Site icon ETHIO12.COM

“አጥፊዎቹ ለጥፋት ስምሪታቸው ሁሉንም ግብዓት ይጠቀማሉ፤ የሚሳሱለት ንብረት፣ ህይወትና እሴት የለም”

ትህነግ ብልጫ ያሳየባቸውን ጉዳዬች መረዳት ይገባል። ለጥፋት ስምሪታቸው ሁሉንም ግብዓት ይጠቀማሉ። የሚሳሱለት ንብረት፣ ህይወትና እሴት የለም።

By Yesuf Ibrahim (Haji Nesrellah)

ሀገራዊ ተቋማትን በመቆጣጠርና ሌሎቻችንን ገፍተው በማስወጣት ለአናሳ ስብስባቸው ጥቅምና አጀንዳ ማስፈፀሚያ ይገለገላሉ። በህዝብ ተሸንፈው ከስልጣን ሲባረሩና በልካችሁ ሁኑ፣ በልካችሁ ተዳደሩ ሲባሉ ጭረሽ አልተመቻቸውም፣ አሻፈረኝ አሉ! በሀገር መከላከያ፣ በደህንነት፣ በፋይናንስና በድፕሎማቲክ ተቋማት ውስጥ ሰርጎ በመግባት አሻጥር ይፈፅማሉ፣ ጥቃት ያደርሳሉ።

በዚህ መልኩ በሀገራዊ ተቋማት ላይ ጥርጣሬ እንዲኖረን በማድረግና ቅሬታዎችን ከአውድ ውጭ እያጣቀሱ በማራገብ ራሳችንን እንድናርቅ የሚገፋፉ ሴራዎችን ያቀናብራሉ።

በሂደት ጠላት ያንቀሳቀሰውን የሴራ ማሽን በውርስ ተቀብለን እንድናሾር ስልቶችን ይጠቀማሉ። ሙሉ ትኩረታችንን ከውልደት ጀምሮ የፀረ-አማራና ፀረ-ኢትዬጵያ ሀይሎች ማሰባሰቢያ ማዕከል በሆነው—በትህነግ ላይ እንዳናደርግ ከፋፋይ አጀንዳዎችን በመቅረፅና በማሰራጨት ጠርዝና ጠርዝ ይዘን ርስበርስ እንድንጓተትና ለጠላት ተጋላጭ እንድንሆን አበክረው ይሰራሉ።

ልቦለዳዊ ትርክት በመፃፍ ወደ ትግል የገባው ትህነግ በሂደት በርካታ ምልምሎቹን በማፍራት እላፊ ሀብትና ስልጣን ለማግኘት፣ በተቃራኒው እኛን ከልክ በታች ለማውረድና ለማዋረድ የተንኮል ስራ ሲሰራ ቆይቷል።

በኛ በኩል ሆነው ለጠላት አጋዥ የሆኑ ስራዎችን የሚያከናውኑ ሰዎች አሉ። የጠላት ሀይል ከንቱ ሀሳብ አንግቦ፣ የተራቆተ ሰብዓዊና ቁሳዊ ግብዓት አንጠልጥሎና አስቤዛውን ከኛ አድርጎ፣ በኛ ላይ ለመንገስ ድፍረት ያገኘው አዋዋላችንን፣ ውስጣዊ መስተጋብራችንን እንዲሁም ክፍተቶችን ስለተረዳ ብቻ ነው።

በዚህ ረገድ:-
1/ በጠላት ላይ ያለንን አቋም ከቃላት ትንተና ባለፈ በተግባራዊ ስምሪት፣ በፅናትና በመስዋእትነት ማረጋገጥ፣
2/ የምናስተጋባቸው የሀሳብ ልዩነቶች —በተዋጊው ሀይላችን ላይ አሉታዊ ተፅእኖ እንደማይፈጥሩ ማረጋገጥ፣
3/ የሀሳብ ልዩነቶቻችን— ተፈጥሯዊና ተናጠላዊ ወይስ ቡድናዊና የተናበቡ? የሚለውን ጥያቄ በድፍረት ማንሳትና መወያየት፣
4/ በጠላት ላይ ብቻ ሳይሆን “ወገንና አጋር” በምንለው ሀይል ዙሪያ ተመሳሳይ፣ ተቀራራቢ ወይም ቢያንስ በጋራ ሊያሰራ የሚችል ምልከታ መያዝ ይጠበቅብናል።

