ʺጎንደር፣ ጎጃም፣ ሸዋ፣ ወሎ ሙሉ አማራ፣ የጎበዝ ሀገር ነው ሞረሽ ብለህ ጥራ”

ሞረሽ ብለህ ጥራቸው እሳት ለብሰው እሳት ጎርሰው ይነሱልሃል፣ ሞረሽ ብለህ ጥራቸው እንደ ነብር ተቆጥተው፣ እንደ አንበሳ አግስተው ይመጡልሃል፣ በአፋፉ ዘልቀህ ንገራቸው እየበረሩ ይደርሱልሃል፣ የአተኳኮስ ዘዴውን፣ የአጣጣል ብልሀቱን ያሳዩሃል፡፡

ሞረሽ ብለህ ላክባቸው ሀገር ስትነካ ያማቸዋል፣ ወገን ሲደፈር ያንገሸግሻቸዋል፣ ሞረሽ ብለህ ጥራቸው ያቀረቡትን ማዕድ ሳይጨርሱ አቋርጠው፣ የተመቸ ሕይወታቸውን ረስተው ሲከንፉ ይመጡልሃል፡፡ ሞረሽ ብለህ ጥራቸው መውዜራቸውን ወልውለው፣ ክላሹን አሰናድተው፣ ካዝናቸውን ሞልተው፣ ሳንጃቸውን ስለው አቤት ይሉሃል፡፡

ጨለማ አይበግራቸውም፣ ብርድ አይመልሳቸውም፣ ረሃብና ጥም አይፈታቸውም፣ የጠላት ጥይት አያሸብራቸውም፣ እሾህና አሜካላው ከግስጋሴያቸው አያስቆማቸውም፡፡ ሞረሽ ብለህ ጥራቸው ተራራውን ወጥተው፣ ቁልቁለቱን ወርደው፣ ሜዳውን ተረማምደው፣ ሸለቆውን አቆራርጠው ድረሱ በተባሉበት ይደርሳሉ፣ ተገኙ በተባሉበት ይገኛሉ፣ አድርጉ የተባሉትን ያደርጋሉ፡፡

ምሽግ ማፍረስ፣ ጠላት መመለስ፣ አልሞ መተኮስ ከእነርሱ በላይ ላሳር ነው፡፡ የጦር መምጫውን፣ ድል ማድረጊያውን፣ የአተኳኮስ ዘዴውን አሳምረው ያውቁበታል፣ ኢትዮጵያ ተነክታለች፣ እምዬ ተወራለች በላቸው ሳይውሉ ሳያድሩ ይደርሳሉ፡፡

አደራ የተቀበሏትን ሀገራቸውን፣ ተከብራ የምትኖር እናታቸውን አያስደፍሯትም፡፡ በሞታቸው ሞትን ድል ያደርጋሉ፣ በአጥንታቸው ሀገርን ያጸናሉ፣ በደማቸው መሠረት እናታቸውን ያስከብራሉ፡፡ ጀግኖች መከራውን ይሻገሩታል፣ ጀግኖች የክፉ ቀን መውጫውን ያውቁታል፣ ጀግኖች ማዕበሉን በኃይላቸው ያልፉታል፣ ድቅድቅ ጨለማውን ያበሩታል፡፡ እንደ ተራራ የገዘፈውን ችግር ይሰባብሩታል፣ የተከመረውን ይንዱታል፣ ያበኑታል፡፡

ጀግኖች ኢትዮጵያን አስከብረዋታል፣ ጠላቶቿን ቀጥተውላታል፣ የአባቱን ጋሻ ልጁ እያነሳ፣ አባቱ ያስከበራትን ልጁም አስከብሯታል፣ የተዋደቀላትን ልጁም ተዋድቆላታል፡፡ ኢትዮጵያ ጀግኖችን ትወልዳለች፣ ኢትዮጵያ ጀግኖችን ትፈጥራለች፣ ኢትዮጵያ ጀግኖችን በየዘመናቱ ታበቅላለች፡፡ በስሜን የመጡት በጀግና ልጆቿ ተመልሰዋል፣ በምዕራብ የመጡት በጀግና ልጆቿ ተመትተዋል፣ በምሥራቅ የመጡት በአይደፈሬ ልጆቿ ተደምስሰዋል፣ በደቡብም የመጡት ባዶ ቀርተዋል፡፡ በየዘመናቱ የተነሱት ሁሉ ተመትተዋል፡፡ በአራቱም ንፍቅ የኢትዮጵያ ጀግኖች ሀገራቸውን አያስነኩም፡፡ አያስደፍሩም፣ ከሰው ወሰን ደርሰው አይገቡም ከገቡባቸው ግን አይምሩም፡፡

