Site icon ETHIO12.COM

ከአብን – የተሰጠ መግለጫ

የአብን መግለጫ!…

ለመላው የአማራ ህዝብ ፣
ለንቅናቄያችን አባላትና ደጋፊዎች ፣
ለመላው ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን፡፡
………
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) የብሔራዊ ሥራ አስፈፃሚ በሀገራዊና ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ የተሰጠ የአቋም መግለጫ፡፡

በሀገራችን ኢትዬጵያ ዉስጥ ለበርካታ አስርተ-አመታት ያክል ስሁት የሆነ የጨቋኝ ተጨቋኝ ትርክት ገዥ መንግስታዊ መርህ ሆኖ በመተግበሩ ምክንያት በርካታ ህዝብ በማንነቱ፣ በህይወቱ እና በክብሩ ላይ ዘግናኝ ግፎች ተፈጽመዉበት እና ለከፍተኛ የንብረት ዉድመትም የተዳረገ ሲሆን ሀገራችንም የመፍረስ አደጋ ተጋርጦባት ቆይቷል። በማንነቱ የተገፋው ህዝብ እልህ አስጨራሽ ትግል ቢያደርግም በመንግሥት በኩል ፈጣን ምላሽ ባለማግኘቱ ሀገር አፍራሹና አማራ ጠሉ ትህነግ ፍላጎቱን በጉልበት ለመጫን የሰሜን ዕዝ የሀገር መከላከያ ሠራዊት አባላትን ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም በመጨፍጨፍ የሀገር ክህደት እንዲፈፅም ፣ ሀገረ መንግሥቱን ለማፍረስና የአማራ ህዝብን በገሃድ ለማጥፋት ሙሉ ወረራ እንዲከፍት አስችሎታል፡፡

በትግራይ ወራሪ ኃይል ብዙ ሺህዎች ረግፈዋል ፣ ለአሰቃቂ አካላዊና ሥነልቡናዊ ጥቃት ተዳርገዋል፡፡ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎች ከቀያቸው ተፈናቅለው ሜዳ ላይ ወድቀዋል፡፡ በአማራና በአፋር ክልሎች ከግማሽ ትሪሊዮን ብር በላይ ቁሳዊ ውድመት ደርሷል፡፡ ዛሬም ትህነግ በየግምባሩ ሁለገብ ወታደራዊ ፣ ፖለቲካዊና ዲፕሎማሲያዊ ጥቃት በሀዝባችን ላይ እየፈፀመ ይገኛል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ የፌዴራል መንግሥቱ በታህሣሥ 29 ቀን 2014 ዓ.ም በሀገር ላይ ይቅር የማይባል ክህደት የፈፀሙና ህዝብ ቀስቅሰው ፣ ጦር አደራጅተው በመምራት ለዚህ ሁሉ ሀገራዊ ውድመት የዳረጉንን ፣ በሀገሪቱ ፓርላማ በአሸባሪነት የተፈረጀው ድርጅት ቁንጮ አመራሮችን ያለምንም ቅድመ ሁኔታና ማብራሪያ ከእስር በመፍታት የሀገርና የህዝብን ጥቅምና ክብር በፅኑ የሚጎዳ ታላቅ ታሪካዊ ስህተት ፈጽሟል፡፡ ለሀገር ህልውናና ለህዝባችን ሰላምና ደህንነት በመላው ኢትዮጵያውያን የተከፈለውን መስዋዕትነት ዋጋ የሚያሳጣ ፤ በይቅርታና በሰብአዊነት ስም የተፈፀመ ኢሰብአዊና ኢፍትሃዊ ውሳኔ መሆኑንም ያምናል፡፡
እንዲህ ዓይነቱ ግብታዊና ኢፍትሃዊ ውሳኔ በመንግሥት ህጋዊና ሞራላዊ መሰረት ላይ እየጎሉ የመጡትን ክፍተቶች የሚያረጋግጥ ፣ በመንግሥትና በህዝብ መካከል በየጊዜው እየጨመረ የመጣው ርቀትና ያለመተማመን የሚያጎላ መሆኑን ይገነዘባል፡፡ ከሁሉም በላይ አመፅንና አመፀኞችን የሚሸልምና ሰላማዊና ህጋዊ ፖለቲካን ክፉኛ የሚጎዳ ውሳኔ በመሆኑ በአፋጣኝ እርምት እንዲያገኝ ይጠይቃል፡፡
አስቸኳይ ትኩረት የሚሹ ጉዳዮችን በተመለከተ
ንቅናቄያችን ሀገራችንና ህዝባችን ከተጋረጠባቸው የህልውና አደጋ በአስተማማኝ እንዲወጡና በነቢብ የምናስተጋባው ኢትዮጵያዊ አንድነት ፣ ወንድማማችነትና ይቅር ባይነት በተግባርና በዘላቂነት መሰረት እንዲቀጥል በአንኳር አጀንዳዎች ላይ የሚኖረንን አረዳድና አቋም እንደገና መፈተሸ እንዳለብን በፅኑ ያምናል፡፡

