ETHIO12.COM

የትህነግ ነውር- የኮምቦልቻ ኢንዱስትሪ ፓርክ ዝርፊያና ውድመት

በኮምቦልቻ የኢንዱስትሪ ፓርክ በሚገኙ ድርጅቶች ላይ የህወሓት አማፂያን ያደረሱት ዝርፊያና ውድመት ከፍተኛ የሚባል መሆኑን የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሳንዶካን ደበበ ለቢቢሲ ገለፁ።

እንደ ዋና ሥራ አስፈጻሚው ገለጻ በኢንዱስትሪያል ፓርኩ ውስጥ ስድስት ከተለያዩ አገራት የመጡ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ወደ ሥራ ገብተው ነበር።

በኢንዱስትርያል ፓርኩ ከ90 ሚሊየን ዩሮ በላይ ወጪ በማድረግ የአልባሳትና ጨርቃ ጨርቅ ምርት ላይ ተሰማርቶ የነበረው የጣልያኑ ካርቪኮ ኩባንያ ለሥራዎቹ ያስገባቸው መለዋወጫ እቃዎችና ሌሎች ጥሬ እቃዎች ከፍተኛ ውድመትና ዝርፊያ እንደተፈፀመባቸው ጨምረው ገልፀዋል።

በአገር ደረጃ ከጣልያን፣ ከቻይና እንዲሁም ከኮሪያ የመጡ ድርጅቶች በኢንዱስደትርያል ፓርኩ እንደሚገኙ የተናገሩት ኃላፊው፣ እነዚህ ኩባንያዎች በብዛት በአልባሳትና ጨርቃ ጨርቅ ምርት ላይ ተሰማርተው የሚገኙ መሆናቸውን ያስረዳሉ።

በተጨማሪ ደግሞ እንደ ካልቪን ክላይን ያሉ ዓለም አቀፍ ብራንዶች ጋር የሚሰሩ፣ በቆዳና በቆዳ ውጤቶች ላይ ተሰማርተው የነበሩ ድርጅቶችም አሉ። ጉዳትም የደረሰው በእነዚሁ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ላይ ነው ሲሉ ገልፀዋል።

የኢንዱስትሪ ፓርኮች ኮርፖሬሽን በኮምቦልቻ ኢንዱስትሪ ፓርክ የደረሰውን ዝርዝር ጉዳት ለማጣራት መርማሪ ቡድን አቋቁሞ ወደ ስፍራው መላኩን ዋና ሥራ አስፈጻሚው ለቢቢሲ ገልጸዋል።

የህወሓት ኃይሎች ይዘዋቸው በነበሩ የአፋርና የአማራ ክልል አካባቢዎች ውስጥ በመንግሥትና በሕዝብ ንብረት ላይ ከፍተኛ ዝርፊያና ውድመት ማድረሳቸው ተገልጿል።

ከእነዚህ መካከል ደግሞ በአማራ ክልል የሚገኘውና ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰበት የተነገረው የኮምቦልቻ ኢንዱስትሪያል ፓርክ ተጠቃሽ ነው።

የፓርኩ የአንድ ማዕከል አገልግሎት መስጫዎች፣ የማምረቻ ቦታዎች፣ የኬሚካል ማጣሪያ እና ሌሎች በፓርኩ ውስጥ አገልግሎት ይሰጡ የነበሩ ክፍሎች በሙሉ ዝርፊያና ውድመት ደርሶባቸዋል።

በተጨማሪም በኢንዱስትሪያል ፓርኩ ውስጥ ያሉ ድርጅቶች ተሽከርካሪዎችም ቢሆኑ በአማጺያኑ መወሰዳቸው ተገልጿል።

እንደ ዋና ሥራ አስፈጻሚው ገለጻ የፓርኩ የቢሮ እቃዎችና የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሲስተሞች፣ የአምራች ኩባንያዎች ቢሮዎችና ቁሳቁሶች፣ ለውጭ ገበያ የተዘጋጁ የጨርቃ ጨርቅ አልባሳትና የቆዳ ውጤቶች ተዘርፈዋል።

እንዲሁም የምርት ማከማቻ መጋዘኖች ውስጥ የነበሩ ለምርት የተዘጋጁ ጥሬ እቃዎች፣ የተለያዩ ተሽከርካሪዎች እንዲሁም ሌሎች በፓርኩ ውስጥ የሚገኙ ቁሳቁሶች ዝርፊያና ውድመት እንደደረሰባቸው የኢንዱስትሪ ፓርኮች ኮርፖሬሽን ለቢቢሲ አስታውቋል።

ዝርፊያ እና ውድመት

የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሳንዶካን ደበበ እንደሚሉት በኮምቦልቻ ኢንዱስትሪ ፓርክ ላይ የደረሰው ጉዳት በሁለት መንገድ የሚገለጽ ነው። የመጀመሪያው ዝርፊያ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ውድመት ነው።

