Site icon ETHIO12.COM

እሸቴ ሞገስ – የጸና ቃላቸውን እንደጠበቁ ለሀገር ክብር ታግለው ወደቁ

ኢትዮጵያ የጀግኖች መፈጠርያ የሀገር ወዳዶች መኖርያ ምድር ናት። በጀግኖቿ ብርቱ ክንድ ነጻነቷን አስጠብቃ ቀጥላለች።

የቅኝ ግዛትን ክፉ ህልም አምክናለች። “በባርነት መኖር” ይሉትን የክፉዎችን ምኞት እንደማይሳካ በተግባር አሳይታለች።ከትናንት እስከ ዛሬ ያለው የታሪክ ማኅደሯ ሲገለጥ የሚያሳየው ለክብሯ የተዋደቁ እልፍ አዕላፍ ጀግኖች እንደነበሯት ነው። አሁንም ጀግኖችን እየተፈጠሩ ነው፡፡ ግርማቸው እንደ አንበሳ፣ቁጣቸው እንደነብር ፣ሲወዱ የሚያኮሩ፣ሲቆጡ የሚያስፈሩ ነበልባል ጀግኖች የት ይገኛሉ ለሚል መልሱ ኢትዮጵያ ነው።

ባህር አቋርጦ የመጣን ወራሪ ቅስሙን ሰብረው የሚመልሱ፣ጠላትን እንዳራሙቻ ነቃቀለው የጣሉ ጀግኖች አባቶች ነበሩባት ፣ዛሬ ደግሞ ልጆች ተተኩበት። “ነብር ዥንጉርጉርነቱን ኢትዮጵያዊ መልኩን አይቀይርም” እንዲሉ ዛሬም የኢትዮጵያ ማህጸን ጀግኖችን ማፍራቱን ቀጥሏል።ባንዳውና አሸባሪው ትህነግ ኢትዮጵያዊያን ላይ የከፈተው ጦርነት በጀግኖች ብርቱ ክንድ እየመከነ አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድንም ሽንፈቱን እየተከናነበ ይገኛል።ከነዚህ በተለያዩ አካባቢዎች ጎልተው ከሚያንጸባርቁ እልፍ አዕላፍ የጀግንነት ታሪኮች አንዱ የጀግናው የእሸቴ ሞገስና የልጃቸው ይታገሱ የጀግንነት ታሪክ ይገኝበታል።

እሸቴ ሞገስ ትውልዳቸው ቀወት ወረዳ ማፉድ ሳርአምባ አካባቢ ሸዋሮቢት ከተማ ቤተሰብ መስርተው በንግድ ይተዳደሩ ነበር። ገና በ15 ዓመታቸው ክላንሽኮቭ ጠመንጃ ታጥቀው ያደጉት እሸቴ በአካባቢው ማህበረሰብ ዘንድ በጀግንነታቸው ይታወቃሉ። በሕዳር ወር አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን ወደ አጣየ ሲጠጋ እሸቴ የአካባቢው ጀግኖች አብረዋቸው እንዲፋለሙ ጠየቁ፡፡ ጽኑ አቋማቸውንም ነገሯቸው። “ሸዋሮቢትን ጥየ የትም ንቅንቅ አልልም በጀግንነት ተፋልሜ የክብር ሞቴን እሞታለሁ እንጅ” አሏቸው። “እኛ ልጆቿ ትተናት ከሄድን ለሸዋሮቢት ማን ዘብ ሊቆምላት ነው”ነበር ያሏቸው።

ጀግና ቃሉን ያከብራል።ከቃሉ ዝንፍ አይልም።እሸቴም ቃላቸውን አክባሪ ያሰቡትን ተግባሪ ጀግና ነበሩና ወራሪዎችን ለመፋለም አስቀድመው አዘጋጅተውት ከነበረው ምሽግ ውስጥ ኾነው ሸዋሮቢትን የወረራትን የጥፋት ቡድን በጀግንነት ተፋለሙ። በዚህ መሀል ነበር እናቱ “ባጠባውህ ጡቴ ይሁንብህ ብለው ሸዋሮቢትን ያስለቀቋቸው። የእናታቸውን ቃል አክብረው ወደ ሳላይሽ ሄዱ።ወራሪ ቡድኑም ሳላይሽ ደረሰ። እሸቴ ሞገስም አካባቢውን ለቀው እንዲሸሹ ተመከሩ።ነገር ግን ከዚህ በኋላ መሸሽን አልፈለጉም።

ለቃላቸው ሟች የሆኑት ጀግናው እሸቴ ወራሪ ቡድኑን በጀግንነት ተፋለሙት። ከልጃቸው ይታገሱ ጋር ሆነው ዘጠኝ የጠላት ቡድን አባላት በጥይት ረፈረፏቸው።ግንባር ግንባራቸውን በረቀሷቸው።ተኩሰው የማይስቱት እሸቴ ወደ ጠላት የተኮሷት ጥይት አንዷም ያለ ግዳይ መሬት ላይ አልወደቀችም።የአባቱ ልጅ የሆነው ልጃቸው ይታገስም ከአባቱ ጎን ተሰልፎ ጠላትን ያረግፈው ይዟል።በዚህ መሀል ነበር ልጃቸው ይታገስ እሸቴ በጥይት ተመትቶ ህይወቱ ያለፈው።