  1. የህልውና ጦርነቱ ቀጣይነት

አብን በአሁኑ ወቅት በሀገራችንና በህዝባችን ላይ የተደቀነው የህልውና አደጋ በአስተማማኝ እንዳልተቀለበሰ ፣ ትህነግ አሁንም አደገኛ አጥፍቶ ጠፊ ኃይል እንደሆነና በየግንባሩ ያለው ጦርነት ገና እንዳልተቋጨ ፣ እንዲያውም በአዲስ መልኩ እያገረሸ መሆኑን ይገነዘባል፡፡
ይህንን ጥሬ ሀቅ በሚቃረን መልኩ መንግሥትና ገዥው ፓርቲ ጦርነቱ በአሸናፊነት እንደተደመደመ ፣ የህልውና አደጋው እንደተቀረፈና እንደ ሀገር ፊታችንን ወደ ድህረ ጦርነት ስራዎች ማዞር እንዳለብን በሰፊው እያስተጋቡ ይገኛሉ፡፡
እንዲህ ዓይነት ከእውነታው የተጣረሱና ህዝብን የሚያዘናጉ ድርጊቶች ሀገራችንን በድጋሚ ዋጋ የሚያስከፍሉ በመሆናቸው ፣ መንግሥት ካለፉት ስህተቶቹ ተምሮ ተቀዳሚ ሃላፊነቱ የሆነውን ሰላምና ደህንነት የማስከበር ግዴታውን በአግባቡ እንዲወጣ እናሳስባለን፡፡ ህዝባችንም ለአፍታም ቢሆን ሳይዘናጋ በሁሉም አውደ ግንባሮች የሚያደርገውን ፍልሚያ አጠናክሮ እንዲቀጥል በአክብሮት እንጠይቃለን፡፡

  1. በህዝባችን ላይ የቀጠሉት የጅምላ ጥቃቶች

ንቅናቄያችን በሀገራችንና በህዝባችን ላይ የተከፈተው ጦርነት በርካታ ውስጣዊና ውጫዊ ተዋንያን የሚሳተፉበት መሆኑን ይገነዘባል፡፡ አማራ ጠል የሆነው ሥርዓት ያስከተለውንና እስከዛሬም በመላ ሀገሪቱ በህዝባችን ላይ ያለማሰለስ የሚደረገውን የዘር ጭፍጨፋ ፣ መሳደድና ውድመት የህልውና ጦርነቱ አካል አድርጎ ይወስዳል፡፡
በዚህ ረገድ ከትግራይ ወራሪ ኃይል ጋር በተናበበና በተቀናጀ መልኩ በኦሮሚያና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች የቀጠሉ የጅምላ ግድያና ማፈናቀል ድርጊቶች እንዲቆሙ ፤ በተለይ በወለጋና በሸዋ ደራ በኦነግ/ሸኔ አማካኝነት የሚፈፀመው ግልፅ ወረራ አስቸኳይ ምላሽ እንዲያገኝ የሚመለከታቸው መንግሥታዊ አካላት ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ ያሳስባል፡፡ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ትህነግና ኦነግ/ሸኔን አስመልክቶ ያሳለፈውን ውሳኔ ተግባራዊነቱን እንዲቆጣጠር አበክሮ ይጠይቃል፡፡

