ETHIO12.COM

ፖሊስ የፋናና የአሶሲየትድ ፕሬስ ‘ጋዜጠኖችን’ ጫካ ሄደው ኦነግ ሸኔን ፊልም ቀርጸው ኢትዮጵያ ላይ የተከፈተውን ዘመቻ አግዘዋል ሲል አሰረ

ፖሊስ ሪፖርት እንዳደረገው የተጠቀሱት የአሶስዬትድ ፕሬስና የፋና ብሮድካስት ባለሙያዎች ኦነግ ሸኔ ያለበት ዘንዳ በእግራቸው ተጉዘው ፊልም ከቀረጹ በሁዋላ ፊልሙን ለአሶሲየትድ ፕሬስ በላኩ በበነጋታው ነው። በመኖሪያ ቤታቸው በርካታ ማስረጃ ማግኘቱን ያስታወቀው ፖሊስ፣ ትህነግ በሰሜን፣ ኦነግ ሸኔ በምዕራብ እየገቡ ነው በሚል ዲፖላቶችና የውጭ ድርጅቶች አዲስ አበባን ለቀው እንዲወጡ ለተጀመረው ዘመቻ እንዲያግዝ ታስቦ የተሰራ መሆኑንን አመልክቷል።

ፖሊስ እንዳለው አገሪቱ በአስቸኳይ ጊዜ ባለችበት በአሁኑ ወቅት በፓርላማ በአሸባሪነት ከተፈረጀ ድርጅት ጋር መገናኘት በራሱ በህግ ያስቀጣል። ይህ ብቻ ሳይሆን ተግባሩ ታቅዶና ተናቦ የተሰራ መሆኑ አስታውቋል። በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ደንብ መሰረት እስከ 17 ዓመት በሚያደርስ ወንጀል ክስ እንደሚመሰረትም አመክቷል።

በኖቬምበር አንድ ከሁለት ሳንት በፊት ፍራንስ 24 በዝግጅቱ የት እንደሆነ ያልተገለጸውና ፖሊስ ምዕራብ ሸዋ ሲል የጠራው ቦታ ፣ የተዘጋጀው ፊልም ከቃለ ምልልስ ጋር በእንግሊዘኛ፣ እንዲሁም ኦሮምኛ ንግግር፣ በእንግሊዘኛ ትርጉም እየተተረጎመ ተላልፎ ነበር። ኤኤፍፒ ቀርጾት እንዴት በፍራንስ 24 የተለቀቀው ቪዲዮ ቃለ ምልልስ ጠያቂውና ፊልሙን ያዘጋጁት ዋና ሰዎች አይታዩም። ድምጻቸውም አይሰማም። ተጠያቂዎቹ የኦነግ ሸኔ አባላትና በየደረጃው ያሉ የጦር አመራሮች ሲሆኑ፣ ሲታዩ የነበሩት አዲስ አበባን እንዴት እንደሚቆጣጠሩ ልምምድ ሲያደርጉ ነው። የውጊያ ቦታ አያያዝ ሲማሩ በሚያሳየው ቪዲዮ ” ይህን አገዛዝ እናስወግደዋለን” ሲሉ ቀን እየቆረጡም ተናግረዋል።

ፊልሙን እዚህ ላይ ይመልከቱ

ወቅቱ ትህነግ ከኦነግ ሸኔ ጋር በጥምረት አዲስ አበባ ሊገቡ በቅርብ ርቀት ላይ መሆናቸው በስፋት የሚሰበክበትና በዘመቻ መልክ የሚታወጅበት ስለነበር፣ ቪዲዮው “ቁጥራቸው አነስተኛ ቢሆንም ሚዲያው ኢትዮጵያ ውስጥ ሆኖ እንደዚህ ያለ የጦር ሜዳ ልምምድ ሲያደርጉ መንግስት፣ በተለይም የኦሮሚያ ክልል ጸጥታ ክፍል አውቆ ነው ወይስ ሳያውቅ?” የሚል ጥያቄ በስፋት ከቪዲዮው ይፋ መሆን ጎን ለጎን ሲጠየቅ ነበር። አገሪቱ በአስቸኳይ አዋጅ ውስጥ የመሆኗ ጉዳይ ከምን ደርሶ እንዲህ ያለ ፊልም አገር ቤት በማንና እንዴት ተሰራ? የማይታየው ጠያቂስ ማን ነው? የሚለው ጉዳይ ሲያነጋግር ቆይቶ ነበር።

