Site icon ETHIO12.COM

“የሀገር ሉዓላዊነትን አደጋ ላይ የሚጥል የጥፋት ተልእኮ የያዘ ጥምረት ፍፁም ተቀባይነት የለውም” የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት

የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት አደጋ ላይ የሚጥል የጥፋት ተልእኮ የያዘ ማንኛውም አይነት ጥምረት ፍፁም ተቀባይነት የሌለው መሆኑን የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ገለጸ።

በኢትዮጵያ ላይ እየደረሰ ያለው ግፍና ጫናም ለምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና ጭምር የሚተርፍ መሆኑን ገልጿል።

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮችን አስመልክቶ መግለጫ ሰጥቷል።

በመግለጫው የኢትዮጵያ ሕዝብ ራሱ መርጦ የሚያቆመውን እንጂ ከሀገር ውስጥም ኾነ ከውጪ “ተጠፍጥፎ የሚመጣለትን አሻንጉሊት መንግሥት” በታሪክ ተቀብሎ አያውቅም፤ ዛሬም አይቀበልም ብሏል።

የምክር ቤቱ ሰብሳቢ ዶክተር ራሔል ባፌ፤ የአንዳንድ የሀገራት ሚዲያዎች፣ የኢትዮጵያ መንግሥታት ያለቀለትና የተበታተነች አስመስለው እየቀረቡ ነው ብለዋል።

በሰሜን አሜሪካ ራሳቸውን የፌዴራሊስት /ኮንፌዴራሊስት/ ጥምረት በማለት ኢትዮጵያን ለማፍረስ በሚል መመስረታቸውን መስማታቸውንም አንስተዋል።

በጥምረቱ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአሸባሪነት በተፈረጀው ሕወሓት አቀናባሪነት ሲንደፋደፉ የታዩ ግለሰቦች ማየት ያሳዝናል ያሉት ሰብሳቢዋ የጥፋት ተልእኮ የያዘ ማንኛውም አይነት ጥምረት ፍፁም ተቀባይነት የለውም ብለዋል።

በዚህ ፈታኝ ወቅት ኹሉም ዜጋ በተለይም የቀድሞ የሠራዊት አባላትና የውትድርና ስልጠና ያላቸው ዜጎች ኹሉ ኢትዮጵያ ለምትጠይቀው ኹሉ ምላሽ ለመስጠት እንዲዘጋጁ መጠየቃቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

መግለጫው መንግሥት በጦርነቱ ምክንያት የተፈናቀሉ ዜጎችን መልሶ ለማቋቋም ቅድሚያ እንዲሰጥ ነው የጠየቁት።

የምክር ቤቱ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል አቶ የሺዋስ አሰፋ በበኩላቸው በአንዳንድ ምዕራባውያን በኩል በኢትዮጵያ ላይ በጭፍን ጥላቻ ጫና እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

ጫናው የሚያስከትለው ችግር ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለምሥራቅ አፍሪካ ጭምር የሚተርፍ መሆኑን ሊያውቁ ይገባልም ነው ያሉት።
ወቅታዊ ሁኔታውን ተገን በማድረግ ጸረ ኢትዮጵያ እንቅስቃሴ እያደረጉ ያሉ ግለቦችም ከድርጊታቸው መቆጠብ እንዳለባቸው ገልጸዋል።

የነጻነት ተምሳሌት የኾነችን ሀገር ለማፍረስ ጥረት ማድረግ ፍፁም ተቀባይነት የለውም ብለዋል።

የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት 53 የፖለቲካ ፓርቲዎችን በአባልነት ያቀፈ መሆኑ ይታወቃል።

ENA

Exit mobile version