ETHIO12.COM

እምባ ያፋሰሰው ልዩ ቀን ” ድልድዩ ተሰበረ”

ስሜቱ ቀላል አይደለም። ምንም ይሁን ምን አገር አገር ናት። እንደተወለዱበት፣ እነድፈነጩበትና እንዳደጉበት ምድር የሚሆን የለም። ዘንግዳና ቂጣው በአገር ምድር ያስደስታል። በወገን፣ ዘመድ፣ ባልደረባ ታጅቦ በራስ ማንነትና ባህል መከበብ ልዩ ስሜት ነው። በተለይም አገር ሰላም ስትሆንና ልማቷን በማፋጠን ካጎበጠን ድህነት፣ መዛበቻ ካደረግን ልመና፣ እንድንበረከክ ከሚገፋን ድንቁርና ለመላቀቅና ለመጪው ትውልድ በጎ ስንቅ ለማኖር በተደረገ ጥሪ ተገኝቶ ጠጠር መወርወር ታላቅነት ነው።

አገራችንን ከጠላትና ክፉ አሳቢዎች ጋር ተባብሮ ወደ አመድነት ለመቀየር የተነሳው ትህነግ ተቀጥቅጦ በተባረረበትና መልሶ ማቋቋሙ ከጦርነቱ በላይ ፈጥኖ እያስገመገመ ባለበት ወቅት አገር ምድር ላይ ሆኖ የመልሶ ግንባታው አካል መሆን የወርቃማ ታሪክ አባል ያደርጋል። አመድ ላይ እንዲወድቁ የተደረጉ ወገኖችን፣ ያለ ህክምናና ትምህርት ቤት የቀሩ አካሎቻችንን አመዱን አፍሶ ህይወት ለመለስ በተጀመረው ርብርቦሽ አጋር መሆኑ፣ ቁስሉን መጋራት ከምንም በላይ ሃያልና ህያው ተግባር ነው።

ethiopia homecoming 1 mil poster

በዚሁ መነሻ ተገፍተውም ሆነ በተለያዩ ምክንያቶች ኢትዮጵያን ለቀው የወጡ ወይም እንዲወጡ የተደረጉ ዜጎች በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ ጥሪ በልዩ ክብር አገራቸው ገብተዋል። እየገቡ ያሉም አሉ። ቀደም ሲል በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ የደህንነት ቢሮ ስማቸው ተቀምጦ አገር ቤት መግባት የማይችሉ ሰተት ብለው ምድራቸውን ረገጠዋል። ሳይሸማቀቁ ከብረዋል። በሆነው ሁሉ የደስታ እንባ አንብተዋል። የአዛኑ ያህል አቶ ደመቀ እንዳሉት ” ስንቸገር የሚወዙ፣ ሲሳካልን የሚደበዝዙ” አፍረዋል። ውድቀታችንን እንደማየት የሚያኮራቸና የሚያስደስታቸው ነገር እንደሌለ ሲተፉ የነበሩ አፍረዋል። ኤትዮጵያ በአምላኳ ክንፍ ተሸፍና የደረሰባትና የተቃጣባትን የድራጎኖች ዘመቻ መክታ በራች።

ዓመድ እንድትሆን የተፈረደባት ኢትዮጵያ አመድ ሊያደርጓት ያሰቡትን በአባቶችና እናቶች ጸሎት የጨው አምድ ሆነውላት፣ በልጆቿ ብርታት ተፈረካክሰው፣ በውጭ በሚኖሩ ልጆቿ የአዝማቾቻቸው ልሳንና ላንቃ ተዘግቶ፣ በደጀኑ ህዝብ ያላሰለሰ ድጋፍ እዚህ ደርሳ ልጆሿን እምብርቷ ላይ አከበረች። አሁን ቀሪው ተግባር በዘላቂነት እንደ ሌሎች አገሮች ኢትዮጵያን ማበልጸግ ላይ መረባረብና ስንበራ በሚወረዙት ፊት ማብረቀርቅ ነው። እምባችንን ተርገን ከወደመው በላይ በዕልህ መልሶ መገንባት ነው።

