Site icon ETHIO12.COM

አብይ አሕመድ ከፕሬዚዳንት ባይደን ጋር በስልክ መከሩ፤ ዜናው የተለያዩ ስሜቶች ፈጥሯል

ከገና በዓል ጋር በተያያዘ ሁለተኛው አስገራሚ ዜና ተሰማ። ዜናውን ይፋ ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ እንዳሉት ከፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ጋር የስልክ ውይይት አድርገዋል። ዜናው ኢትዮጵያና አሜሪካ መካከል የተፈጠረው መካረር በዚህ ደረጃ ይቋጫል ወይም ለውጥ ያሳያል የሚል ግምት ላልነበራቸው በሙሉ መነጋገሪያ ሆኗል። ያስደነገጣቸውም አሉ።

“የትህነግ እምብርት” የሚባሉትን አቶ ስብሃት ነጋና ቤተሰቦቻቸው ክስ ተቋርጦ እንዲለቀቁ መውሰኑ በከፍተኛ ደረጃ መነጋገሪያ በሆነበት በዚህ ወቅት፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ጋር በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ግልፅ የስልክ ውይይት ማድረጋቸውን መግለጻቸው እያነጋገረ ነው።

“በጋራ መግባባትና መከባበር ላይ የተመሰረተ ግንኙነትን ማሳደግ እንደሚያስፈልግ ተግባብተናልም” ሲሉ የውይይቱን ፍሬ ጉዳይ ያስታወቁት አብይ አህመድ፣ በሁለቱ አገሮች የሁለትዮሽ ግንኙነትና ቀጠናዊ ጉዳዮች ላይም እንደመከሩ በቲወተር ገጻቸው አስፍረዋል።

የኢትዮጵያ ጦር ወደ መቀለ መግባቱን ካቆመና የትግራይ ወራሪ ሃይል በሽንፈት ወደ ትግራይ ( አፈግፍጌ ነው ይላል) ከተመለሰ በሁዋላ፣ የትህነግ ሰራዊት አመራሮችና አሜሪካ ከአፍ ውጭ ያደገችላቸው ድጋፍ እንደሌለ ሲያስታውቁ ነበር። ይሁን እንጂ ከሳተላይት አቅጣጫ ጥቆማ ጀምሮ በሚዲያና በዓለም አቀፍ ጫና አሜሪካ ትህነግን ስትመራ እንደነበር ማስተባበል አይቻልም።

የድርጅቱ አፈ ቀላጤ አቶ ጌታቸው ረዳ “አሜሪካ ወደ አዲስ አበባ እንድነገባና መንግስት እንድንገለብጥ መመሪያ ሰጥታን ነበር” ሲሉ መናገራቸው፣ አሜሪካንም ” በፍጹም ” ስትል ማስተባበሏ አይዘነጋም። አቶ ጌታቸው ይህን ያሉት ትህነግ አዲስ አበባ ይገባል ተብሎ ሲወራ በሁለት ሳምንት ተደብድቦና ከፍተኛ ሰባዊና ቁሳዊ ጉዳት ደርሶበት መሸሹ በትግራይ ሕዝብ ዘንዳ ጥያቄ እንዳያስነሳበት እንደሆነ አስተያየት ሲሰጥ ነበር።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በቅርቡ በኢትዮጵያ ጉዳይ ከኬንያ ፕሬዜዳንት ጋር መነጋገራቸውን ሲያስታውቁ ” በኢትዮጵያ ጉዳይ ጎረቤት አገር መሽከርከር አይገባም ከእኛ ጋር ተነጋገሩ” በሚል መንግስት በውጭ ጉዳይ አማካይነት ማስታወቁ አይዘነጋም።

አስቀድመው በያዙት አቋም መነሻ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይን ለማነጋገር ፍላጎት ያልነበራቸው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዛሬ አቋማቸውን ቀይረው የስልክ ወይይት ማድረጋቸው በግልጽ መሰረታዊ ጉዳዩ ባይታወቅም፣ የአቋም ለውጥ መሆኑ ተመልክቷል። ይህ የአቋም ለውጥ በርካታ ጉዳዮችንና የተቋማትን አቋም ሊያስቀይር እንደሚችል ግምት አስጥቷል። ጉዳዩ በትግራይ ነጻ አውጪ አመራሮችና ደጋፊዎች ዘንዳ የፈጠረው ስሜት በቅላት ደረጃ እንደ አቋም ባይገለጽም ሃዘን መፍጠሩ ታውቋል።

ይህንኑ ጉዳይ አስመልክቶ ዋይት ሐውስ የወጣው መግለጫ በሁለቱ መሪዎች መካከል በአገሪቱ እየተካሄደ ስላላው ጦርነትና እንዲሁም ሰለምና እርቅ ሊወርድ የሚችሉባቸውን ዕድሎች አስመልክቶ የስልክ ውይይት መደረጉን አርጋግጧል።

