Site icon ETHIO12.COM

ትህነግ በሚሌ እንዳልተሳካለት ፌልትስማን አረጋገጡ፤ “ለትህነግ ዛሬ 1983 እንዳልሆነ ነግረናቸዋል”

አዲስ አበባ ከርመው ወደ አገራቸው የተመለሱት የምስራቅ አፍሪካ የአሜሪካ ልዩ መልዕክተኛ አምባሳደር ጄፍሪ ፌልትማን አክራሞታቸውን አስመልክቶ ከወትሮው ለየት ባለ መልኩ የግንባሩን ሚዛን አካተው ከመገናኛ ሰዎች ለተሰነዘረላቸው ጥያቄዎች ማብራሪያ ሰጥተዋል። ይፋ በሆነው የፕሬስ መግለጫ እንደተመለከተው ትህነግ በሚሌ ግንባር መመታቱን አረጋግጠዋል። በሸዋ ሮቢት በኩል ማቅናቱንም ገልጸዋል። ከዛ በላይ ግን ” ዛሬ 1983 አይደለም” ብለው እንደነገሯቸውም አመልክተዋል።

በሚሌ ግንባር የጅቡቲን መንገድ ለመቆጣጠር ትህነግ ያደረገው ሙከራ የሚፈለገውን ያህል መግፋት እንዳልቻለ፤ የአገር መከላከያ ሰራዊትና ስሙን ሳይተቅሱ ” አጋር” ያሉት የአፋር ሃይል በጥምረት እንዳሸነፉትና በዚያ በኩል የሚሆን ነገር እንደሌለ በይፋ አመልክተዋል። ትህነግ ሚሌን መቆጣተሩን በመግለጽ ለደጋፊዎቹን ለውጭ ሚዲያዎች ሲያራግብ የነበረው ሁሉ ፍጹም ሃሰት እንደሆነ ” ከፈረሱ አፍ” እንደሚባለው አምባሳደሩ ግልጽ አድርገዋል። በዛ በኩል ያልተሳካለት ሃይል በከሚሴ ወደ ሸዋ ሮቢትና ደብረሲና ማቅናቱ ጠቁመዋል።

እሳቸው አዲስ አበባን ከለቀቁ በሁዋላ አዲስ ጥቃት በሁሉም አቅጣጫ መከፈቱን መንግስት ይፋ ማድረጉን ተከትሎ ሸዋ ሮቢት ነጻ መውጣቷንና የትህነግ ሃይል ተቆርጦ መሃል መግባቱ ተገልጿል። የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጽህፈት ቤትም ዛሬ ማለዳ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ግንባር ካመሩ በሁዋላ በርካታ ድሎች መመዝገባቸውን ይፋ አድርገዋል። የአፋር ሚዲያዎች ” ሰበር ዜና” ሲሉ ” ከአፋር ሰሙሮቢ የተነሳው የአፋር ህዝባዊ ሰራዊት በሸዋሮቢት ጁንታውን ቆርጠዋል። ወደ ደብረሲና አልፎ የነበረው ጁንታ በአራት አቅጠጫ እየተቀጠቀጠ ነው” ሲሉ አስታውቀዋል። ከዛም በሁዋላ ማጥቃቱ ቀጥሎ ከፍተኛ ሰብአዊ ቀውስ እንደደረሰ ተመልክቷል። በሌላ ግንባርም ላሊበላና ዳሸና ነጻ መውጣታቸውን ተከትሎ ወደ ወልደያ እየገፋ ያለው ሃይል ድል እንደቀናው የአብን አመራር አቶ ዩሱፍ ኢብራሂም አመልክተዋል።

“በሴራ የተካኑ” የሚባሉት ፌልትስማን ሃላፊነቱን እንደተቀበሉ ኢትዮጵያንና መንግስቷን በቃለለ መልኩ በሰጡት መግለጫ ሳቢያ መንግስት አጻፋውን መልሶ አቋማቸውን እንዲያሻሽሉ ነገሯቸው ነበር። በዚሁም ምክንያት ጠቅላይ ሚኒስተር አብይ እንዳላገኙቸው ተጠቁሞ ነበር።