በስደት በሚኖሩባቸው አገራት ሆነው የቀደመውን የትግራይ ነጻ አውጪ ግንባር ዘረኛና አምባገነን አገዛዝ የሚቃወሙ የነበሩ አብረዋቸው በስደት ባሉ የትህነግ ደጋፊና አባላት ምስላቸው እየተነሳ ወደ አገር ቤት እየተላከ አገራቸው እንዳይገቡ በጥቁር መዝገብ ይሰፍር ነበር። ከሃያ ስምንት ዓመት በሁዋላ አገሩ የገባው ስደተኛ ይህን ጉዳይ ሲያነሳ ያለቅሳል። ዛሬ ይህ ተረት ነው። የሚሻሻሉ ተግባራት ቢኖሩም የቀድሞው ዓይነት መዘገብ የለም።

“አውሮፕላን ማረፊያ ስደርስ እግሬ ተርበተበተ። መቆም አቃተኝ። ምን እንደሆንኩ የማላውቀው ስሜት ነዘረኝ። ልቤ መምታት አቆመች” ሲል የሚናገረው አቤል ስለሺ በደቡብ አፍሪካና አሜሪካ ነው ህይወቱን የገፋው። የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤም ይህን ጉዳይ ነክተው አልፈዋል። የማይታሰበው እንደሆነ አመልክተው “የመለያየቱ ድልድይ ተሰብሯል” ሲሉ አገራቸው እንዳይገቡ ሲሸማቀቁ የነበሩ ያን ስሜት ረስተው በነጻነት በአገራቸው ምድር ሽር ብትን እንዲሉ አሳስበዋል።

ለውጡን ተከትሎ በርካታ ዜጎች ወደ አገራቸው የመመለስ እድል አግኝተው የነበረ ቢሆንም፣ የአሁኑ ጥሪ የተለየ መሆኑንን አስተአየት ሰጪዎች አመልክተዋል። ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ” አገራችን ከጦርነት በአፋጣኝ ወጥታ ወደ ልማት ፊቷን እንዳመራች በኈዳችሁበት ሁሉ ተናገር” ሲሉ እንግዶች በቆይታቸው ትርጉም ያለው ስራ እንዲሰሩ ጠይቀዋል።

በምትጎበኟቸው ቦታዎች ሁሉ ወራሪው ሃይል ያፈጸመውን በቃላት መግለጽ የማይቻል ድርጊት ሰንደው የዲፕሎማሲ ዘመቻቸው ትጥቅ እንዲያደርጉ የአምባሳደርነት ስልጣን መስተታቸውን አመልክተዋል። እንደ ጀርመን አይነቱ የአማርና ፕሮግራም ከኢትዮጵያ ጠላቶች ጋር አድመው ኢትዮጵያ የኤንባሲ ቁጥር መቀነሷንና ከማዕከል የኦንላይን የዲፕሎማሲ ስራ መጀመሯን እንደ ድክመት ሲተቹ ስለነበር የተቅላይ የአቶ ደመቀ ጥሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ” የዲፕሎማሲ ስራ የሚሰሩልን ዲያስፖራዎች ናቸው” ሲሉ አስቀድመው የተናገሩትን አረጋግጠዋል።

እነደተባለውም በኢትዮጵያ ታሪክ ታይቶ በማይታወቅ ንቅናቄ የዲፕሎማሲ ዘመቻው ተጠናክሮና ተናቦ በጋራና በህብረት አስደማሚ የ”በቃ” ዘመቻ በመካሄድ የሃሰተኛ ሚዲያዎችን ላንቃ እንዳዘጋ በዛሬው የአቀባበል ስነ ስራአት ላይ ተመልክቷል። እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ በሄደበት ሁሉ የአገሩ አምባሳደር መሆኑ አስር ኤምባሲ ታጥፎ ሚሊዮን አምባሳደሮችን ያፈራ አሰራር መሆኑንን አምለካቷል።