“ከዝርፊያው አንጻር ድርጅቶቹ አምርተዋቸው የነበሩና ወደ ውጪ ሊላኩ የነበሩ የተለያዩ ምርቶች ተሰርቀዋል። እንዲሁም ኩባንያዎቹ የሚያመርቷቸውን ምርቶች ለማምረት ጥቅም ላይ የሚውሉ ጥሬ እቃዎች ሙሉ በሙሉ ተወስደዋል።”

ከዚህ በተጨማሪም ድርጅቶቹ ቢሮዎች ውስጥ የነበሩ መገልገያዎች ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ መዘረፋቸውን፣ በተለይ ደግሞ በቀላሉ ሊተኩ የማይችሉ መሳሪያዎችና የምርት ሥርዓቶች ሙሉ በሙሉ መውደማቸውን ዋና ሥራ አስፈጻሚው ይናገራሉ።

“ይህ በፓርኩ ውስጥ የሚሰሩ ድርጀቶች ላይ የደረሰው ጉዳት ነው። ወደ ኢንደስትሪ ፓርኩ ስንመለስ የቢሮ እንዲሁም አገልግሎት መስጫዎች ውድመት፣ የመሳሪያዎች ውድመትና ስርቆት እንዲሁም የአምቡላንስ እና የእሳት አደጋ ተሽከርካሪዎች ጭምር ተዘርፈዋል።”

የኢንደስትሪያል ፓርኩ ማጣሪያዎች ተነቅለው እንደተወሰዱና ሊወሰድ ያልቻሉት ደግሞ እንዲወድሙና እንዲቃጠሉ መደረጉን የሚናገሩት አቶ ሳንዶካን፤ በተጨማሪም የተለያዩ አገልግሎት የሚሰጡ እንደ ደኅንነት መጠበቂያ መሳሪያዎችም ጭምር እንዲወድሙ ሆኗል ይላሉ።

“የኤሌክትሪክ እና ሌሎች ገመዶች አገልግሎት እንዳይሰጡ ተደርገው ተቆራርጠዋል። እንዲሁም ለፓርኩ ተጨማሪ ግንባታ ለማድረግ እንደ መጋዘን ሲያገለግሉ የነበሩ ሦስት ኮንቴይነሮች ተጭነው ተወስደዋል።”

የሥራ እድል

የህወሓት አማጺያን የኮምቦልቻ ኢንዱስትሪያል ፓርክ ላይ ዝርፊያና ጉዳት ከማድረሳቸው በፊት በአጠቃላይ በውስጡ ወደ 3600 አካባቢ የሚሆኑ ሠራተኞች ተቀጥረው ይሰሩ ነበር።

እነዚህ በቀጥታ በድርጅቶቹ ተቀጥረው ይሰሩ የነበሩ ሲሆኑ በተዘዋዋሪ ደግሞ ለእነዚህ ሠራተኞች የምግብና ተያያዥ አገልግሎቶችን የሚሰጡ ቀላል የማይባል ቁጥር ላላቸው ሰዎች የሥራ እድል ተፈጥሮላቸው ነበር።

“የደረሰው ውድመት ፈታኝ ነው። አንዳንዶቹ የጠፉት ነገሮች እጅግ መሠረታዊ ነገሮች በመሆናቸው በቀላሉ ተገዝተው ብቻ ሥራ የሚጀመርባቸው አይደሉም። ምናልባት በሙሉ አቅም ወደ ሥራ ለመመለስ ጊዜ ሊወስድ እንደሚችል እንገምታለን” ይላሉ አቶ ሳንዶካን።

ኮርፖሬሽኑ ያዋቀረው መርማሪ ቡድን የደረሰውን ጉዳት መጠን አጥንቶ ሲጨርስ በሚያመጣው መረጃ መሰረት ደግሞ ማስተካከል የሚቻለውን አስተካክሎ ወደ ሥራ ለመግባት ታቅዷል። በዚህም ምናልባት በወራት የሚቆጠር ጊዜን ሊፈጅ እንደሚችል ታሳቢ መደረጉን ዋና ሥራ አስፈጻሚው ለቢቢሲ ገልጸዋል።

የኮምቦልቻ ኢንደስትሪያል ፓርክ በመጀመሪያው ምዕራፍ ከተገነቡት ፓርኩች መካከል ሲሆን ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ሁሉም መሰረተ ልማት የተሟላለት ፓርክ ነበር።

በመሠረታዊነት ማምረቻ ቦታዎችን ከማከራየት በተጨማሪ የውሃ፣ የመብራት፣ የቆሻሻ ማጣሪያ እንዲሁም የደኅንነት አገልግሎት የተሟላለት ነበር። ከአቀማመጥ አንጻር ደግሞ የኮምቦልቻ ኢንደስትሪያል ፓርክ አማካይ በሚባል ቦታ ላይ የሚገኝ በመሆኑ በባለሀብቶች ይመረጣል።

BBC AMHARIC


Exit mobile version