Site icon ETHIO12.COM

” ከህወሃት ጋር ምንም አይነት ግንኙነትም፣ ንግግርም፣ ድርድርም አንፈልግም “- አቶ ሙሳ አደም

የአፋር ህዝብ ፓርቲ ከህወሃት ጋር ምንም አይነት ንግግርና ድርድር ማድረግ እንደማይፈልግ አስታወቀ።

የፓርቲው ሊቀ መንበር አቶ ሙሳ አደም ለአል ዐይን በሰጡት ቃል፤ አሁን ላይ በሕዝብ ላይ ትንኮሳና ጥቃት እያደረሰ ካለው የህወሃት ቡድን ጋር እንደ ፓርቲ መነጋገርም ሆነ መደራደር እንደማይፈልጉ ገልፀዋል።

አቶ ሙሳ ህወሃት ትናንትና ከሰዓት በኋላ በሰሜን አፋር በኩል አዲስ ጥቃት መክፈቱን ተናግረዋል።

ህወሓት በመጀመሪያ በአፋር ክልል በራህሌ ጥቃት ሰንዝሮ እንደነበር አስታውሰዋል።

አቶ ሙሳ፥ ህወሃት የአብአላ ከተማን ለመቆጣጠር 3 እና 4 ጊዜ ሙከራ ማድረጉን ገልጸው በአካባቢው ያለው የአፋር ሕዝባዊ ሰራዊት ይህንን ጥቃት እየመከተ መሆኑንም ተናግረዋል።

የአፋር ሕዝብ ፓርቲ ከስር መሰረቱ የተቋቋመው ህወሃት በሕዝብ ላይ ሲፈጽመው የነበረውን የረጅም ዘመናት ግፍና መከራን ለመታገል ነው ያሉት አቶ ሙሳ ፓርቲያቸው ከሕወሃት ጋር ምንም አይነት ግንኑነትም፣ ንግግርም፣ድርድርም እንደማይፈልግ ተናግረዋል።

አቶ ሙሳ፤ እንደፓርቲ ከህወሃት ጋር ድሮም ምንም ንግግር አልነበረንም ያሉ ሲሆን፤ ወደፊትም ንግግር ሊኖር አይችልም ሲሉ ገልጸዋል።

ሊቀመንበሩ፥ “ህወሃት የአፋርን ሕዝብ ብዙ መከራ አብልቷል” ያሉ ሲሆን የፓርቲውን አመራሮች አሸባሪ ብሎ ፈርጆ እንደነበር አስታውሰዋል።

እንደፓርቲ ከህወሃት ጋር መነጋገር እንደማይፈልጉ የተናገሩት አቶ ሙሳ እንደሀገር ግን የኢትዮጵያ ሕዝብ ተነጋግሮ ችግሮቹን በጠረንጴዛ ዙሪያ መፍታት ከቻለ “እኛም እንደ አንድ የኢትዮጵያ ክፍል ሰላም የምናገኝበት አጋጣሚ ሊኖር ስለሚችል የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚወስነውን አብረን የምንወስን ይሆናል” ብለዋል።

#አልዓይን

Exit mobile version