Site icon ETHIO12.COM

የኢትዮጵያ አየር መንገድ “ለ1 ሚሊየን ወደ አገር ቤት” ዘመቻ ተሳታፊዎች የ30 በመቶ የዋጋ ቅናሽ አደረገ፤ ቅድመ ዝግጅቱ ቀጥሏል

የኢትዮጵያ አየር መንገድ “ለ1 ሚሊየን ወደ አገር ቤት” ዘመቻ ለሚሳተፉ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የ30 በመቶ የዋጋ ቅናሽ አደረገ።በቅናሹ ተጠቃሚ የሚሆኑት ከዛሬ ጀምሮ እስከ ፈረንጆቹ ታህሳስ 20 ቀን 2021 ድረስ ትኬት የሚቆርጡና፥ ከፈረንጆቹ ጥር 1 እስከ 31 ቀን 2022 ድረስ ወደ ኢትዮጵያ የሚጓዙ የዘመቻው ተሳታፊ መንገደኞች መሆናቸውን አየር መንገዱ በትዊተር ገጹ አስታውቋል።

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና የኢትዮጵያ ወዳጆች “የ1 ሚሊየን ወደ አገር ቤት” ዘመቻ ተሳታፊ እንዲሆኑ ጥሪ ማቅረባቸው ይታወሳል።ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው ባስተላለፉት ጥሪ የፈረንጆቹን አዲስ ዓመት በኢትዮጵያ ለማክበር ይፋ የሆነውን 1 ሚሊየን ዳያስፖራ ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች ወደ አገር ቤት እንዲገቡ የማድረግ ጥሪን እንዲቀበሉ ጠይቀዋል፡፡

በተያያዘ ዜና በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ 1 ሚሊየን ዳያስፖራ ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች ወደ አገር ቤት እንዲገቡ የቀረበውን ጥሪ ተከትሎ የቅድመ ዝግጅት ስራ እያከናወነ መሆኑን የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ አስታወቀ፡፡

ኤጀንሲው የዳያስፖራ ጉዳዮችን እንዲያስተባብር በማቋቋሚያ ደንቡ ሃላፊነት እንደተሰጠው የኤጀንሲው ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መሐመድ እንድሪስ ዝግጅቱን አስመልክቶ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ዳያስፖራው ካለበት አገር ጀምሮ ኢትዮጵያ እስከሚገባ ድረስ እንዲሁም በቆይታው ወቅት ስለሚኖሩ ሁነቶችና መከናወን ስላለባቸው ጉዳዮች የቅድመ ዝግጅት ስራዎችን በማከናወን ላይ እንደሚገኝም ተናግረዋል።

ዳያስፖራው በስፋት በሚኖርባቸው አገራት ባሉ ኤምባሲዎችና በአገር ቤት ካሉ ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት ለመስራት የሚያስችል ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም አብራርተዋል።

ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ለኢትዮጵያውያን፣ ትውልደ ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች ባስተላለፉት መልዕክት ኢትዮጵያ ለሚወዷት ደማቅ አቀባበል ለማድረግ ዝግጁ መሆኗን ጠቅሰዋል፡፡

ዳያስፖራው ይህን አጋጣሚ ተጠቅሞ በስፋት ወደ አገር ቤት በመምጣት በኢትዮጵያ ላይ ዲፕሎማሲያዊና ኢኮኖሚያዊ ጫና ለመፍጠር በመንቀሳቀስ ላይ ላሉ አካላት ግልጽ መልዕክቱን በድጋሚ እንዲያስተላልፍ ጥሪ ማቅረባቸውን ከኤጀንሲው ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

Exit mobile version