አሁን ላይ እሳቸው ራሳቸው እንዳሉት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይን አግኝተዋቸዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ትህነግን ከወረራቸው ስፋራዎች ማስለቀቀ ቀዳሚ ኢላማቸው እንደሆነ በግልጽ እንደነገሯቸው አመልክተዋል። የአዲስ አበባው ጉዞ እንደምያሳካ የገባቸው አምባሳደሩ ህወሓት ከ30 ዓመት በፊት የወቅቱ የኢትዮጵያ መሪ መንግስቱ ሃይለማርያምን አስተዳድር በትጥቅ ትግል ከስልጣን ያነሳበትን መንገድ አሁን ለመድገም ማሰብ እንደማይገባውና ይህንንም በደንብ አድርገው እንዳስረዷቸው አመልክተዋል።

“የህወሓት አመራሮች የአሁኑን ወቅት እንደሚረዱ ተስፋ አደርጋለሁ፣ ይህ 1983 ዓ.ም አይደለም ሁኔታዎቹን እንዲረዱም ለህወሃት ነግረናቸዋል” ያሉት አምባሳደር ፊልትማን፤ አዲስ አበባን መያዝ ቀደም ሲል ከነበረው ጋር ፍጹም ልዩ መሆኑንን አስረግጠው ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ህወሃት በትግራይ ክልል የነበረውን ሀገር መከላከያ የሰሜን እዝን ማጥቃቱን፣ የጠናጠል ተኩስ አቁም ተደርጎ ሰራዊቱ ከትግራይ መውጣቱን እና የፌደራል መንግስት በክልሉ ላሉ ተጎጂዎች እያደረገ ያለውን የሰብዓዊ መብት ድጋፎችን አሜሪካ እውቅና እንድትሰጥ እንደሚፈልጉም አምባሳደር ፌልትማን ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር በነበራቸው ውይይት ወቅት መስማታቸውን አክለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ባለፈው ሰኔ እና መስከረም ወራት ላይ በተደረገ ምርጫ ተመርጠዋል ያሉት አምባሳደሩ “የአሜሪካ ፍላጎት ለ27 ዓመት በስልጣን ላይ የነበረውን ህወሓት መራሽ ኢህአዴግን ወደ ስልጣን መመለስ አይደለም” ብለዋል። “ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ሕጋዊ እና በምርጫ የተመረጡ መሪ ለመሆናቸው እውቅና እንሰጣለን፣ ይሁንና አሜሪካ በሰሜኑ የኢትዮጵያ ጦርነት ዙሪያ ለየተኛውም አካል ውግንና የላትም” ሲሉም ከጋዜጠኞቹ ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ ሰጥተዋል።

“የአሜሪካ ፍላጎት ጦርነቱ በቀጠለ ቁጥር ወደ ችግር የሚገቡ ዜጎች ቁጥር ይጨምራል የሚል እና የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ይጨምራሉ እንዲሁም ሌሎች ያልተጠበቁ የኢትዮጵያን አንድነት የሚጎዱ ችግሮች ይከሰታሉ የሚሉ ስጋቶችን ለመከላከል ነው” ብለዋል አምባሳደሩ።

በኢትዮጵያ ቆይታቸው ወደ ጦርነት የገቡት አካላት ወደ ስምምነት እንዲመጡ በአዲስ አበባ እና በጎረቤት ሀገራት ካሉ አመራሮች፣ዲፖሎማቶች እና ሌሎች ጉዳዩ ይመለከታቸዋል ከተባሉ አካላት ጋር መወያየታቸውንም ተናግረዋል። አምባሳደሩ በተናጠል ከሁለቱም አካላት ጋር መወያታቸውን ተናግረው ሁለቱም ወገኖች ጦርነቱን እንደሚያሸንፉ እንደነገሯቸውም ጠቅሰዋል::

ይህ እንዳለ ሆኖ ግን የህወሃት ሀይሎች እና የፌደራል መንግስት ወደ ስምምነት ለመምጣት ፍላጎት እንዳላቸው ነግረውኛል ያሉት አምባሳደሩ ችግሩ ቀድሞ ማን ይጀምር የሚለው ነው ሲሉም አክለዋል።

ጦርነቱ አሁንም በመቀጠሉ ምክንያት ከመኖሪያ ቤታቸው የተፈናቀሉ ዜጎች ቁጥር እየጨመረ ነው ሁለቱማ አካላት ግን ለተጎጂዎች የሰብዓዊ ድጋፎች እንዲደርሱ ማድረግ እንዳለባቸውም ገልጸዋል።

Exit mobile version