Site icon ETHIO12.COM

ትህነግ አደራጃቸው የተባሉ ማጅራት መቺዎች ተያዙ

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በቡድን ተደራጅተው በውጭ ሃገር ዜጎች ላይ ትኩረት በማድረግ የዘረፋ ወንጀል የፈጸሙ ማጅራት መቺዎች ላይ ምርመራ እያደረገ መሆኑን አስታወቀ። ትህነግ እንዳደራጃቸውም ተጠቆመ።

ፖሊስን ጠቅሶ ፋና እንደዘገበው የአዲስ አበባ ሰላም ውሎ ማደር እንቅልፍ የሚነሳው የሽብር ቡድኑ ህወሓት ስጋት ለመፍጠር ከሚያሰራጨው ሃሰተኛ መረጃ ባሻገር እኩይ ተግባሩን የሚያስፈጽሙ አካላትን በማደራጀት ማሰማራቱን አስታውቋል።

የሽብር ቡድኑ የጥፋት ተልዕኮውን የሚፈጽመበትን የትግራይ ተወላጆችን በማደራጀት ለዘረፋ ወንጀል ማሰማራቱ እንደተደረሰበት የጠቀሰው ፖሊስ፥ ይህን ለማስፈጸም ሲንቀሳቀሱ የነበሩ 24 ግለሰቦች ተይዘው ምርመራ እየተደረገባቸው መሆኑንም አስታውቋል።ተጠርጣሪዎቹ ለትውልደ ኢትዮጵያውያን ጥሪ ከመተላለፉ አስቀድሞ አዲስ አበባ የሚኖሩ የውጭ ሃገር ዜጎችን መኖሪያ ቤት ኢላማ ያደረገ የዘረፋ ወንጀል ሲፈጽሙ እንደነበርም ተመላክቷል።

በተለይም ለወንጀል ተግባር በገቡባቸው መኖሪያ ቤቶች በሰው አካል ላይ ጭምር ከባድ ጉዳት ሲያደርሱ እንደነበር የአዲስ አበባ ፖሊስ የልዩ ልዩና የተደራጁ ወንጀሎች ምርመራ ዳይሬክተር ኮማንደር አለማየሁ አያልቄ ተናግረዋል።የተፈጸመው ወንጀል በሃገራት መካከል ቅራኔ ለመፍጠር እና ከተማዋን ለውጭ ሃገር ዜጎች የተመቸች አይደለችም የሚል መልዕክት ለማስተላለፍ ያለመ እንደሆነም ነው የተናገሩት።

በዚህም ቀን ላይ የመኖሪያ ቤቶቹን በማጥናት እና ሰዎችን በማገት በሰው አካል ላይም ጉዳት በማድረስ ጭምር ወንጀል ፈጽመዋልም ነው ያሉት።በተደረገ ምርመራም ለወንጀል መፈጸሚያ የሚጠቀሙባቸው ተሽከርካሪዎች፣ የብረት መቁረጫ እና የቁልፍ መስበሪያዎች መያዛቸውን ጠቁመው፥ ወንጀል በተፈጸመባቸው መኖሪያ ቤቶችም ተሽከርካሪ፣ ላፕቶፖች እና ቴሌቪዥን በማስረጃነት መያዛቸውን ገልጸዋል።በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተደረገባቸው ካሉ ግለሰቦች መካከል ከዚህ ቀደም በፈጸሙት ተመሳሳይ የወንጀል ድርጊት የ20 እና የ15 አመት እስራት ተፈርዶባቸው ከእስር ያመለጡ እንደሚገኙበትም ነው የገለጹት።


Exit mobile version