ETHIO12.COM

በምሥራቅ ወለጋ ዞን 312 የአሸባሪው ሸኔ አባላት እጅ ሰጡ

በምሥራቅ ወለጋ ዞን የአባ ገዳዎችን ጥሪ የተቀበሉ 312 የአሸባሪው ሸኔ አባላት እጅ መስጠታቸውን የዞኑ አስተዳደር አስታወቀ።

እጃቸውን የሰጡት የቡድኑ አባላት አሸባሪው ሸኔ በአፉ ለኦሮሞ ሕዝብ እታገላለሁ ቢልም እስካሁን በወሰደው እርምጃ የሰላማዊ ሰዎችን ሕይወት ሲያጠፋ፣ አካል ሲያጎድል፣ የሕዝብ ሀብት ንብረት ሲዘርፍ እና ሲያወድም ብቻ ማየታቸውን ተናግረዋል።

“ከዚህ በመነሳትም የያዝነው መንገድ የተሳሳተ መሆኑን በመረዳት አባ ገዳዎች ያደረጉልንን ጥሪ ተቀብለን ለመንግሥት እጃችንን ሰጥተናል” ብለዋል በሳሲጋ እና ዲጋቲ ወረዳዎች እጃቸውን የሰጡ የቡድኑ አባላት።

“የእነርሱ ዓላማ ሕዝቡን አደህይተው ለራሳቸው በአቋራጭ መክበር መሆኑን ተረድተናል፤ ሌሎች ወጣቶችም ይህንኑ ዓላማቸውን ተረድተው ራሳቸውን ከስህተት እንዲጠብቁ እንመክራለን” ብለዋል፡፡

እጃቸውን ከሰጡት በተጨማሪ 112 የተለያዩ መሳሪያዎች፣ ከ2 ሺሕ 100 በላይ የተለያዩ ጥይቶች፣ ከአርሶ አደሩ የተዘረፈ 949 ኩንታል እህል፣ ከ600 በላይ ከብቶች እና ከ6 ሺሕ በላይ ፍራሾች መያዛቸውን ኦቢኤን ዘግቧል።


Exit mobile version