ገሎ በመጨረስ የሚሆንስ ምን ውጤት አለ? እስኪያልቅ ዝም የሚል አካልስ ይኖራል ብሎ ማሰብ የተቻለበት መንገድ …

4- በወሎ ግንባር በዚህ መጠን ወረራ መፈጸም ያስፈለገበትና የትግራይ ታዳጊዎች፣ አዛውንቶች፣ አባቶች፣ እናቶች እንዲሞቱ የሚፈረድበት አጋባብ ምን ለማግኘት ነው? ትህነግ ደሴን ይዞ ለትግራይ ሕዝብ ምን ያቀርባል? ምን ይጨምራል? እሰከምቼስ ደሴን ይዞ ይኖራል? ካልተሳካስ ? የተገላቢጦሽ ቢሆንስ? ያ ሁሉ የረገፈ ወጣት በምን ምክንያት ሞተ ተብሎ ሂሳብ ይወራረዳል? የሰው መንደርና የሰው ቀዬ ወሮ መሞት ምን የሚሉት ገድል ይሆናል? በየትኛው የክብር መዝገብ ላይ እንዲጻፍ ይሆናል?

5- ምን ባደረገ የአፋር ሕዝብ ይወጋል? በምን ዕዳው የከብት ጭራ ተከትሎ የሚኖር ምስኪን ሕዝብ ጦር ይከፈትበታል። በሃሩር ውስጥ መኖሩ ሳያንሰው፣ ድህነት የሚለበልበውን ደሃ ህዝብ መጨፍጨፍን ምን አመጣው? ለትግራይ ሕዝብ የአፋር ምስኪን ቢጨፈጨፍ ምን ይጠቅመዋል?

ብዙ ማለት ይቻላል። ይህን ለማለት ያነሳሳኝ አንድ ምክንያት ነው። ነብዩ ስሑል ሚካኤል በማህበራዊ ገጻቸው ” ጥንቃቄ እናድርግ” ሲሉ ያሰራጩት ሃሳብ ነው። አዎ ጥንቃቄ ያሻል። ሃሳባቸውን እጋራለሁ። ነገሮች እየተበለሹ ነው። ስሜት እየጎሸ ወደ መገንፈል እያመራ ነው። ነጹህ የትግራይ ተወላጆች እንዳሉ መዘንጋት የለበትም። ነብዩ እንዳሉት የትግራይ ሰዎች በምትኖሩበት ሁሉ ማህበራዊ ትሥራችሁን አጥብቁ።

ጥንቃቄ እናድርግ?!ባልተረጋገጠና ባልተጨበጠ አሉባልታ በተለያዩ የአገራችን ክፍሎች የሚኖሩ ንፁሃን ተጋሩ ላይ የሚቃጣ ማንኛውም አይነት ጥቃት ሆነ መገለል ፍፁም ተቀባይነት የለዉም።ህግና ስርዓት ባለበት አገር ዜጎች በደቦ ፍርድ እንዲጠቁ መወትወት ሃላፊነት የጎደለው ብቻ ሳይሆን በተለያዩ ወንጀሎችም ጭምር የሚያስጠይቅ አስነዋሪ ተግባር ነው። ህዝብም የወንድሙና የእህቱ ጠባቂ በመሆን ታሪካዊ ግንኙነቱ፣ ወንድማማችነቱና ኢትዮጵያዊ አንድነቱ መጠበቅ አለበት። በተለያዩ የአገራችን ክፍሎች የምትኖሩ ተጋሩም ከማንኛውም ግዜ በላይ አብራችሁ ከምትኖሩት ማህበረሰብ ጋር ያላቹ ቀረቤታና መልካም ግንኙነት አጽንታቹ የአከባብያቹና የመላ አገራችን ሰላም በመጠበቅ ረገድ ያላቹ ዜግነታዊ ሚና በሚገባ አሳዩ፣ ግዴታቹ ተወጡ እንዲሁም መብታቹ ጠይቁ።ሁሉም ያልፋል… ለሚያልፍ ግዜ የማያልፍ ታሪካዊ ጠባሳ እንዳንተው ሁላችንም ከፍተኛ ጥንቃቄ እናድርግ።

ነብዩ ስሑል ሚካኤል)

ነብዩ ጥሩ ብለዋል። አንድ መታከል ያለበት ነገር ሁሉም የሚወደውን ነገር መንከባከብ ይፈልጋልና “አንተ የምትወደው ላይ ቆሜ አንተ የምትጠላውን ግን እኔ የምወደውን እጭንብሃለሁ” የሚለው እሳቤ አሁን ጊዜው አልፎበታል።

ትህነግ እንዲያስተዳድረው የሚፈልግ ሃይል ምን አልባትም ከትግራይ ውጪ ቢሰላ መልሱ ግልጽ ነው። ስለሆነም አሁን ሕዝብ እያለቀ ያለው ለሚሳካ ጉዳይ ነው? ወይስ ለማይሆን ቅዠት የሚለውን ጉዳይ አበጥሮ መመልከት ብለጠት ይሆናል። የሶማሌ ክልል ሌላ ክልል ሄዶ ልውረር እንደማይለው ሁሉ የትግራይ ክልልም ሌላውን ክልል ለመውረር ሲነሳ “ለምን” ቢባል፣ “አትወርም” የሚሉ ቢነሱ ፍትህ ተጓደለ ማለት ያስቸግራል። የሚቻልም አይሆንም።

በዚህ ደረጃ ነገሮች ተካረው ግጥሚያው ከሯል። ጦርነት ላይ ” ለምን ገደልከኝ” ብሎ አቤቱታ አይሰራም። ሊገድል የሚሄድ ይገደላል። ሊገድለ የነበረ ይገድላል። ሲባዛ ይገዳደላሉ። ውጤቱ ቆሻሻ ቢሆንም ጦርነት መገዳደል ብቻ ነው። በጦርነት ተገዳድሎ አቤቱታ ማሰማት “እኔ ልግደልህ አንተ ዝም ብለህ ሙት፣ እኔ ላሸንፍ አንተ ተሸነፍ፣ እኔ እጓዳህ ሰተት ብዬ ልግባ አንተ …” የማለት ያህል ነውና አይሰራም። ግጥሚያው ተጀምሯል። ወደ መጨረሻው እየሄደ ነው። ቢቻል ሁሉም ወገን ጫና ፈጥሮ እንዲቆም ማድረግ፣ ካልሆነም ሁለት ቦታ መጫወትን ማስወገድ፣ ይህ ካልሆነ ከኈቱ አንዱን በገሃድ መርጦ መጫወት፣ ካልሆነም … ከሁሉም ወገን ሕዝብ እይታ የሚያመልጥ ነገር የለምና ሁሉም ወገን ይጠንቀቅ።

ነጻ አስተያየት – ሰብስቤ አያልነህ ገጽ


Exit mobile version