ባይደን መንግስት ክስ አቋርጦ ስለፈታቸው የፖለቲካ አስረኞችን አስመልክቶ በጎ እርምጃ መወሰዱን ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ገልጸውላቸዋል። አክሎም መግለጫው ፣ መሪዎቹ በድርድር ላይ የተመሰረተ ተኩስ አቁም ማድረግን በተመለከተ መነጋገራቸውን አመልክተዋል። ድርድር ስለተባለው ግን መግለጫው በዝርዝር ያለው ነገር የለም።

በኢትዮጵያ የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት ሊሻሻል እንደሚገባው፣ ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ጋር በተቆራኘ ፖሊስ ስለያዛቸው ግለሰቦች የሰብአዊ መብት አያያዝ መነጋገራቸውንም የፕሬዚዳንቱ ጽህፈት ቤት ያስረዳል።

መንግስት ምንም ምላሽ ያልሰጠበትና በቅርቡ ተካሄዱ ስለተባሉት የአየር ጥቃቶች አንስተው መወያየታቸውን ያመለከተው መግለጫው እንደቀድሞው ሁሉ አሜሪካ ከአፍሪካ ሕብረትና አካባቢያዊ አጋሮች ጋር በመሆን ግጭቱ በሰላም እንዲያበቃ ድጋፍ እንደምትሰጠ አመልክቷል።

ዜናው ነገሮች ወደ ድርድርና ወደ ሁሉን ወዳካተተ ንግግር የሚያመራ አዝማሚያ ቢታይበትም፣ መንግስት ከመከላከያ ጭፍጨፋ ጋር በተያያዘ በቀጥታ እጃቸው አለበት የተባሉትን የትህነግ መሪዎች ክስ አለማንሳቱ፣ የተፈቱትም እንደ አቃቤ ሕግ ማብራሪያ በውሳኔው ላይ ቀጥታ ተሳታፊ ያልነበሩና በጡረታ የተገለሉ መሆናቸውን ከማስታወቁ ጋር ተያይዞ ሲታይ አሜሪካ ያነሳቸው የድርድር ሃሳብ ውሎ አድሮ ምን ዜና እንደሚያሰማ አጓጊ ሆኗል።

ከለውጡ በፊት ሁለት ዓመት ጀምሮ አገሪቱ በከፍተኛ ደረጃ ችግር ላይ መውደቋ፣ ለወሬ ነጋሪም ለሰሚውም የሚከብድ ወንጀልና ግፍ ሲፈጸም መቆየቱ፣ ጦርነቱ በይፋ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ እጅግ ሰፊ ቀውስ፣ ውድመት፣ የሰው ልጆች ክብር ጥሰት፣ መፈናቀል፣ ዝርፊያና የጅምላ ግድያ መፈጸሙ፣ ወደፊትም ለተመሳሳይ እልቂትና ውድመት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑ ያሳሰባቸው ጉዳይ በንግግር እንዲቋጭ ይወዳሉ። አብዛኞች እርቅና ሰላምን ቢሹም ወንጀለኞች ለህግ እንዲቀርቡ ይጠይቃሉ። በአመሪካ ጫናና በኢትዮጵያ ሕዝብ ቅሬታ የተወጠረው መንግስት ” የምወስደው እርምጃ ሁሉ ከኢትዮጵያ ጥቅም አንጻር ነው” ቢልም ተቃዋሚ ፓርቲዎች ተቃውመዋል። በራሱ በብልጽግና ህብረት ውስጥም መጠነኛም ቢሆን መሻከር እንዳለ እየተሰማ ነው።

ከሁሉም ወገን ያልሆኑት ግን አገሪቱ ኢኮኖሚዋ እየደቀቀ፣ ኑሮ እየጨሰና የገባችበት ጦርነት ከዓለም ሃያላን፣ እንዲሁም ከፍተኛ ተቋማትና በአግባቡ በተጠናና በተደራጀ መልኩ በመሆኑ በቀጣይ አሁን ባለው መልኩ ውጊያ ማካሄድ ሊሳን እንደሚችል ዳታ ጠቅሰው ያስረዳሉ። አምስት የነጻ አውጪ ድርጅቶችና ተቀጣሪ ነበሰ ገዳዮች በየአቅጣጫው እየተመረቱላት መሆኑንን የሚናገሩት ወገኖች፣ አሜሪካን ከዚህ በላይ እርቆ በመሄድ መገዳደል ሌላ ዋጋ እንደሚያስከፍልና ምን አልባትም ውጤቱ ኪሳራ ሊሆን እንደሚችል ያመለክታሉ።

ከወኔና ከደረሰው በደል አንጻር በስሜት መነዳት አግባብ እንዳልሆነ የሚመክሩ ” አንዳንዴም ካልነበት ወቅታዊ ሁኔታ፣ አቅም፣ እንዲሁም የተቀናቃኝን ጡንቻ በመገመት፣ በሌሎች አገሮች ላይ የደረሰውን በመገምገም ብልህ መሆን ግድ ነው” ይላሉ። በተመሳሳይ “ያበጠው ይፈንዳ” የሚሉና “ትግራይ ገብተን የተዘረፈ እናስመልስ” የሚል አቋም ያላቸው አሉ።


Exit mobile version