Site icon ETHIO12.COM

ዓለም አቀፍ ተቋማትና ድርጅቶች የኢትዮጵያን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አክበረው መንቀሳቀስ እንደሚገባቸው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አሳሰበ

ባህርዳር: ሕዳር 02/2014 ዓ.ም (አማራ ኮሚዩኒኬሽን) የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል ዐቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤታቸውን የሳምንቱን የሥራ እንቅስቃሴ በተመለከተ ለሀገር ውስጥ እና ለዓለም አቀፍ ብዙኃን መገናኛ መግለጫ ሰጥተዋል።

የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ ጉዳዮች ኀላፊ እና በአሜሪካ የምሥራቅ አፍሪካ ልዩ መልእክተኛ አምባሳደር ጄፍሪ ፌልትማን ማነጋገራቸውን አምባሳደር ዲና ገልጸዋል፡፡

ቃል ዐቀባዩ በመግለጫቸው እንዳነሱት የአሜሪካ የምሥራቅ አፍሪካ መልእክተኛ ጄፍሪ ፌልትማን አዲስ አበባ በመገኘት ከኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ጋር ተወያይተዋል።

አቶ ደመቀ አሜሪካ ኢትዮጵያን ከአጉዋ ማገዷ እና የተለየ ጫና ማድረጓ ተገቢ እንዳልሆነ ለአምባሳደር ፌልትማን በማስረዳት አሜሪካ የሚገባትን የበሰለ እና የቆየ ዲፕሎማሲ ሁኔታን አንድትከተል ማስገንዘባቸው ተገልጿል።

በተመድ የሰብዓዊ መብት ኀላፊ ማርቲን ግሪፍት አዲስ አበባ ተገኝተው በአቶ ደመቀ ስለ ሽብርተኛው የትግራይ ወራሪ ኃይል ጥፋት ማብራሪያ ተሰጥቷቸዋል።

አቶ ደመቀ በማብራሪያቸው ትግራይ ክልል እርዳታ ጭነው ከገቡ 1 ሺህ 142 መኪኖች መካከል 242 ብቻ ተመልሰዋል ብለዋል። በዚህም ለሰብዓዊ ድጋፉ እንቅፋት ራሱ ሽብርተኛው የትግራይ ወራሪ ኃይል መሆኑን ገልጸውላቸዋል።

የፍትሕ ሚኒስትሩ ጌዲዎን ጢሞቲዎስ (ዶ.ር) እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን በወቅታዊ የሀገሪቱ ዲፕሎማሲ እና ሁኔታ ማብራሪያ እንደሰጡም በመግለጫው ተብራርቷል። በዚህም ዓለም አቀፍ ተቋማት የኢትዮጵያን ሕግ አክብረው እንዲንቀሳቀሱ አስረድተዋቸዋል።

በሕዝብ የተመረጠ መንግሥት የዜጎቹን ደኅንነት የመጠበቅ ግዴታ ስላለበት አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጁን እና ዓለም አቀፍ ተቋማትም ይህን ተገንዝበው ማክበር እንዳለባቸው ማብራሪያ ተሰጥቷቸዋል።

አንዳንድ ብዙኃን መገናኛ ተቋማት የተቀነባበረ ውሸት መረጃ የሚያሰራጩት ኾን ብለው ዓላማቸውን ለማሳካት እንደሆነ አምባሳደር ዲና በመግለጫቸው አንስተዋል። እነዚህ ብዙኃን መገናኛ ተቋማት ዓላማቸውን ከእውነት ጋር ሊያስታርቁ እንደሚገባ አሳስበዋል።

አምባሳደር ዲና እንደገለጹት በአፍሪካ ሕብረት የምሥራቅ አፍሪካ መልእክተኛ ኦሊሴጎን ኦባሳንጆ በተለያዩ ሁኔታ የእውነታ ፍለጋቸውን እያካሄዱ ነው። ከመቀሌ እስከ አፍሪካ ሕብረት እና አሜሪካ ድረስ እየተንቀሳቀሱ ሁኔታዎችን ለመገንዘብ እና ለማወቅ ጥረት እያደረጉ ነው ብለዋል።

ሰሞኑን ተመድ “ሠራተኞቼ ታሰሩብኝ” ብሎ ጥያቄ ማቅረቡን በተመለከተ ጥያቄ የተነሳላቸው አምባሳደር ዲና ሠራተኞቹ የተያዙት ሀገሪቱ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በመሆኗ የኢትዮጵያን ሕግ በመጣሳቸው ነው ብለዋል። ማንም ቢሆን ዓለም አቀፍ ተቋም ሠራተኛ ይሁን ነጋዴ ኢትዮጵያ ውስጥ እስካለ ድረስ የኢትዮጵያን ሕግ አክብረው መንቀሳቀስ አለባቸው ነው ያሉት፡፡ ያን ካላደረጉ ግን በጣሱት ሕግ አሁን ብቻ ሳይሆን በቀጣይም ይጠየቃሉ ሲሉ አሳስበዋል ።

ዘገባው፡- የአሚኮ ነው

Exit mobile version