Site icon ETHIO12.COM

“ የትግራይ ወራሪ ከመሸሹ በፊት ሴቶችና ሕፃናትን ጨፍጭፏል፤ካሳጊታና ሙዴና ከተሞችን አውድሟል” ተባለ

አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ኀይል በካሳጊታ እና ሙዴና ከተሞች በወገን ጦር ተመቶ ከመሸሹ በፊት ሴቶችና ሕፃናትን ጨፍጭፏል፥ ንብረትም አውድሟል፡፡

የአሸባሪው የትግራይ ወራሪ ኀይል በአፋር ክልል ካሳጊታ እና ሙዲና ከተሞች በወገን ጦር ተመትቶ ከመሸሹ በፊት በርካታ ሕጻናትና ሴቶችን ጨፍጭፏል፤ ንብረትም አውድሟል፡፡

በኢፌዴሪ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ የሚመራው መላው የጸጥታ ኀይል በካሳጊታ ግንባር አሸባሪውን የትግራይ ወራሪ ኀይል አይቀጡ ቅጣት በመቅጣት ስትራቴጂካዊ ስፍራዎችን ማስለቀቁ ይታወቃል፡፡

የጸጥታ ኀይሉ ቡርቃንና በባቲ ከተማ ዙሪያ ያሉ ተራሮችን ተቆጣጥሮ ወደ ባቲ ኮምቦልቻ እየገሠገሠ መሆኑንም ትናንት ማምሻውን የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት መግለጹ ይታወሳል፡፡

የኢዜአ ምንጮች እንዳረጋገጡት አሸባሪ ቡድኑ በካሳጊታ እና ሙዲና ከተሞች የወገን ጦርን መቋቋም አቅቶት ከመሸሹ በፊት በርካታ ሕፃናትን እና ራሳቸውን መከላከል የማይችሉ አቅመ ደካሞችን ጨፍጭፏል፡፡ መስጂዶችን አውድሟል፤ ቁራዓን ሰብስቦ አቃጥሏል፡፡

የዜጎች ጥሪቶች የሆኑ ቤቶች፣ ሱቆች፣ ምግብ ቤቶች፣ ጤና ጣቢያዎች፣ ትምህርት ቤቶች እና የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማቶችን በከባድ መሳሪያ በመምታትና በእሳት በማቃጠል አውድሟል።

አሸባሪ ቡድኑ የዜጎችን ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊና ምጣኔ ሃብታዊ መሰረተ ልማቶች በማውደም ለሰው ልጆች የማይበጅ አረመኔያዊ ቡድን መሆኑን በተግባር አረጋግጧል።

አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ኀይል በወገን ጦር እየደረሰበት ያለውን ምት መቋቋም አቅቶት የያዘውን ሁሉ እያዝረከረከ በመፈርጠጥ ላይ ይገኛል።

የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ዛሬ በሰጠው መግለጫ ሽንፈት ገጥሞት በመፈርጠጥ ላይ የሚገኘው የአሸባሪው የትግራይ ወራሪ ኀይል እያወደመና እየዘረፈ እንዳይሄድ ኅብረተሰቡ አካባቢውን እንዲጠብቅ ጥሪ ማቅረቡ ይታወቃል፡፡

ሕዳር 18/2014 ዓ.ም (አሚኮ)

Exit mobile version