የአማራ ጀግኖች ለሀገራቸው ሞተዋል፣ ለሀገራቸው ቆስለዋል፣ ለሀገራቸው ደም አፍስሰዋል፣ ለሀገራቸው ሲሉ ደረታቸውን ለጦር፣ እግራቸውን ለጠጠር ሰጥተዋል፡፡ ስለ ሀገር የሚሠራውን አብዝተው ይወዱታል፣ በሀገር ላይ የሚነሳን አምርረው ይጠሉታል፣ ጠልተውም ዝም አይሉትም፣ ይቀጡታል፣ ይመቱታል እንጂ፡፡

See also  ውሃና ኢነሪጂ ሚኒስተር -ክልሎች አምስት ቢሊዮን ብር ወስደው ከለከሉኝ

በክብር፣ በሀገር፣ በኢትዮጵያዊነት ለሚመጣ ምረት የላቸውም፡፡ ከኢትዮጵያዊነት ማማ ዝቅ የሚያደርጋቸው፣ ከአንድነታቸው የሚነጥላቸው፣ ከከፍታ የሚገፋቸው በተነሳ ቁጥር አሳምረው ቀጥተውታል፡፡ የአማራ ጅግኖች ለሠንደቅ ክብርና ለሀገር ፍቅር ሲሉ መስዋዕት ይኾናሉ፡፡ ሀገር በየትኛውም ጫፍ ትነካ ሲበሩ ይደርሳሉ፣ ከወንድሞቻቸው ጋር ኾነው ጠላትን ድባቅ ይመታሉ፣ አሳፍረው ይመልሳሉ፡፡

ለሀገር መሞት ክብርና ኩራት መኾኑን ጠንቅቀው ያውቃሉ፣ አባትና እናት የሰጣቸውን የሀገር ቃል ኪዳን ያከብራሉ፣ ይጠብቃሉ፣ ኢትዮጵያ ከምንም በላይ ናት፣ ኢትዮጵያ አይነኬ ናት ይላሉ፡፡ ስለ ጀግንነታቸው የኢትዮጵያ ተራራዎች፣ ሸለቆና ሸንተረሮች ይመሰክራሉ፡፡ ጠላቶች ሳይቀር ስለ አማራ ጀግኖች ጀግንነት ይናገራሉ፡፡ ምንም ሞት ቢደረደር ኢትዮጵያ ከተነካች ፍንክች የለም፡፡

ቃላቸውን ያከብራሉ፣ እስከ መቃብር ድረስ ይታመናሉ፣ ለሀገር ቢያልፉ እንኳን የማይሻር ቃል ኪዳን ለልጅ አስረው ይሄዳሉ፡፡ ኢትዮጵያን በአጥንትህ አስከብራት፣ በደምህ አጽናት፣ በሞትህ ሞቷን ሙትላት፣ ዝቅ ብለህ ከፍ አድርጋት፣ ተርበህ አጥግባት፣ ተጠምተህ አጠጣት፣ ታርዘህ አስውባት ይላሉ፡፡ አርቆ አሳቢነት፣ ጀግንነት፣ ትዕግሥት፣ ጽናት፣ ኢትዮጵያዊነት፣ ሥራ ወዳድነት፣ የጦር ስልት እና አይደፈሬነት ከእነርሱ ጋር ናት፡፡