  1. በጦርነቱ የወደሙ አካባቢዎች መልሶ ግንባታ

አብን የትግራይ ወራሪ ኃይል በአማራና በአፋር ክልሎች ላይ ያደረሰው መጠነ ሰፊ ጥቃት የነዚህን ህዝቦች አጠቃላይ ህይወት ክፉኛ ያመሰቃቀለና የአጠቃላይ የዘር ማጥፋቱ እቅድ አካል መሆኑን ይገነዘባል፡፡ ይህ ጉዳት ዋነኛ ሰለባዎች አፋርና አማራ ቢሆኑም ቅሉ ተፅእኖው በመላ ሀገሪቱ ፖለቲካዊ ፣ ማህበራዊና ኤኮኖሚያዊ ደህንነት ላይ የሚንፀባረቅ የጋራ ጉዳይ መሆኑን ያምናል፡፡
ንቅናቄያችን የመልሶ ግንባታ ስራው ይደር የማይባልና ከህልውና ጦርነቱ አደማደም ጋር በጥምረት ሊሰራ የሚገባ መሆኑን ፣ ይሁን እንጂ በአሁኑ ወቅት ጉዳቱን የሚመጥን ትኩረት እንዳላገኘ ያምናል፡፡ የአማራና የአፋር ህዝብ በተለይ ከመላው ኢትዮጵያውያን ፣ ከማዕከላዊ መንግሥትና ከአቻ ክልሎች ልዩ ትኩረትና ድጋፍ እንዲያገኝ ይጠይቃል፡፡

  1. ፋኖን በተመለከተ

የአማራና አፋር ህዝቦች ያደረጉት ተጋድሎም ይሁን የደረሰባቸው ውድመት ለሀገር የተከፈለ ዋጋ በመሆኑ ሂደቱና ውጤቱ ሊቃኝ የሚገባው በኢትዬጵያ ማዕቀፍ እንደሚሆን ታሳቢ ይደረጋል።

ስለሆነም በወረራው ግንባር ቀደም ገፈት ቀማሽ ለሆኑት የአማራና የአፋር ህዝቦች በዋናነት የማዕከላዊ መንግስቱ፣ የክልልና የማህበረሰብ አስተዳደሮች እንዲሁም መላው ኢትዮጵያውያን ወገኖች ልዩ ትኩረት እና ድጋፍ እንዲያደርጉ እየጠየቅን በተጓዳኝ ለሀገርና ለህዝብ ህልውና ግንባር ቀደም የተሰለፉት የአማራና የአፋር ክልል የፀጥታ ኃይሎች የመልሶ ግንባታ እንቅስቃሴው አንድ የትኩረት ማዕከል ሆነው ድጋፍ ሊደረግላቸው ይገባል፡፡