ነገር ግን ከዚህ ውጭ በየአቅጣጫው ያፈነገጠና በትግሉ ዙሪያ ያልተቀነበበ ምልከታ ይዘን የምንወስደው “የጋራ ስምሪት”—በተጀቦነ የትግል ማዕቀፍ ውስጥ ተመሳሳይ ዩኒፎርምና ጠመንጃ የተከማቸበት ብቻ ስለሚሆን—ድል ሊያጎናፅፈን አይችልም!

“ሴራ” የሚል ሀሳብ በተደጋጋሚ ይነሳል። ትክክል ነው። አሁን ሳይሆን ዱሮ የጀመረ ከባድ ችግር፣ ሀገራችንን ለዘመናት የተጣባ ተግዳሮት ነው። በጥቅሉ ጠላት በስንቅ፣ በትጥቅና በጀግንነት ብልጫ ኖሮት አይደለም። ግን ላቅ ያለ የሴራ ትስስር ፈጥሯል።

ትህነግ ራሱን የልዩ እውቀትና አቅም ባለቤት ለማስመሰል በርካታ የፈጠራ ተረኮችን አዘጋጅቶ ሲያሰራጭ ኖሯል። ብዙዎች እንዲያምኑትና እንዲቀበሉት አድርጓል። ይህ በሴራ ነው!

ህዝብን ለመከፋፈልና ለማዳከም የሚያስችሉ ሴራዎችን ተግባራዊ ሲያደርግ ቆይቷል። መከላከያ ሰራዊቱን በሰርጎ ገብነትና በሴራ አጥቅቷል። በሰራዊቱና በፖለቲከኛው ውስጥ የተረክ ተጋሪዎችና ነጭ ለባሽ ሴራ ፈፃሚዎች እንዳሉት በተደጋጋሚ የታየ ጉዳይ ነው።

ነገር ግን ሰራዊትና ፖለቲከኛ ስንል ምን ማለታችን ነው? ወገናቸውን ክደው ለጠላት የሚሰሩ የሰራዊት አባላትና የፖለቲካ አመራሮች እነማን ናቸው፣ የት ነው ያሉት?
ግን—ሰራዊት በትነውና ለጠላት አጋልጠው የጠፉና የሸሹ ሰዎች በመከላከያ ሰራዊቱ ውስጥ ብቻ ነው ያሉት? በመከላከያ ሰራዊቱ ውስጥ የነበሩና ያሉ የትህነግና የሸኔ ምልምሎች ጉዳይ ውሎ ያደረ ነው። ባጠቃላይ የሽብር ቡድኖችን በመደገፍ፣ ለትግራይ ተወላጆች፣ ለሸኔ አባላት፣ ለቅማንት ኮሚቴ አባላት፣ ለጉሙዝ ታጣቂዎች እንዲሁም ለሱዳን ሽፍቶች ጭምር በማገዝ በህዝብ ላይ ተደጋጋሚ ጥቃት የፈፀሙት ይታወሳሉ።

በመጨረሻ ጥቅምት 24 ላይ የመከላከያ ሰራዊታችንን ከውስጥና ከውጭ ተቀናጅተው በግፍ አርደዋል። የትግራይ ልሂቃን፣ ትህነግ እንደ ድርጅት፣ ሸኔን ጨምሮ ሁሉም የጥላቻ ሀይሎች እጃቸው በደም ተጨማልቋል። ከዛ በኋላ በተከታታይ በክህደት ተግባር የተዘፈቁ በርካታ አባላትና አመራሮች እንዳሉ ታውቋል።

ነገር ግን:-

ሀ/ ከሀዲ አባላትና አመራሮች የነበሩትና ያሉት በመከላከያ ሰራዊቱ ውስጥ ብቻ ነው? በልዩ ሀይሉና በሚኒሻው ውስጥ አልተገኙም? አሁንስ የሉም? ግንባር በትነው በጅምላ የሸሹ የሉም? እናንተን አይመለከትም አትዋጉ፣ ለቃችሁ ውጡ ያሉ የሉም?

የሴራ ቀለሙ ምን አይነት ነው?