አዳነች አቤቤ ” ስናጠፋ እየመከራችሁ፣ ስናጎድል እየጠቆማችሁ” ሲሉ በቤተሰባዊ ቋንቋ ለእንግዶች ” የአገራችሁን ምርት ግዙ፣ በአጋራችሁ ምርት ኩሩ” የሚል ወቅታዊ ጥሪ አስተላልፈዋል። አምባሳደርነት የሚጀምረው በራስ ከመኩራት በመሆኑ የከንቲባዋ ጥሪ አግባብ እንደሆነ ተመልክቷል። ከስር የአቶ ደመቀና የወ/ሮ አዳነች ንግግር ከኢቢሲ የተወሰደውን እንዳለ አትመነዋል።

“በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ለፍትሕ ያደረጉት የ‘#በቃ’ ዘመቻ ታሪካዊ ጀግንነት ነው”፦ አቶ ደመቀ መኮንን

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ለፍትሕ ያደረጉት የ‘#በቃ’ /‘#NoMore’/ ዘመቻ ታሪካዊ ጀግንነት መሆኑን ተናገሩ።

ደመቀ መኮንን – ም/ጠ/ሚ

አቶ ደመቀ የሀገርን ጥሪ ተቀብለው ከመላው ዓለም ወደ ሀገር ቤት የመጡ ኢትዮጵያዊያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያንን እንኳን በሰላም መጣችሁ በማለት በወዳጅነት አደባባይ በተዘጋጀው መርሐ-ግብር ላይ ምስጋና አቅርበዋል።

“በየዘመኑ በውድ ልጆቿ ትብብር እና አይበገሬነት የተደቀነባትን ፈተና ሁሉ እየተሻገረች እዚህ የደረሰችው እናት ሀገራችን ኢትዮጵያ ዛሬም ማህፀነ ለምለም የጀግኖች መፍለቂያ መሆኗን በተግባር አረጋግጣችኋልና ሀገር እና ወገን በእናንተ መኩራቱን ስገልጽ በኩራት ነው” ብለዋቸዋል።

ባለፉት ጥቂት ዓመታት በተለይም ባለፈው አንድ ዓመት ዳያስፖራው ማኅበረሰብ ለሀገሩ የተለያዩ የውጭ ጣልቃ ገብነትን በዓለም አደባባይ ቅሬታውን ሲገልጽ እና ሲቃወም አጥብቆም ሲዋጋ መቆየቱንም አውስተዋል።

በተለይም በአሁኑ ሰዓት በቃ ወይም /#NoMore”/ በማለት ከጀግኖች አባቶቻችን በወረስነው ጀግንነት የጀመራችሁት የፍትሐዊነት ትግል ይሄን አድሏዊ ዓለም እርቃኑን አስቀርቷል ብለዋል።

የዳያስፖራው ትግል ለፓንአፍሪካኒዝም ወኔ መሆኑን እና አፍሪካን እና የዓለም ጥቁር ሕዝቦችን እንዲሁም የኢትዮጵያ ወዳጆችን ማነቃነቁን ገልጸው ምስጋና አቅርበዋል።

በሀገር ቤት ያለው ሕዝብ ለሀገሩ ዘብ በመቆም ከምንጊዜውም በላይ የተሻለ ሁሉን አቀፍ ርብርብ በማካሄድ ላይ እንደሚገኝ አብራርተው፣ ይሁንና አሸባሪው ህወሓት የእኛን ልዩነት ከሚፈልጉ የጥፋት ኃይሎች እና ጠላቶቻችን ጋር አብሮ ጉዳት አድርሷል ብለዋል።

አሸባሪው ህወሓት ከኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ጋር በመሆን ሀገራችን ላይ ያልፈጸመው ጥፋት የለም ነው ያሉት።

አሸባሪው ቡድን በርካታ አሳዛኝ እና ዘግናኝ ድርጊቶችን መፈጸሙን የገለጹት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ፣ የሀገር መከላከያ ሠራዊት እና የክልል ልዩ ኃይሎች አሸባሪውን ኃይል በመደምሰስ ረገድ ዘመን ተሻጋሪ ጀግንነት ፈጽመዋል ብለዋል።

