Site icon ETHIO12.COM

“የአሜሪካ በኢትዮጵያ ተላላኪ መንግሥት የመመስረት ፍላጎት ከሽፏል”አንዳርጋቸው ጽጌ

የአሜሪካ በኢትዮጵያ ውስጥ ተላላኪ መንግሥት የመመስረት ፍላጎት መክሸፉን አንጋፋው ፖለቲከኛ አንዳርጋቸው ፅጌ ገለጹ።

አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤የአሜሪካ መንግሥት ለአሸባሪው የሕወሓት ቡድን የተለያዩ ድጋፎችን በማድረግ በኢትዮጵያ ውስጥ ተላላኪ መንግሥት ለመመስረት ፍላጎት ቢኖረውም ቡዱኑ ሽንፈትን በመከናነቡ ከሽፏል።

የአሜሪካ መንግሥት ሰሞኑን አሸባሪው ሕወሓት በአፋርና በአማራ ሕዝብ ላይ በፈጸመው አሰቃቂ ግድያና ሰቆቃ ዙሪያ መግለጫ ማውጣቱን አውስተው፤ መግለጫውን ያወጡት በአማራና በአፋር ሕዝብ የሚፈጸመው ግፍና ጭፋጨፋ አሳስቧቸው ሳይሆን በአሻባሪው ቡድን በኩል ተላላኪ መንግሥት የመመስረት ፍላጎታቸው በመክሸፉ ነው ብለዋል።

የአሜሪካ መንግሥት አሸባሪው ሕወሓት እንደማያወጣቸው ሲረዱና ከተሸናፊው ጋር አብሮ መውደቅ ስለማይፈልጉም ከአሸናፊው ጎን ለመቆም ሲሉ በአፋርና በአማራ ሕዝቦች ላይ የደረሰው ሰቆቃና ግፍ እንደሚያሳስበቸው አድርገው መግለጫ ማውጣታቸውንም ገልጸዋል።

 የአሜሪካ ወይም የአውሮፓ አገራት በውጭ ጉዳይ ፖሊሲዎቻቸው የዴሞክራሲ፣ የፍትህና የሰብዓዊ መብት ጉዳይ አሳስቦቸው አያውቅም ያሉት አቶ አንዳርጋቸው፣ እነዚህን ጉዳዮች የሚያነሱት የራሳቸውን ፍላጎት ለማሳካት ሲሉ ብቻ መሆኑን ተናግረዋል።

እነዚህ አገራት ሲመቻቸውና ጊዜ ጠብቀው በኢትዮጵያ ውስጥ ደካማና በራሱ መቆም የማይችል መንግሥት ለመመስረት ፍላጎት እንዳላቸው አመልክተዋል። ዕድል ካገኙ ተመሳሳይ ሽብርና ሰቆቃ ከሚፈፅሙ ኃይሎች ጋር መተባበራቸው የማይቀር መሆኑን ጠቁመው፤ የኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት የእነዚህ መንግሥታትን መሰረታዊ ባህሪ ጠንቅቆ ማወቅ እንዳለበትም አሳስበዋል።

አሜሪካኖች በቀደመ አቋማቸው ጸንተው ቢቀጥሉ ሁሉንም መሰረታዊ ጥቅማቸውን እናጣለን ብለው ስላሰቡ ገለልተኛ ለመምስል ጥረት ሲያደርጉ ይታያል ያሉት አቶ አንዳርጋቸው፣ ኢትዮጵያ ህዝብና መንግሥት አሁን የአሜሪካ መንግሥት በያዘው አቋም ሳይዘናጉ ሁለንተናዊ ዲፕሎማሲያዊ ሥራዎችን አጠናክረው መቀጠል እንደሚኖርባቸው አስታውቀዋል።

ፀጋዬ ጥላሁንአዲስ ዘመን ታኅሣሥ 6/2014


MORE NEWS


Exit mobile version