በተለይም በዋናነት ትጥቅና ስንቃቸውን ራሳቸው በማሰናዳት፣ የስልጠናና የውጊያ ግብዓቶችን ከራሳቸው በማቅረብ፣ አስቻይ የዕዝ መዋቅሮችን አቋቁመው በግንባር በመሰለፍ አኩሪ ታሪክ የሰሩት የአማራ ፋኖዎች ድጋፍ ሊደረግላቸው ይገባል። ፋኖዎች እጅግ ፈታኝ ነገር ግን ወሳኝ በሆነው የወረራ ወቅት የሀገርና የህዝብ አለኝታነታቸውን በመስዋዕትነት አረጋግጠዋል። ከሀገር መከላከያ ሰራዊት አመረሮችና አባላት ጋር በመተባበር፣ መረጃዎችና ግብዓቶችን በመለዋወጥና በግንባር ስምሪት በመውሰድ ከወራሪው ሀይል ጋር ተፋልመዋል። ስለሆነም የፋኖ ሰራዊት የኢትዬጵያ ሰራዊትና የደህንነት ጥምር ሀይል አንድ አካል ሆኖ የታገለና መስዋዕትነት የከፈለ የወገን ሀይል እንደመሆኑ መጠን ቀደም ሲል ሲንከባለል የነበረው አጉል የፖለቲካ ፍረጃ ዳግም ያልተጫነውና ሀቀኛ የሆነ ምልከታ እንዲሰጠው ለማሳሰብ እንወዳለን።

በተጨማሪ ለሀገርና ለህዝብ አንድነትና ህልውና በተደረገው ታሪካዊ ፍልሚያ ወቅት አኩሪ ገድል ለፈፀሙትንና ዛሬም ከፍተኛ መስዋዕትነት ለሚከፈሉት የአማራ ፋኖዎች ተገቢው ክብርና እውቅና ሊሰጣቸው ይገባል።
ስለሆነም የፋኖ ጉዳይ ዘላቂና የከበረ ስፍራ እንዲያገኝ፣ የአንድነትና የትብብር ስልት እንዲዘረጋለትና በቀጣይ የህዝባችንና የሀገራችን የደህንነት ጋሻ ሆኖ እንዲቀጥል ለማስቻል ሁሉም ባለድርሻ አካላት በጋራ እንዲመክሩና እንዲሰሩ አብን በአፅንኦት ያሳስባል፡፡

  1. የሀገራዊ ውይይትና ምክክር ሂደት

አብን ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ እንደገለፀው ብሔራዊ ፖለቲካችን ከዜሮ ድምር የሥልጣን ግብግብ ወደ ዘላቂ ሰላምና ልማት ጎዳና እንዲሻገር ከሚያስፈልጉ ግብአቶች አንዱ የማያቋርጥ ሀገራዊ ምክክር ፣ ድርድርና እርቅ ሂደት መሆኑን በፅኑ ያምናል፡፡
አብን በፖለቲካ ኃይሎችና ልሂቃንም ሆነ በማህበረሰቦች መካከል የሚደረጉ ብሔራዊ ውይይቶች ግልፅ ፣ አካታችና ተአማኒ መሆናቸውን ፤ የችግራችንን የስር መንሥኤዎች ማስተናገዳቸውን ፤ የምክክር ሂደቱም ግልፅ ኃላፊነት የተሰጠው ፣ በተገቢ አወቃቀር ፣ ህግጋትና ሥርዓተ ደንብ መመራቱን ለማረጋገጥ የበኩሉን ጥረት እያደረገ ይገኛል፡፡
በመሰረታዊነት በድርድር ስም የአማራ ህዝብ የተገፋበትና ሀገሪቱን ለትልቅ ኪሳራ የዳረጋት ፣ ህዝባችንን ነጥሎ የጥቃት ዒላማ ያደረገው የ1983 ዓ.ም ዓይነት የአሸናፊዎች ድግስ ለሁለተኛ ጊዜ እንዳይደገም እንደምንሰራ ፤ በአንፃሩ ሁሉም ኢትዮጵያውያን ተገቢ ውክልናና ጉልብትና (empowerment) የሚያገኙበት ሥርዓት የሚፈጥር ፍሬያማ ውይይት እንዲኖር የሚጠበቅብንን ሁሉ እንደምናደርግ ከወዲሁ እናረጋግጣለን።

  1. ለተጠናከረ ትግል የየድርሻችንን እንወጣ

ውድ ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን ፣
የተከበርከው የአማራ ህዝብ ፤
መላው የንቅናቄያችን አባላትና ደጋፊዎች :-