ወዳጃቸውን አቅፈው ይቀበላሉ፣ አንጥፈው ያሳርፋሉ፣ ስሞት አፈር ስኾን እያሉ ያጎርሳሉ፣ ጠላታቸውን አስቀድመው ተመከር ተው ይላሉ፣ እንቢ ያለ ጊዜ ደግሞ ተመልከት ብለው ይማታሉ፡፡ በውስጥም በውጭም የተነሱ ጠላቶች ይፈሯቸዋል፣ ጀግንነታቸው ወደር የለሽ መኾኑን ያውቃሉና ይርበተበቱላቸዋል፡፡ በኢትዮጵያ የተነሳው ጠላት ሁሉ የእነርሱን ክንድ ቀምሷልና ጠላት አብዝቶ ይጨነቃል፡፡ ኢትዮጵያ ዛሬም ሌላ ተነስቶባታል፣ በምድሯ የተነሳው ጠላት ደግሞ የመጀመሪያው ጠላቴ አማራው ነው ብሏል፡፡ አሸባሪው ትህነግ ስለ አማራ ጠላትነት ለትውልድ ሁሉ ነግሯል፣ ስለ አማራ ጠላትነት መዋቅር አበጅቷል፣ ስለ አማራ ጠላትነት ሕግ አርቅቋል፣ ግጥም ገጥሟል ዜማ ደርሷል፡፡

ትህነግን የሚደግፉት ሁሉ አማራን እንዲጠሉ አድርጓቸዋል፡፡ ዳሩ አማራ በጥላቻ አይሰበርም፣ ለጠላት አይንበረከክም ሊያጠፉት የፈለጉትን ያጠፋቸዋል፣ ሊገፉት የፈለጉትን ይጥላቸዋል እንጂ፡፡ ትህነግ ዛሬም በአማራ ላይ ጦርነት ከፍቷል፡፡ ትናንት የገደላቸው ንጹሐን፣ ትናንት ያጠፋው፣ የዘረፈው ሃብትና ንብረት ሳይሽር ድጋሜ መጥቷል፡፡ ለዳግም ወረራና ዝርፊያ የመጣውን የትህነግ ጀሌ ጀግኖች እንደ አመጣጡ እየመለሱት፣ እንደ አቀራረቡ እያስተናገዱት ነው፡፡ አማራን ጠልቶና አንገት አስደፍቶ፣ በአፋርም ዘምቶ ኢትዮጵያን አሳንሳለሁ ያለውን ጀግኖች ከዳር ዳር እየተጠራሩ እየዘመቱበት፣ በባሩድ እየቆሉት፣ በክንዳቸው እያደቀቁት ነው፡፡

See also  ኢትዮጵያና ሶማሊላንድ የበርበራ ወደብን አልምቶ የመጠቀም ስምምነታቸውን አጸኑ

ʺጎንደር፣ ጎጃም፣ ሸዋ፣ ወሎ ሙሉ አማራ፣
የጎበዝ ሀገር ነው ሞረሽ ብለህ ጥራ” የጎበዝ ሀገር ነው ሞረሽ ብለህ ስትጣራ ጀግና ሲበር ይደርሳል፣ የጀግና ሀገር ነው በቁጣ ይነሳል፣ በወኔ ይገሰግሳል፣ በድል አድራጊነት ይተምማል፡፡ ሞረሽ እየተባባሉ እየተጠራሩ ጠላት በመጣበት እየተሰባሰቡ ነው፡፡ ሞረሽ ብለው እየተጠራሩ ከጠላት ጋር እየተናነቁ ነው፡፡ ሞረሽ ብለው እየተጠራሩ የሀገርና የሕዝባቸውን ጠላት እያደቀቁ ነው፡፡ ሞረሽ ብለው እየተጠራሩ ጠላቶቻቸውን እየቀጡ ነው፡፡ ሞረሽ ብለው እየተጠራሩ እሳት ኾነው እያነደዱት፣ ወላፈን ኾነው እየገረፉት፣ መብረቅ ኾነው እያደባዩት ነው፡፡

አንድ ኾነህ ስትነሳ ጠላት ይርዳል፣ አንድ ኾነህ ስትነሳ ጠላት ይደነብራል፣ ወኔ ይርቀዋል፣ ጉልበት ያንሰዋል፡፡ በክፉውም በደጉም ዘመን አንድነት አሸናፊ ነው፡፡ አንድነት የድል በትር ነው፣ አንድነት የነፃነት መሠረት ነው፣ አንድነት የመከበሪያ ምስጢር ነው፣ አንድነት የክፉ ዘመን መሻገሪያ ነው፡፡ አንድ ያልኾኑት ለጠላቶቻቸው ይንበረከካሉ፣ አንድ የኾኑት ግን በድል አድራጊነት ይኖራሉ፡፡

ፎቶ ከፋይል በታርቆ ክንዴ (አሚኮ)

Leave a Reply