Site icon ETHIO12.COM

የአጣዬው ደብዳቤ

ከአጣዬ የደረሰን ደብዳቤ የአንድ ጀግና ኢትዮጵያዊን ተጋድሎ ያትታል፤ ስለፍትህ፣ ስለሃገር ፍቅር እና ስለክብር የታገለ ኢትዮጵያዊ ጀግና።

ስድስቱን የአሸባሪ ታጣቂዎች ከሚጠብቀው ባንክ ደጃፍ ጥሎ በክብር የተሰዋ የጀግኖች ቁና ነው። ጀግናው ወታደር አረጋ ግዛው።

ወታደር አረጋ የቀድሞ ሠራዊት አባል ነበር። በጀግንነት እስከተሰዋበት ቀን ድረሥ ደግሞ የወጋገን ባንክ የአጣየ ቅርንጫፍ የጥበቃ ሰራተኛ። ተወልዶ ያደገው በማጀቴ ከተማ ነው። ገና ከልጅነቱ ጀምሮ ለሀገሩ ያለውን ፍቅርና ክብር የገለጠው የቀድሞውን ሠራዊት በመቀላቀል ወያኔን በግንባር በመፋለም ነበር።

ከ1983 ዓ.ም የመንግስት ለውጥ በኋላ የህወሓት አመራሮች ሠራዊቱን ሲበተኑ፡ አረጋ ለሀገሩ እንዳልደማና እንዳልቆሰለ ሜዳ ላይ ተጣለ። ህይወት በውጣ ውረድ ውስጥ ይቀጥላልና የተለያዩ ሥራዎችን አየሰራ ኑሮውን ሲገፋ የቆየው ወታደር አረጋ፤ የወጋገን ባንክ አጣዬ ቅርንጫፍ የጥበቃ ሰራተኛ ሆኖ የተቀጠረው በዚህ አመት ነበር።

የትግራይ ወራሪ ሃይል ከግብር አጋሩ ሸኔ ጋር በመሆን ወደከተማዋ እየተጠጉ መሆናቸውን የተረዱት የባንኩ ኃላፊዎች ለወታደር አረጋ እና ሌሎች ባልደረቦቻቸው ራሣቸውን እንዲያድኑ መመሪያ ሰጧቸው፤ ሠራተኞችም የተባሉትን አደረጉ።

በእለቱ ተረኛ የነበረው የወታደር አረጋ ባልደረባ እነሡም በተመሳሳይ ወደቤታቸው እንዲሄዱ ጥያቄ ቢያቀርብለትም፤ “ባንኩን ጥዬ አልሄድም” በሚል እዛው እንደቀረ የባንኩ ሎቢ አቴንዳንት ሃምሳ አለቃ ቴዎድሮስ ደግነት ለኢፕድ ተናግረዋል።

የ2890 ብር ደመወዝተኛው ወታደር አረጋ ለባንኩ የገባውን ቃል ኪዳን ላለመሻር ሲልም በባንኩ ውስጥ ብቻውን ሆኖ የሚመጣውን መጠበቅ ተያያዘ። ዘራፊዎቹ የአሸባሪው ታጣቂዎች ወደ ባንኩ ተጠጉ። ባንኩን ሰብረው ለመግባት ትግል ሲጀምሩ ወታደር አረጋ አልፈቀደላቸውም፤ ለጥበቃ የተሰጠውን መሳሪያ አቀባብሎ ወራሪዎቹን መልቀም ጀመረ። ስድስቱን ገደላቸው።

ያልጠበቁት የገጠማቸው የትግራይ ወራሪ ሃይል አባላት የተኩስ ሩምታ ወደ ባንኩ አዘነቡ። ከረጅም ተኩስ ልውውጥ በኋላ ወታደር አረጋ የያዘው ተተኳሽ አለቀበት፤ በጀግንነት ወደቀ፤ በክብር ተሰዋ።
የአሸባሪው ታጣቂዎችም የጀግናውን እስከሬን ተረማምደው የፈለጉት ያህል ዘርፈው ንብረቱን አውድመው ለ15 ቀናት አስከሬኑን በባንኩ አስቀምጠው አንሰጥም በሚል እዛው መሰንበታቸውን እማኞች ተናግረዋል።

ጀግናው ወታደር ባንኩን አላስደፍርም በሚል 6 ያሸባሪውን ታጣቂዎች እንደገደለባቸውም አሸባሪዎቹ አስከሬን ስጡን ብለው ለመጡ ጓደኞቹና ቤተሰቦቹ ተናግረዋል። “6 ጓዶቻችንን የገደለብንን ሠው አስከሬን አንሰጥም” ብለው በዛቻ እንደመለሷቸውም ሃምሳ አለቃ ቴዎድሮስ ነግረውናል።

አሸባሪዎቹ ከከተማዋ ሲባረሩም ለተላላኪዎቻቸው የሸኔ ታጣቂዎች “ይህ አስከሬን 6 ጓዶቻችንን የነጠቀን ስለሆነ እንዳይቀበር ለማንም እንዳትሰጡ” ብለው መሄዳቸውን፤ ነገር ግን እነሱም በሀገር መከላከያ ሠራዊት፡ በአማራ ልዩ ሀይል፡ ፋኖ እና ሚሊሻ እንደ ላኪዎቻቸው መባረራቸውን ነው ሃምሳ አለቃ ቴዎድሮስ የተናገሩት።

የጀግናው ወታደር አስከሬን ከወደቀበት ተነስቶ በክብር አርፏል። የሰራው ገድል ከመቃብር በላይ ዝንት ዓለም ሲነገር ይኖራል።

Via – (ኢ.ፕ.ድ)


Exit mobile version