ከፖለቲካ አመራሩ መካከል ክህደት የፈፀሙና ወገናቸውን ለጠላት አሳልፈው የሰጡ ሰዎች የሉም? የእኛን አርማ ይዘውና ካኔቴራ ለብሰው ለጠላት የተሰለፉ እኩያን አልተገኙም?

በተደጋጋሚና አበክረው “አማራ/ኢትዬጵያ” ሲሉ የነበሩ ሰዎች—ለወቅታዊ ፍጆታ አልሆኑንም በሚል—የትህነግን ፍላጎትና አጀንዳ— የጥርጊያ መንገድ ጥያቄ ለማስመሰል ጥረት አድርገዋል።

የወራሪው ሀይል አፈቀላጤ ጌታቸው ረዳ ደጋግሞ የተናገረውንና “ከአማራ ጋር ሂሳብ እናወራርዳለን፣ ኢትዬጵያን እናፈርሳለን” የሚለውን አቋም አሻሽሎ “ፍላጎታችን በትግራይ ላይ የተጫነውን አፈና ማስወገድ (to remove the siege of Tigray) እና አዲስ አበባ ገብተን አብይ አህመድን ማግኘት ነው” ያለውን ተቀብለው “የአማራ ህዝብ አይመለከተውም፣ ለትህነግ መተላለፊያ ኮሪዶር ይክፈት፣ ጦርነቱ በትህነግና በአብይ መንግስት መካከል ነው” ያሉትን በጎሪጥ ተመልክተናል፣ ታዝበናል። ሆኖም በወገናቸው ላይ የደረሰው ሰቆቃና ምስቅልቅል ባሳደረባቸው የስሜት ጫና እና ብስጭት ተገፋፍተው የተናገሩትንና የፃፉትን ለይተን እናውቃለን!

ያም ሆነ ይህ ሀሳቡ ትክክል አይደለም፣ ፍፁም ስህተት ነው! ቅድመ-ወረራ የነበረውን ትህነግ የአማራ ህዝብ ወዳጅ የማስመሰል አንድምታና ፍላጎት ያለው ስለሆነ ስህተት ይሆናል። በትህነግ አገዛዝ ዘመን የተፈፀመውን ግፍ የመካድ ዝናባሌ እንዳለው ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል።

የአማራ ህዝብ በአዲስ አበባና በአራት ኪሎ ዙሪያና አካባቢ የሚጠይቀውና የሚጋራው ፍላጎትና ድርሻ እንደሌለውና እንደማይገባው ስለሚያመላክት ስህተት ይሆናል።

“ትህነግ አሸንፎ አዲስ አበባ ይገባል፣ አራት ኪሎን ዳግም ይቆጣጠራል፣ የአማራ ኤሊትን ያጠፋል፣ ስለዚህ በአማራ ምትክና በአማራ ህዝብ ላይ በሹምባሽነት ስልጣን መያዝ አለብን” ብለው በሩቅ ሀገር የተሰደሩትን Mannequins አጀንዳ የሚደግፍ ይመስላል—ስህተት ነው!

ለማንኛውም የሴራ ጉዳይ ከተነሳ አድማሱ ሰፊ መሆኑን አብሮ መገንዘብ ይገባል! በዚህ የትግል ምዕራፍ ውስጥ ሆነን በሴራ ትንተና ልንዘናጋ አንችልም። ሴራ ካለ ይጋለጣል፣ ይታያል፣ ይነገራል፣ ይፃፋል። በንደትና በቁጭት የሚታወሰውን ያክል በኩራት የሚያጣቅሱት ይኖራሉ።

ነገር ግን—አሁን የሴራ ትንተና ያለው ፋይዳ እምብዛም ነው! በሴራ ትንተና የማገት ሴራ እምደሚኖርም መረዳት ያስፈልጋል!

በተቻለ ፍጥነት ጦርነቱን ማሳጠር ይገባል—ኢኮኖሚና ማህበራዊ ጫናውን ከመቀነስ በተጨማሪ ብዙ ነገሮች መስመር እንዳይስቱ ያደርጋል!

ሌላው ሁሉ ይደረስበታል፣ ዳይ ወደ ግንባር!
እዛው እንገናኝ!

Exit mobile version