ዘጋቢዋ በትረካ ድምጽ የጦር ልምምድ ስልጠና ሲሰጥ እያሳየች ” ተዋጊዎቹ አዲስ አበባ አቅራቢያን ተቆጣጥረዋል፣ በርካታ ድሎችንም አስመዝግበዋ” ትላለች። አያይዛም ወደ አዲስ አበባ እየገሰገሱ እንደሆነ ትናገራለች። በመሃል ቃለ ምልልስ ያደረገችለትን የድርጅቱ አባል ታስገባለች። እሱም “አገዛዝ” ያለውን መንግስት በቅርብ እንደሚያስወግዱ ቃል ሲገባ ታሳያለች። ቀደም ሲል ከሚሴ በለውጡ ሰሞን የተቀረጸ ፊልም አስገብተው ከተማ ሲቆጣጠሩ ሕዝብ አቀባበል አደረገ በሚልም ሪፖርቷን አዋዝታ ” በአዲስ አበባ ቅርብ አካባቢ ተቆጣጥረዋል” ስትል ቦታ ሳትገልጽ ገልጻለች። ፖሊስ ይህንን ሰብስቦና በፍተሻ ከተጠርጣሪዎች ቤት ያገነውን መረጃ አደራጅቶ ” ሆን ተብሎ በቅንብር አገሪቱን ለማሸበር የተሰራ” ሲል ተጠርጣሪዎቹን በከባድ ወንጀል እንደሚጠይቅ አስታውቋል።

ዛሬ ይፋ እንደሆነው የፌደራል ፖሊስ “በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ ዞን የአሸባሪውን ሸኔ ቡድንን በዓለም አቀፍ ደረጃ የማስተዋወቅ ስራ ሲሰሩ የነበሩ ጋዜጠኞች በቁጥጥር ስር አውያለሁ” ሲል ይፋ እንዳደረገው ተጠርጣሪዎቹ ረዥም ርቀት በእግራቸው ጫካ ሄደው፣ ሰው ቤት በማደር ፊልሙን ቀርጸው ኬንያ ለሚገኝ የግብጽ አገር ዜግነት ላለው የድርጅቱ ሰራተኛ መላካቸውን እንዳረጋገጠ አመልክቷል። ኮምፒወተሮቻቸውና ስልኮቻቸው በባለሙያዎች ተመርመረው በርካታ መረጃዎች መገኘቱንም ገልጿል።

በቁጥጥር ስር የዋሉት ጋዜጠኞች አንደኛ ተጠርጣሪ አሚር አማን የአሶሺየትድ ፕሬስ ጋዜጠኛ፣ ሁለተኛ ተጠርጣሪ ቶማስ እንግዳ የካሜራ ባለሞያ እና ሦስተኛ ተጠርጣሪ አዲሱ ሙሉነህ የፋና ብሮድካስቲንግ ጋዜጠኛ ናቸው።

አዲሱ ሙሉነህ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ባልደረባ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል። ተጠርጣሪዎቹ መያዛቸው ከመገለጹና ሸኔን በዓለም ዓቀፍ ደራጃ የማስተዋወቅ ስራ ሲሰሩ መገኘታቸው ብቻ ነው የተጠቆመው። ታምራት ነገራን ጨምሮ በድምሩ ሶስት ጋዜጠኞች መታሰራቸው መገለጹ የሚታወስ ነው። የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን የጋዜጠኖቹ ሁኔታ እንዳሳሰበው ሲገልጽ፣ ሲፒጄ እስሩን አውግዟል።

የጋዜጠኖችም ሆኑ የመብት ተሟጋቾች መነካት እንደሌለባቸው በርካቶች ቢያምኑም፣ በኢትዮጵያ የሚዲያ አጠቃቀምና አክቲቪዝም ከፍተኛ ችግር የሚስተዋልበት አውድ መሆኑን ባለሙያዎች ሲናገሩ ይደመጣል። ከታሰሩት ጋር በተያያዘ ብቻ ሳይሆን አጠቃላይ ሙያው የተጠለፈና ለውስን ዓላማ የተቋቋመ መሆኑ ሌላው ችግር እንደሆነ በጥናት ሳይቀር የገለጹ በርካታ ናቸው። የሃሰት ዘገባ መስራት፣ ህግን አክብሮ አለመተቸት፣ የአገርን ሚስጢር አሳልፎ የመስጠትና ያለ በቂ መረጃ ባለስልጣኖችን፣ መሪዎችን፣ ለየት ያለ አቋም ያላቸውን መቀጠቀጥና ማጠልሸት በኢትዮጵያ በስፋት የሚስተዋል፣ ሙያውንም ያኮሰሰ ተግባር እንደሆነ በድፍረት የሚናገሩ አሉ። ከሁሉም በላይ ግን ሳንቲም ለቀማ ላይ ትኩረት በማድረግ የአገሪቱን ወቅታዊ ሁኔታ ያባባሱት እንደሚበዙ ስምምነት አለ።


MORE STORIES

Exit mobile version