ጀግናው እሸቴ በልጃቸው ህልፈት ቢያዝኑም ልጃቸው የተሰዋው የጀግና ሞት መሆኑን ስለተረዱ አስከሬኑን ከማንሳት ይልቅ ከጠላት ጋር መዋደቅ ቀጠሉ። ጠላትን ስለመደምሰስ ብቻ አሰቡ። በዚህ መሀል ለእህታቸው ባል ደውለው ጠላትን እየረፈረፉ እንደሆነና ልጃቸውን እንደገደሉባቸውና እሳቸውም ከልጃቸው ጎን ለሀገራቸው ታምነው እንደሚሰው ተናግረዋል።

“አዳምጠኝ ይታገስን ገደሉብኝ ይሰማሀል በደንብ ያዝልኝ የሞተው የትጋ መሰለህ እኔም አሁን ከሬሳው ጋር ነኝ ከበውኛል።እዚያው ነው የምሞተው አሰፋ ታየ ቤት ከታች በኩል የእሱ ማሽላ አለ በኋለኛው በር ሬሳችን እዚያው ነው የሚሆነው መዝግብ በኋላ ይሄን በሰማይ ነው የምከፍልህ ዘጠኙን ገድለን እኛ በመጨረሻ ወደ ማሽላው ስንሸራተት መቱብኝ አላለቅስም” ሲሉ ነበር መልዕክታቸውን ያስተላለፉት፡፡

የእህታቸው ባልም አካባቢውን ለቀው እንዲወጡ ጎትጉቷቸው ነበር።ይሁን እንጅ ጀግናው ለቃላቸው ጸኑ።

ጀግኖች ኢትዮጵያዊያን ጽናት መለያቸው ነው።ጊዜያዊ ችግር በሀገራቸው ላይ ፊታቸውን እንዲያዞሩ ሊያደርጋቸው አይችልም። የባንዳ “አሸሸ ገዳዎ” አያስበረግጋቸውም። ሀገር ወዳድ ጀግኖች እንደ ባንዳ እስስታዊ ባህርይ የላቸውም።ወቅቶችን እያዩ የደመቀበት ከሚመስላቸው ጋር ራሳቸውን እየቀያየሩ የሚኖሩ ፈሪዎች አይደሉም።ምርጫቸው አንድ ብቻ ነው።ኢትዮጵያ ወይም ሞት።ይህ ድፍረታቸው እና ለሀገር ክብር ያላቸው ቆራጥነት የባንዳን ልብ በፍርሀት ያርዳል፣ያርበደብዳል፣ ሀገር የማፍረስ ተስፋውን ቅዥት ያደርጉታል። ጀግናው እሸቴም በቃላቸው ጸኑ፡፡

ጀግናው ከዚህ በኋላ ከጠላት ጋር ተፋልመው ለሀገራቸው ታምነው በክብር ከልጃቸው ጋር ተሰውተዋል። ውድ መስዋእትነት ለሀገራቸው ክብር ከፈሉ።የጀግኖች አባቶችን የታሪክ ፈለግ ተከተሉ። አስፈሪ የነበረውን ሞትን ንቀው “ከመቃብር በላይ” የሆነውን የክብር ሞት ሞቱ። ለኢትዮጵያ ለክብሯ ሲሉ የወደቁትን እልፍ አእላፍ ጀግኖች መንገድን ተከተሉ። የጀግኖችን የጀግንነት ደማቅ ታሪክ ተጋሩ።መላው ኢትዮጵያዊያንም በጀግንነታቸው ኮሩ።

ጀግናው እሸቴ ልጆቻቸውን የኢትዮጵያ ሕዝብ እንዲያሳድጋቸው ከመሰዋእታቸው በፊት ባደረጉት የስልክ ልውውጥ አደራ ብለዋል። የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፋለ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው “እሸቴ ሞገስ በጀግንነት ሲፋለም መስዋእት እንደሚሆን እርግጠኛ ኾኖ ለመንግሥት ቤተሰቦቹን አደራ ብሏል፤ እኛም የጀግኖቻችንን፣ የእሸቴዎችን አደራ በፍጹም አንረሳም፤ የሰጡንን አደራ ተቀብለን ለህልውናችን እስከ መጨረሻው መስዋእትነት እንታገላለንም ነው” ያሉት።

ጀግና ሞተ አይባልም። ሥራቸው ከመቃብር በላይ ደምቆ፣ ታሪካቸው በእያንዳንዱ ልቦና ውስጥ ዘልቆ ለዘላለም ይኖራልና። ክብር ለጀግኖቻችን ይሁን።

በፈረደ ሽታ – (አሚኮ)

Exit mobile version