ኢትዮጵያውያን ደማቅ መሥዋዕትነት በመክፈል ሀገራቸውን መታደግ ችለዋልና ልንኮራ ይገባል ሲሉም ተናግረዋል።

የደረሰብንን ቁሳዊ እና ሰብዓዊ ጉዳት ለመቋቋም እና ለማደስ ድጋፍ ለሚሻው ወገን እና መልሶ መገንባት ሥራ በተባበረ ክንዳችን አብረን መቆም ይገባናልም ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።

“ዳያስፖራው የሀገሩን ክብር ለመጠበቅ በዓለም አደባባይ የተጫወተው የአምባሳደርነት ሚና ከፍተኛ ነው”፦ ከንቲባ አዳነች አቤቤ

ዳያስፖራው የሀገሩን ክብር ለመጠበቅ በዓለም አደባባይ የተጫወተው የአምባሳደርነት ሚና ከፍተኛ መሆኑን የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ተናገሩ።

አዳነች አቤቤ – ከንቲባ

ከንቲባዋ በወዳጅነት አደባባይ በተካሄደው የዲያስፖራዎች አቀባበል ሥነ-ሥርዓት ላይ ባደረጉት ንግግር፣ የእናት ሀገራቸውን ታሪካዊ ጥሪ አክብረው ለተገኙ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

ዳያስፖራው ለእናት ሀገሩ ጥሪ የሰጠው መላሽ አኩሪ መሆኑን እና ያሳየው ፅናትም ማሸነፍን ከነክብሩ የሚያጎናፅፍ የአንድነት ካባ ሆኖ የሚታይ ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያን ለማፍረስ የተባበሩት የውስጥ እና የውጭ ኃይሎች የተለያዩ ጫና ቢያደርጉም በመላው ዓለም የሚገኙ ኢትዮጵያውያን፣ “#NoMore” /#በቃ/ ብለው በያሉበት ሀገር ያሰማሙት ድምፅ ከኢትዮጵያ አልፎ የአፍሪካውያን ንቅናቄ ሆኗል ያሉት ከንቲባዋ፣ ለዚህም ኢትዮጵያ እንደምታከብራቸው ገልጸዋል።

“ስለዳያስፖራ ሲነሣ መሪዎቹን ማሸማቀቅ እና የፖለቲካ ሽኩቻ ማሳያ መሆኑ ዛሬ ታሪክ ሆኗል፤ ባይተዋርነት ነግሦ ኢትዮጵያውያን እዚህ እና እዚያ ሆነን መራራቃችን ቀርቷል፤ ይህ ደግሞ በታሪካችን አዲስ ነገር ነው” ሲሉም ተናግረዋል።

“ኢትዮጵያ የተሠራችበት ውቅር ከቃል በላይ ነው” ያሉት ከንቲባዋ፣ ለእርሷ የተሰጠ በልጆቿ ደም ውስጥ ብቻ ያለ ከሌሎች ዓለም ሁሉ የተለየ አንዳች ልዩ ፀጋ አላት ሲሉም ገልጸዋል።

“ኢትዮጵያ ትፈርሳለች የሚለውን ብሂል ልጆቿ አፍርሰውታል፤ በጀግንነት እየወደቁ ቀና ማለትን አሳይተናል፤ ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረት አሸንፋለች” ነው ያሉት።

አዲስ አበባም እንደተሟረተባት ሳይሆን ሰላም መሆኑን በግልጽ እያሳየች መሆኑን ተናግረዋል።

ዳያውፖራው በሀገሩ በሚያደርገው ቆይታ የሀገሩን ምርት እንዲገዛ እና የበኩሉን ሚና እንዲጫወት ጥሪ አቅርበዋል።

ኢትዮጵያዊነትን በቃል ሳይሆን በተግባር አሳይተናል ያሉት ወ/ሮ አዳነች አቤቤ፣ ኢትዮጵያ የምትበለጽገው በልጆቿ ጥረት በመሆኑ ሁላችንም በጋራ ልንቆም ይገባል ሲሉ አሳስበዋል።


Exit mobile version