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ሀገራችን ኢትዮጵያ ከምትገኝበት የታሪክ አጣብቂኝ ውስጥ ለመውጣትና በአስተማማኝ ጎዳና ለመራመድ ከምንጊዜውም በላይ የመላው ኢትዮጵያውያን ርብርብ አስፈላጊ መሆኑን ጠንቅቆ ይረዳል፡፡
በዚህ ረገድ ንቅናቄያችን ተቀዳሚና የማይናወጥ ታማኝነቱ ለሀገረ መንግሥቱ ህልውናና ሉዓላዊነት ፣ ለህዝባችን ክብርና ጥቅሞች እንጂ ለየትኛውም ሥርዓተ አገዛዝ አለመሆኑን በድጋሚ ማረጋገጥ ይፈልጋል፡፡
ስለሆነም የሀገራችንና የህዝባችንን ጉዳይ በሚመለከቱ አበይት ውሳኔዎች ድርጅታችን አብን ባይተዋር በማይሆንበትና መንግስት ከሁሉም ባለድርሻ አካላት ጋር በባለቤትነት የማማከርና የመወሰን ሃላፊነቱን እንዲወጣ ሲል ያሳስባል፡፡

አብን በኢትዮጵያ ሀገራችን አጣፋንታ ላይ ከሌሎች ሀገራዊ ኃይሎችና ማህበረሰቦች ጋር በጋራ ፣ በባላቤትነትና ዙሪያ ገብ አሸናፊነት ለመስራትና ለመወሰን ፤ በተለይም በአማራ ህዝብ ጉዳዮች ላይ ወሳኝ የፖለቲካና የሀሳብ አስተዋፅኦውን ለማስቀጠል ሁሉም ባለድርሻ አካላት በአንድነት እንዲሰለፉ ጥሪ ያቀርባል፡፡

በዚህ መሰረት ጀግኖቹ የሀገር መከላከያ ሠራዊት ፣ የአፋርና የአማራ ልዩ ኃይሎችና ህዝባዊ ሚሊሻዎች ፣ እንዲሁም ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ለሀገራቸውና ለህዝባቸው መስዋዕት እየከፈሉ ያሉት የአማራ ፋኖዎች ከምንጊዜውም በላይ ውስጣዊ አንድነታቸውን ፣ የዓላማ ፅናታቸውን ፣ ድርጅታዊ ዲሲፕሊናቸውን በማስጠበቅ አሸባሪና አጥፍቶ ጠፊ ኃይሎችን በማያዳግም ሁኔታ እንዲደመስሱ ጥሪ ያቀርባል፡፡
የትግራይ ወራሪ ኃይልና ግብረ አበሮቹ በከፈቱብን ጠቅላላ ጦርነት የሀገራችንንና የህዝባችንን ህልውና ለማስጠበቅ በግንባር ከመዋደቅ ጀምሮ በአስተማማኝ ደጀንነት ገንዘባችሁን ፣ ጉልበታችሁን እውቀታችሁን ሳትሰስቱ የከፈላችሁ በሀገር ውስጥና በውጭ የምትገኙ ምሁራን ፣ ባለሀብቶች ፣ የፖለቲካ ኃይሎች በአንድ በኩል ጦርነቱን በሙሉ ድል ለማጠናቀቅ ፣ በተጓዳኝም ህዝባችንና ሀገራችንን መልሶ ለማቋቋምና በዘላቂነት ለመገንባት ከቀደመው የላቀ ስራና ሃላፊነት እንድትንቀሳቀሱ ጥሪ ያቀርባል፡፡

አንድ አማራ ለሁሉም አማራ ፤ ሁሉም አማራ ለአንድ አማራ !
አዲስ አበባ ፣ ሸዋ ፣ ኢትዮጵያ
ጥር 1 ቀን 2014 ዓ.ም

Exit mobile version